ር.ሊጳ ፍራንችስኮስ 'ጥላቻን ለመፍጠር ማንም የእግዚአብሔርን ስም መጠቀም የለበትም' አሉ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
"ማንም ሰው በሌሎች ላይ ንቀት፣ ጥላቻ እና ዓመፅ ለማነሳሳት የእግዚአብሔርን ስም መጥራት የለበትም" ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ እለት ነሐሴ 1/2016 ዓ.ም ከአፍጋኒስታን ማሕበረሰብ አባላት ጋር በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ካደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ማብቂያ ላይ በተገናኙበት ወቅት ይህንን አቋማቸውን በጽኑ አረጋግጠዋል።
ማህበሩ በጣሊያን የሚኖሩ የአፍጋኒስታን ወንዶች እና ሴቶች መረብ አካል ሲሆን የአፍጋኒስታን ስደተኞች በጣሊያን ማህበረሰብ ውስጥ እንዲቀላቀሉ፣ ውይይትን እና የሁሉም የጎሳ ማህበረሰቦች ሰብአዊ መብቶች መከበርን በመደገፍ ላይ የተሰማሩ ናቸው።
በአፍጋኒስታን ውስጥ ያለው "አሳዛኝ" ሁኔታ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ንግግራቸውን ሲከፍቱ በአፍጋኒስታን ባለፉት አሥርተ ዓመታት ያለመረጋጋት፣ በጦርነት፣ በውስጥ መከፋፈል እና ስልታዊ በሆነ መንገድ የመሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በርካቶችን ለስደት ያዳረጉትን አሳዛኝ ክስተቶች አስታውሰዋል።
የአፍጋኒስታን ማህበረሰብ መገለጫ የሆነው የጎሳ ልዩነት “አንዳንድ ጊዜ ለመድልኦ እና ለመገለል እንደ ምክንያት ጥቅም ላይ ይውላል፣ ካልሆነም ቀጥተኛ ስደት ያስከትላል” ሲሉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው “አሳዛኝ ጊዜ አሳልፋችኋል፣ ከብዙ ጦርነቶች ጋር" ሲሉ ቅዱስነታቸው ስለሁኔታው በቁጭት ተናግረዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በተጨማሪም ከፓኪስታን ጋር በሚዋሰኑ ድንበሮች ላይ ብዙ አፍጋኒስታዊያን የተጠለሉበትን እና የፓሽቱን አናሳ ጎሳ (በአፍጋኒስታን ውስጥ ያለው አብዛኛው ጎሳ፣ ነገር ግን በፓኪስታን ደግሞ በቁጥር ኢዳጣን ናቸው) በደልና መድልዎ የሚደርስበትን አሳሳቢ ሁኔታ ጠቅሰዋል።
ሃይማኖት ልዩነቶችን በማቃለል ሊረዳ ይገባል
በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ሃይማኖት ልዩነቶችን በማቃለል ማንም ሰው ያለ አድልዎ ሙሉ የዜግነት መብት የሚሰጥበት ቦታ መፍጠር እንዳለበት አስገንዝበዋል። ይልቁንም ወደ “ተጭበረበረ” እና ወደ ብጥብጥ የሚያመራውን ግጭት ለማቀጣጠል የጥላቻ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው የሃይማኖት ሁኔታ ሊገታ ይገባዋል፣ ሐይማኖት የሰላም እንጂ የጦርነት መንስኤ ሊሆን በፍጹም አይገባውም ማለታቸው ተገልጿል።
ስለዚህም የአፍጋኒስታን ኔትዎርክ አባላት የመተማመን፣ የውይይት እና የሰላም መንገዶችን ለመገንባት በተለያዩ ሀይማኖቶች መካከል አለመግባባቶችን ለማሸነፍ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲቀጥሉ አበረታቷቸዋል።
ጥላቻና ብጥብጥ ሳይሆን ሰብዓዊ ወንድማማችነትን ማሳደግ
በዚህ ረገድ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ.አ.አ በየካቲት 4 ቀን 2019 ዓ.ም ከአል-አዝሃር ታላቅ ኢማን ጋር በአቡ ዳቢ የተፈራረሙትን የሰው ልጅ ወንድማማችነት ለዓለም ሰላም እና አብሮ የመኖር ሰነድን አስታውሰዋል። ያ ታሪካዊ ሰነድ “ሃይማኖቶች ጦርነትን፣ የጥላቻ አመለካከቶችን፣ ጠላትነትንና ጽንፈኝነትን እንዲሁም ዓመፅን ወይም ደም ማፍሰስን ማነሳሳት የለባቸውም” ሲሉ በሰነዱ ላይ ማስፈራቸው ተገልጿል፣ እነዚህም ሃይማኖቶችን ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በማገናኘት ከማጭበርበር የመነጨ ነው፣ “ከሃይማኖታዊ አስተምህሮት ማፈንገጥ የፈጠሩት ውጤቶች” ናቸው ብለዋል።
