ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለቻይና ሕዝብ የተስፋ መልዕክት አስተላለፉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቻይና ከሚገኝ የኢየሱሳውያን ማኅበር ፕሬስ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ቅዱስነታቸው “ቻይና ቅርሶቿ መባከን የሌለባት የታላቅ ሕዝብ አገር ናት” ካሉ በኋላ በቻይና ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት በድጋሚ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቻይና በሚገኝ የኢየሱሳውያን ማኅበር የመግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ከሆኑት አባ ፔድሮ ቺያ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ የሚያተኩረው፥ ለመላው የቻይና ሕዝብ በረከት የሚሆን የተስፋ መልዕክት በማስተላለፍ ላይ እንደሆነ ታውቋል። ቃለ ምልልሱ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የግል ትዝታዎች እና አተያየቶች በወደፊቷ የቻይና ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዕጣ ፈንታ ላይ ያተኮረ እና ጠንካራ መንፈሳዊ ትኩረት የተሰጠበት እንደሆነ ታውቋል።

ትሩፋቶቻቸውን ማስቀጠል
ቻይናን ለመጎብኘት ያላቸውን ፍላጎት የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለይም በሶንግጂያንግ አውራጃ የሚገኘውን የክርስቲያኖች ረዳት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ለመጎብኘት ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በእስያ አገራት ከሚገኙ ብጹዓን ጳጳሳት እና ለእምነቱ ታማኝ ከሆነው የእግዚአብሔር ሕዝብ ጋርም መገናኘት እንደሚፈልጉ ተናግረው፥ “የእስያ ምዕመናን ብዙ አስቸጋሪ መንገዶችን የተጓዘ ቢሆንም በእምነቱ የጸና ታማኝ ሕዝብ” ሲሉ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተለይ በቻይና ለሚገኙ ወጣት ካቶሊካውያን ባስተላለፉት የተስፋ ጽንሰ ሐሳብ አጽንኦት ሰጥተው እንደተናገሩት፥ ቀድሞውኑ የተስፋ ሊቃውንት ለሆኑት የተስፋ መልዕክት ማስተላለፍ መደጋገም እንደሚሆንባቸው ገልጸው፥ ይህም መልካም መሆኑን አስረድተዋል። የቻይና ሕዝብ ቅርሶቹን ማባከን እንደሌለበት የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ታላቁ የቻይና ሕዝብ ትሩፋቱን በትዕግስት ማስቀጠል አለበት ብለዋል።

ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ፊትለፊት

ትችትን መቋቋም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቃለ ምልልሳቸው ወቅት፣ በመንበረ ጵጵስናቸው በማሰላሰል፣ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ከልዩ ልዩ የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ሐላፊዎች ጋር በመተባበር እና በመደማመጥ ማበርከታቸውን አስረድተው፥ ትችት ምንም እንኳን ገንቢ ባይሆንም ሁል ጊዜ እንደሚረዳ እና አንድን ነገር እንዴት ማከናወን እንደሚገባ ስለሚያሳስብ ጠቃሚ ነው ብለዋል።

ትችትን ለመቋቋም ከሚደረግ ጥረት በስተጀርባ አንዳንድ ጊዜ መልካም ትችት ሊኖር እንደሚችል የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ አንዳንድ ጊዜ በትናንሽ ቡድኖች መካከል ለምሳሌ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደሚታይ ሕመምን ሊያስከትል የሚችል ተቃውሞ ሲያጋጥም መታገስ እንደሚገባ ገልጸው፥ ችግሮች ወይም የብቸኝነት ጊዜያት ሁል ጊዜ የሚፈቱት ከእግዚአብሔር በሚገኝ መጽናናት እንደሆነ አስረድተዋል።

ጦርነት እና ሌሎች ፈተናዎች

እንደ የቤተ ክርስቲያን መሪነት እስካሁን ያጋጠሙትን ብዙ ተግዳሮቶችን፥ በተለይም የኮቪድ ወረርሽኝ ትልቅ ፈተናን እና እንዲሁም በተለይም በዩክሬን፣ በምያንማር እና በመካከለኛው ምሥራቅ ባሁኑ ጊዜ ያለውን የጦርነት ፈተናን ቅዱስነታቸው አስታውሰው፥ የቅዱስ ቶማስ ሞርን አስተምህሮ በመከተል ዘወትር ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እንደሚሞክሩ አስረድተው፥ ነገር ግን ይህ በማይሰራበት ጊዜ በትዕግስት እና በቀልድ ስሜት እንደሚወስዱት ተናግረዋል።

የግል ቀውሶች

እንደ ኢየሱሳውያን ማኅበር አባል በምንኩስና ሕይወታቸው አንዳንድ ቀውሶች በግል ደረጃ ማጋጠማቸው የተለመደ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እነዚህ ቀውሶች ሰው መሆናቸውን ይገልጻሉ ሲሉ አስረድተዋል። ነገር ግን ቀውሶች በሁለት መንገዶች እንደሚሸነፉ፥ የመጀመሪያ ምን ያህል ውስብስብ መሆናቸውን ለይቶ ማወቅ፣ ሁለተኛው የሰው ልጅ ችግርን ብቻውን መወጣት ስለማይችል በሌሎች ሰዎች ዕርዳታ መታገዝ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፥ በማከልም የእግዚአብሔርን የምህረት ጸጋ እና ትዕግስቱን መጠየቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በድሆች፣ በወጣቶች እና በጋራ መኖሪያ ምድራችን ላይ ማሰላሰል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2019 ዓ. ም. ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ቅድሚያ በተሰጡባቸው አራት ጠቅላላ ሐዋርያዊ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ በማስተንተን፣ መንፈሳዊ ልምምዶችን እና ማስተዋልን ማሳደግ፣ ከድሆች እና ከተገለሉት ጋር መጓዝን፣ ከወጣቶች ጋር በመሆን የወደፊት ተስፋን ማመቻቸት እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን መንከባከብ እንደሆኑ ገልጸዋል። እነዚህ አራት ርዕሠ ጉዳዮች ሊለያዩ የማይችሉ መሆናቸውን ገልጸው፥ በኅብረት መጓዝ፣ ማስተዋል እና ሚስዮናዊ ሥራ የኢየሱሳውያን ማኅበር የመሠረት ድንጋይ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።

የቤተ ክህነት አገልግሎት እጥረት እና የዓለማዊነት ፈተናዎች

የቤተ ክርስቲያኗን የወደፊት ሁኔታ በተመለከተ አንዳንዶች እንደሚሉት፥ የሟቹን የካርዲናል ሄንሪ ዴ ሉባክ መልዕክት በመጥቀስ፥ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ቁጥር ማነስ እና የዓለማዊነት መንፈስ እንዳያጠቃን መጠንቀቅ እንደሚገባ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እነዚህ ሁለቱ ቤተ ክርስቲያንን ሊጎዱ የሚችሉ በዘመናችን ውስጥ እጅግ የከፉ ጠላቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ እርሳቸውን በመተካት በመንበረ ጴጥሮስ ላይ ለሚሆን የቤተ ክርስቲያን መሪ ባስተላለፉት ምክር ለጸሎት አስፈላጊነት አጽንኦት በመስጠት፥ “እግዚአብሔር በጸሎት በኩል ይናገራል” ሲሉ አስረድተዋል።

 

 

10 August 2024, 15:59