ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ማርያም ከኢየሱስ የሚገኘውን ሰላም እንድታማልደን ተማጸኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሮም በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ በተከበረው ዓመታዊ በዓል ላይ ተገኝተው ጸሎታቸውን አድርሰዋል። ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ባደረሱት ጸሎት ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘውን ሰላም እንድታማልድ ጠይቀው፥ በጦርነት ለተጎዳው ዓለማችን ሰላም እንዲገኝ ጸሎት አድርሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም ለሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ የመሠረት ግንባታ ምልክት የሆነውን እና በነሐሴ ወር የሚጥለውን በረዶን ለማስታወስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በየዓመቱ ነሐሴ 5 ከባዚልካው ጣሪያ ነጫጭ የአበባ ቅጠሎች የመበተን አስደናቂ ሥነ-ሥርዓት ይከናወናል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ነሐሴ 4 እና 5/358 ዓ. ም ምሽት ላይ በወቅቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለነበሩት ለፓፓ ሊቤሪያስ እና ለሮማውያን ጥንዶች ተገልጣ በተአምር በረዶ በሚወርድበት ሥፍራ ላይ ቤተ ክርስቲያን እንዲታነጽ መጠየቋን አንድ ጥንታዊ ትውፊት ያስታውሳል።

በዘንድሮው በዓልም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ሄደው በቤተ ክርስቲያኑ የተዘጋጀውን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ተሳትፈዋል።

የጸጋ ምልክት
ቅዱስነታቸው በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ስብከት፥ ተአምረኛው የበረዶ ዝናብ አስደናቂ እና አስገራሚ እንደ ነበር ገልጸው ይህም የጸጋ ምልክት እንደሆነ አስረድተዋል። የእግዚአብሔር ጸጋ በገንዘብ የሚለወጥ ሳይሆን ከእርሱ ዘንድ በስጦታ ብቻ የሚገኝ ነው” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በዚህም መሠረት ከባዚሊካው ጋር ይበልጥ ግንኙነት ያለው እና አስፈላጊ የሆነውን ምልክት እርሱም ጥንታዊውን እና ከሮም ከተማ ነዋሪዎች መፈወስ ጋር ግንኙነት ያለውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ምስል ማድነቅ እንደሚቻል አስታውሰዋል።

ይህ ጥንታዊ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና የልጇ ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ምስል ጸጋን እንደሚገልጥ ቅዱስነታቸው ተናግረው፥ በመቀጠልም፥ “በዚህ ምስል በኩል ለእኛ አስፈላጊ የሆኑትን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እና ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ እናያለን” ካሉ በኋላ ቅድስት ድንግል ማርያም ከዘመናት ሁሉ በፊት የተመረጠች፣ እንደ በረዶ ንጹህ እና የመለኮት ሙላት የሚገኝባት ናት” ሲሉ አስረድተዋል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መጥራት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም፥ “እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር እናት፣ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ የሚፈሰው የጸጋ አማላጅ ስለሆነች ምእመናን ልመናቸውን ይዘው ዘወትር ወደ እርሷ ይመጣሉ” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ሰኞ ሐምሌ 29/2016 ዓ. ም. በተከበረው በዓል ላይ የተገኙት ምዕመናን በመጭው የኢዮቤልዩ ዓመት ወደ ሮም የሚመጡ በርካታ ምዕመናን በመቅደም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ለመለመን መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ምእመናን የእውነተኛ ሰላም ስጦታን ለማግኘት ቅድስት ድንግል ማርያምን በልዩ መንገድ እንደሚማጸኗት ገልጸው፥ የሰላም ስጦታ ሊገኝ የሚችለው ሰዎች ንስሐ ከገቡና ይቅር ከተባባሉ፥ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከወሰደው፣ ለኃጢአት ስርየት በመስቀል ላይ ከፈሰሰው ከኢየሱስ ክርስቶስ ደም ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።

“የእግዚአብሔር እናት ቅድስት ማርያም ሆይ ለምኝልን!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአሌክሳንደሪያውን ቅዱስ ቄርሎስ ጸሎት ባስታወሱበት ስብከታቸው፥ ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት፣ የማሕጸንሽ ፍሬ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሸከምሽ፣ ከዓለም ፍጥረታት ሁሉ የከበርሽ ነሽና፣ የማይጠፋ ብርሃን ካንቺ ተወልዷልና የእግዚአብሔር እናት ቅድስት ማርያም ሆይ ለምኝልን!” በማለት ስብከታቸውን ደምድመዋል።

 

06 August 2024, 16:44