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ያቀረቡት አቤቱታ “የንግግር ባህልን እንደ መንገድ አድርጎ በመያዝ በሰላም አብሮ መኖር ለሚችሉ የጎሳ-ቋንቋ-ባህላዊ ልዩነቶችም እንደሚሠራ አስታውሰዋል። የጋራ ትብብር እንደ የሥነ ምግባር ደንብ በሁሉ የኑሮ ሂደቶች ውስጥ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጿል።
ስለዚህም "እነዚህ መመዘኛዎች የጋራ ቅርስ ይሆናሉ፣ እናም በሰዎች አስተሳሰብ እና ባህሪ ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ" በማለት "በፍፁም ተስፋ" በፓኪስታን ውስጥ ተግባራዊ ቢሆኑ እዚያ ያለውን የፓሽቱን ማህበረሰብ እንደሚጠቅሙ ገልጿል።
“ሁለት ጠቃሚ ሃይማኖቶች ባሉባቸው አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች - እስልምና እና ካቶሊካዊነት – በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ገና እለት የሙስሊም እምነት ተከታዮች ክርስቲያኖችን ለመቀበል እና ጠቦቶችን እና ሌሎች ነገሮችን በማምጣት እንዴት አብረው እንደሚኖሩ አይቻለሁ፥ እናም በትንሳኤ በዓል ክርስቲያኖች ወደ ሙስሊሞች ሄደው ለእነርሱ የሚሆን ነገር እንደሚያመጡላቸው አይቻለሁ። የእነሱ ክብረ በዓል፡ ይህ እውነተኛ ወንድማማችነት ነው እና ይህ ቆንጆ ነው” ብለዋል።
ማንም የማይገለልበት ማህበረሰብ መገንባት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የመንግስት መሪዎችን እና ህዝቦችን ለሁሉም እኩል መብት ሙሉ ዜግነት የሚያገኙበትን ማህበረሰብ በመገንባት እንዲረዳቸው” በማለት አምላክን በመማጸን ንግግራቸውን ደምድመዋል። ሁሉም ሰው እንደየራሱ ወግ እና ባህል (...)፣ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ወይም አድልዎ ሳይደረግበት መኖር የሚችልበት አለም መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ያጎሉት ሁለተኛው ዓለም አቀፍ ፈተና የሰላም ተግዳሮት ነው።
ከእዚህ ቀደም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በካዛኪስታን ዋና ከተማ አስታና በኑር-ሱልጣን አዳራሽ በተካሄደው 7ኛው የዓለም እና የባህላዊ ሃይማኖቶች መሪዎች ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ሃይማኖቶች ለዓለም ሰላም ጥማት እና በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ ለሚኖረው ወሰን የለሽ ጥያቄ እንዴት በወዳጅነት ማደግ እና ሰላምን መፍጠር እንደሚችሉ እንዲሁም ሊያበረክቱት የሚችሉትን ሚና ላይ አስምረው ተናግረው ነበር።
በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህንን በተመለከተ በተለይ ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የተወያዩበት ቢሆንም የጦርነትና የግጭት መቅሰፍት አሁንም ዓለምን እያስጨነቀ መሆኑን ተመልክቷል። ይህም በዘመናችን ያሉ ሰዎች በአክብሮት እና ኃላፊነት የተሞላበት ውይይት ለማድረግ እንዲነሳሱ ከተፈለገ በታላላቅ ሀይማኖቶች ውስጥ በንቃት ለመሰባሰብ እና ለሰላም ቅድሚያ በመሰጠት "ወደ ፊት መስፈንተርን" ይጠይቃል ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ። አክለውም ...
"እግዚአብሔር ሰላም ነው። እሱ ሁል ጊዜ በሰላም መንገድ እንጂ በጦርነት መንገድ አይመራንም። እንግዲያውስ፣ ግጭቶችን በኃይልና በማያዳግም መንገድ፣ በትጥቅና ዛቻ ሳይሆን፣ በሰማይ በተባረከና ለሰው በተገባ ብቸኛ መንገድ፣ መገናኘት፣ መነጋገር እና በትዕግስት ድርድር መፍታት እንደሚያስፈልግ አምነን ራሳችንን እንስጥ። በተለይም ወጣቱን እና መጪውን ትውልድ ከግምት ውስጥ በማስገባት እድገትን የሚያቀላጥፉ ተግባራትን እንደግፍ... በዚህ ላይ መዋለ ነዋይ እናፍሥሥ ፣ እማጸናችኋለሁ፣ በዚህ ላይ ብዙ የጦር መሳሪያ ሳይሆን ብዙ ትምህርት መስጠት አስፈላጊ ነው!” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።