ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጥሩ ፖለቲካ ከዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት ጋር አብሮ እንደሚሄድ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው በቪዲዮ መልዕክታቸው፥ በአሁኑ ጊዜ ፖለቲካ ጥሩ ስም ባይሰጠውም ከሚባለው የበለጠ ክቡር እንደሆነ ገልጸው፥ ወደ ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት መገስገስ ከመልካም ፖለቲካ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ በኩል ይፋ ባደረጉት የቪዲዮ መልዕክት፥ “ዛሬ ፖለቲካ ሙስና እና ቅሌት የሚታይበት እንዲሁም ከሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ የራቀ በመሆኑ ጥሩ ስም እንደሌለው ገልጸው፥ ፖለቲካ ሀብታም ለመሆን ወይም ስልጣን ለመያዝ በሚያስቡ ሰዎች ልብ ውስጥ የሚገኝ እንደ ሆነ፣ በተለመደው ዕይታ ፖለቲካ አንዳንድ ድብቅ የግል ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የሚያራምዱት በመሆኑ በጥርጣሬ ዓይን ሊታዩ እንደሚገባ የሚያሳስብ ይምሰል እንጂ የቅዱስነታቸው መልዕክት ፖለቲካ ከዚህ የተለየ እንደ ሆነ ግልጽ አድርጓል።
ከዚህ ሃሳብ የተለየ ሌላ ዓይነት ፖለቲካ ሊኖር እንደሚችል፥ ለሕዝብ፣ በተለይም ለድሆች አገልግሎት የሚውል ፖለቲካ መኖሩን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተው፥ ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነትን ለመቀጠል ከፈለግን ሁላችንም ጥሩ ፖለቲካ ያስፈልገናል” ብለዋል።
ከድምጽ ጋር የቀረቡት ምስሎችም ይህንን በትክክል ለማሳየት የሞከሩ ሲሆን፥ እውነተኛ ሕይወትን በሁለት የተለያዩ መንገዶች በማቅረብ በመጀመሪያ ስደተኛ ሴት፣ ሥራ አጥ ሰው፣ የሚጠጣ ውሃ የሌላቸው ልጆች፣ ጎዳና ላይ የቀረ ሰው ሲሆን ሌላው እና ሁለተኛው ሰዎች ለችግራቸው ምላሽ ያሚያገኙበት እና ለሚያጋጥማቸው አደጋዎች በዘላቂነት ምላሽ እንደሚገኝ የሚያስይ ሲሆን፥ ይህም ዓለማች ጥሩ እና መጥፎ የፖለቲካ ሂደቶች እንዳሉት ያረጋግጣል።
ለሰዎች የሚሰጥ የበጎ አድራጎት አገልግሎት
ፖለቲካ ለተሳታፊዎቹ የሞራል ባህሪ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል የገለጸው መልዕክቱ፥ ፖለቲካ ለቅድስና እና ለበጎነት የሚሆን ጥሪ ሊሆን እንደሚችል መልዕክቱ ያስገነዝባል። በዚህ ረገድ የቪዲዮ መልዕክቱ መጀመሪያ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ፖለቲካ “የጋራ ጥቅምን ስለሚፈልግ ከፍተኛ ከሚባሉት የበጎ አድራጎት ዓይነቶች አንዱ ነው” በማለት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ የተናገሩትን አስታውሰዋል።
ፖለቲካ ግለኝነትን በማሸነፍ ለበለጠ ሕዝባዊ የጋራ ጥቅም የሚውል የማኅበራዊ ንቃተ-ህሊና ጉዳይ እንደሆነ ቅዱስነታቸው ገልጸው፥ ክርስቲያኖች በተለይም ምእመናን በፖለቲካ ሕይወት ውስጥ እንዲሳተፉ፣ የበለጠ ፍትሃዊ እና ደጋፊ የሆነ ማኅበረሰብን ለመገንባት የተጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ጭብጥ ላይ በማስተንተን "ግለሰቦች የተቸገሩትን መርዳት ይችላሉ፤ የወንድማማችነት እና የፍትህ ማሕበራዊ ሂደቶችን ሲጀምሩ ወደ በጎ አድራጎት መስክ እና ሰፊ በሆነው ፖለቲካዊ በጎ አድራጎት ውስጥ የሚገቡ መሆኑን “ሁላችን ወንድማማቾች ነን” በማለት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2020 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ላይ ገልጸዋል።
ፖለቲካን ለድሆች አገልግሎት ማዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልካም ፖለቲካ በግዙፍ ሕንፃዎች ውስጥ የተከማቸ ሳይሆን ነገር ግን እየሆነ ያለውን በመመልከት ለድሆች አገልግሎት የሚውል እንደሆነ ገልጸው፥ አንድ ፖለቲከኛ ለውይይት፣ ለትብብር እና ለሰብዓዊ ክብር ቁርጠኝነት ቦታን የሚሰጥ መሆን አለበት ብለዋል።
ቅዱስነታቸው “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ውስጥ አፅንዖት የሰጧቸውን ቁልፍ ጉዳዮች በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል፥ የኅብረተሰብ መሠረታዊ የዕድገት ውጥኖች ሳይሳኩ መቅረታቸው፥ እንደ ረሃብ፣ ድህነት፣ ጦርነት እና የአካባቢ ቀውሶችን የመሳሰሉ ችግሮች በተሳሳተ የስልጣን ጥመኞች የፖለቲካ አመራር ምክንያት ተባብሰው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ተግዳሮቶች
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በበኩላቸው፥ “የፖለቲካ መሪዎች እኛ መርጠናቸው ሰዎች በመሆናቸው ልንጸልይላቸው ይገባል” ብለው፥ “በንግግር እና በሃሳብ ለፖለቲከኞች ያለንን ንቀት ከማባባስ ይልቅ በምንፈልገው መንገድ እንዲያስተዳድሩን ልናግዛቸው ይገባል” ያሉትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማሳሰቢያ አስታውሰዋል።
ፖለቲከኞች ራሳቸውን፣ ጊዜያቸውን፣ የቤተሰብ ሕይወታቸውን፣ አቅማቸውን እና ጉልበታቸውን በሙሉ
ለአገልግሎት እንደሚያውሉት የገለጹት አባ ፍሬደሪክ፥ ፖለቲከኞችን “ስግብግቦች፣ የስልጣን ጥመኞች እና ገንዘብ ወዳጆች” ብሎ ማሰብ ቀላል እነደሆነ እና አንዳንዴም እውነት ቢሆንም ነገር ግን በዚያው ልክ ለጋራ ጥቅም የሚሠሩ ብዙ ፖለቲከኞች መኖራቸውን ገልጸው፥ እኛ ምን እየሰራን እንገኛለን? በእነርሱ ቦታ ብንሆንስ ምን እናድርግ ነበር? በማለት ጠይቀው፥ ማድረግ የምንችለው ጥቂት ነገር ቢኖር እርሱም ለፖለቲከኞች መጸለይ ነው” በማለት አስገንዝበዋል።