ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በማቅረብ ላይ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በማቅረብ ላይ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ኢየሱስን አንዴ ካገኘነው ለግላችን ብቻ ልናደርገው አንችልም” ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እስከ መጭው ሰኞ ድረስ በማዳጋስካር በመካሄድ ላይ ለሚገኝ ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ምዕመናን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመሆን ያላቸውን ጥልቅ ፍላጎት እንደገና እንዲገነዘቡት እና የእርሱን ፍቅር ለግላቸው ከማድረግ ይልቅ ለሌሎችም እንዲያካፍሉ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የክርስቲያን ማኅበረሰባችሁ ወንዶች እና ሴቶች ወደሚያስፈልጋችሁ እና ወደሚጠቅማችሁ ነገር እንድትመለሱ፣ ለቅዱስ ቁርባን የምታቀርቡትን ስግደት እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመሆን የሚያነሳሳችሁትን ፍላጎት በድጋሚ እንድትገነዘቡት አበረታታችኋለሁ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአፍሪካዊቷ ደሴት ማዳጋስካር ውስጥ ከነሐሴ 17-20/2016 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ ለሚገኝ ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ በላኩት የድጋፍ ቃል፥ “ለቅዱስ ቁርባን ያላችሁት የስግደት ስሜት እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመሆን ያላችሁትን ፍላጎት በድጋሚ እንድታገኙት” በማለትም አሳስበዋል።

ለቅዱስ ቁርባን የሚሰጥ አክብሮት አጥብቆ መያዝ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለማዳጋስካር ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ለሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማሪ ፋቢየን ራሃሪላምቦኒያይን በላኩት መልዕክታቸው፥ “በቅዱስ ቁርባን በኩል ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መቅረብ በተጠራችሁትም መሠረት እያንዳንዳችሁ ታድጉ ዘንድ አስተዋጽዖ ያደርጋል” ብለው፥ በማዳጋስካር በመካሄድ ላይ የሚገኘው ብሔራዊ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ከቅዱስ ቁርባን የወጣቶች እንቅስቃሴ መቶኛ ዓመት ጋር አንድ ላይ በመከበር ላይ እንደሚገኝም አስታውሰዋል።

ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በማያያዝ ጉባኤውን በጸሎት መተባበራቸውን እና ለተሳታፊዎች በሙሉ ወንድማዊ ሰላምታ መላካቸውን ገልጸው፥ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤው ለሁለተኛው ምዕራፍ የሲኖዶሱ ጉባኤ በምናዘጋጅበት ወቅት የሚካሄድ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው አስረድተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስን ለራሳችን ብቻ ማድረግ አንችልም!
“የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ አጋጣሚ እርስ በርስ የመገናኘት፣ የመጸለይ እና ከሌሎች ጋር በመሆን የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በመከተል በቅዱስ ቁርባን የመሳተፍን አስፈላጊነት እንደገና እንድታውቁ ይረዳችኋል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስን በስግደት እና በቅዱስ ቁርባን አንዴ ከተቀበልነው በኋላ ለራሳችን ብቻ ከማድረግ ይልቅ ፍቅሩን ለሌሎችም በመመስከር ሚስዮናውያን እንሆናለን” ብለው፥ “ኢየሱስ ክርስቶስን በስግደት ካገኘነው እና በቅዱስ ቁርባን ከተቀበልነው በኋላ ለራሳችን ብቻ ማድረግ አይቻልም” ብለዋል።

ቅዱስ ቁርባን ሌሎችን እንድናፈቅር ያስገድደናል!
"ቅዱስ ቁርባን ለባልንጀራችን ያለንን ጥልቅ ፍቅር እንድናደርግ ያስገድደናል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ልባችን ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ከተዘጋ የቅዱስ ቁርባንን ትርጉም በትክክል ልንረዳው እና ልንኖረው አንችልም” ብለዋል።

ስለዚህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ተካፋዮችን እና መቶኛ ዓመት የሚያከብሩ የቅዱስ ቁርባን የወጣቶች እንቅስቃሴ አባላት ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን ኢየሱስ ክርስቶስን በቅዱስ ቁርባን በኩል እንዲያገኙት በማስቻል እንዲረዷቸው አደራ ብለዋል።

ሕይወትን መስዋዕትነት ለእግዚአብሔር ማቅረብ
የቅዱስ ቁርባን የወጣቶች እንቅስቃሴ አባላት ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር መስዋዕት አድርገው በማቅረብ፣ በመሠዊያው ላይ ካለው ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ በመሆን፥ ወንድሞች እና እህቶች እርሱን እንዲታውቁት፣ እንዲወዱት እና እንዲያገለግሉት እንዲረዷቸው አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ተሳታፊዎች ጉባኤያቸው ፍሬያማ እንዲሆን በመመኘት ለሁሉም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናታዊ ጥበቃን በጸሎት ተማጽነው፥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸው ግንኙነት በየቀኑ እንዲያድግ ታማልድ ዘንድ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።


 

24 August 2024, 13:42