ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የኢንዶኔዥያ ምእመናን ወንድማማችነትን ለማለም ድፍረት እንዲኖራቸው አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዶኔዥያ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አራተኛ እና የመጨረሻ ቀን በመዲናዋ ጃካርታ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ለምእመናኑ ባሰሙት ስብከት፥ ኢየሱስ ክርስቶስን በማድመጥ ቃሉን በተግባር መኖር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኢንዶኔዥያ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጨረሻ ቀን በሆነው ሐሙስ ነሐሴ 30/2016 ዓ. ም. በተዘጋጀው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ቅዱስነታቸው ባሰሙት ስብከት፥ “ቃሉን ማዳመጥ እና መኖር የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንድንሆን የሚያስችሉን ሁለት መሠረታዊ አመለካከቶች ናቸው” ብለዋል።

በካልካታዋ ቅድስት ቴሬዛ ዓመታዊ ክብረ በዓል ዕለት በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል (ሉቃ.5:1-11) ላይ በማስተንተን ባሰሙት ስብከት፥ እውነት በሰዎች ንግግር ውስጥ ሳይሆን ነገር ግን በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ብቻ እንደሚገኝ አስገንዝበው፥ “በክርስትና ጉዞአችን፣ በብዙ ቁስሎች እና ግራ መጋባት መካከል ወደ እውነተኛ የሕይወት ትርጉም ሊመራን የሚችል ብቸኛው የአቅጣጫ ጠቋሚው የእግዚአብሔር ቃል ነው!” ብለዋል።

በቃሉ ለመፈተሽ ፈቃደኛ መሆን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ምእመናን እንደ ደቀ መዛሙርት፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ በዓሣ ማጥመጃ ጀልባው ተሳፍሮ መስበክ ሲጀምር እንዳደረገው ሁሉ፥ የመጀመሪያ ሥራችን የእግዚአብሔርን ቃል ማዳመጥ መሆኑን አስታውሰው፥ “የእምነታችን ሕይወት የሚጀምረው ኢየሱስ ክርስቶስን በሕይወታችን ውስጥ በትሕትና ስንቀበል፣ ለእርሱ ቦታ ስንሰጥ፣ ቃሉን ስናዳምጥ እና ራሳችንን በእርሱ እንድንጠየቅ፣ እንድንፈተሽ እና እንድንለወጥ ስንፈቅድ ነው” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ “የተጠራነው የኢየሱስን ቃል ለማዳመጥ ብቻ ሳይሆን እንድንኖርበትም ነው” ብለው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስን፥ “ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል፤ መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ” ባለው ጊዜ በጌታ በማመን እንዳደረገው ሁሉ፥ እኛም ደግሞ “የወንጌልን መረቦች ወደ ባሕሩ ዓለም ውስጥ በድፍረት በመጣል በኢየሱስ እንድንታመን ተጠርተናል” ብለዋል።

ጥሪውን ላለመቀበል ሁል ጊዜ ሰበቦችን ማግኘት እንደምንችል የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከሽንፈት እና ከብስጭት ሌሊት በኋላ ለጌታ ጥሪ የታዘዘውን የሐዋርያው የጴጥሮስ ትህትና እና እምነት ምእመናን እንዲኖራቸው አሳስበው፥ “የምናጭደውን እና የምንሰበስበውን ምርት እንኳ ስናጣ ለመዝራት ልንታክት አይገባንም” ብለዋል።

ሰላምን ማለም እና መገንባት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ማጠቃለያ ላይ በተዘጋጀው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ያሰሙትን ስብከት ሲደመድሙ፥ “ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! የኢንዶኔዥያ ሕዝብ፣ አስደናቂ እና ልዩ ልዩ ደሴቶቹ መርከቦቻችሁ ላይ ወጥተው መረቦቻችሁን ወደ ባሕር መወርወርን እና ሰላምን እንደገና ለመገንባት ማለምን አትታክቱ!” ብለዋል።

“ወንድማማችነትን ለማለም ዘወትር ድፍረት ይኑራችሁ!” ያሉት ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ “የፍቅርን ዘር ለመዝራት እንድትችሉ የውይይት መንገድ በልበ ሙሉነት እንድትራመዱ፣ በባህሪያችሁ ፈገግታ ታክሎበት መልካምነትን እና ደግነትን እንድታሳዩ” በማለት አበረታቷቸዋል።

የኢንዶኔዢያ ካቶሊክ ምዕመናን የመስዋዕተ  ቅዳሴውን ሥነ-ሥርዓት በቀጥታ ስርጭት በመከታተል ላይ
የኢንዶኔዢያ ካቶሊክ ምዕመናን የመስዋዕተ ቅዳሴውን ሥነ-ሥርዓት በቀጥታ ስርጭት በመከታተል ላይ

 

06 September 2024, 10:27