ፈልግ

በቤልጂየም የሚገኘው የሉቨን ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ለዘመኑ ዓለም ክፍት መሆኑ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቤልጂየም ባደረጉት የመጀመሪያ ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ከአገሪቱ ንጉሥ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከአውሮፓ ጥንታዊ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች እና ከወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎች ጋር ተገናኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብራስልስ ውስጥ ዓርብ መስከረም 17/2017 ዓ. ም. የመጀመሪያ ሙሉ ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን የጀመሩት ከንጉሡ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሊኬን ንጉሣዊ ቤተ መንግሥት ውስጥ ባደረጉት ስብሰባ እንደ ነበር ይታወሳል።

ሁለቱም ባለሥልጣናት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በባሕሎች መካከል ውይይት እንዲኖር ላሳዩት ቁርጠኝነት እና ለድሆች ላላቸውን እንክብካቤ አመስግነዋል። በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለይም በቤልጂየም ውስጥ በከፍተኛ ትኩረት ይታይ የነበረውን የወሲባዊ ጥቃት በደል እና እያስከተለ ባለው ጉዳት ላይ ለመነጋገር ዕድል አግኝተዋል።

ንጉሡ ይህን በደል ይፋ ለመውጣት ረጅም ጊዜ የወሰደ እና ሊነገር የማይችል አሳዛኝ ጉዳይ ነበር” ሲሉ ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በበኩላቸው “ክስተቱ የቤተ ክርስቲያን ውርደት ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተው፥ “ምንም ዓይነት ጥፋት ዳግም እንዳይከሰት ቤተ ክርስቲያን የተቻላትን ጥረት ማድረግ አለባት” ሲሉ አሳስበዋል።

ቅዱስነታቸው በዚያው ቀን ከሰዓት በኋላ የ600 ዓመት ዕድሜ ያለው ታዋቂ የካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ወደሚገኝባት የሉቨን ከተማ አጭር ጉዞ አድርገዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አቶ ሉክ ሴልስ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባደረጉት ረጅም እና ጥልቅ ንግግር፥ በካቶሊክ ወግ የተመሠረተውን እና ለዘመናዊው ዓለም ክፍት የሆነውን የሉቨን ዩኒቨርሲቲ ድርብ ማንነት አንፀባርቀዋል።

“የምርምር ሥራችን ያለ አድልዎ ወይም እንቅፋት ለሁሉም ክፍት ነው” ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት፥ ይህ ነፃነት ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ እሴት ነው ሲሉ ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲያቸው በሥነ-ምግባር፣ በማኅበራዊ እና በፍልስፍና ጉዳዮች ላይ ግልጽ ውይይት የሚደረግበት ወሳኝ የፍትሃዊነት እና የሃሳብ ማዕከል እንደሆነ ገልጸው፥ “ካቶሊክ ማኅበረሰብን የሚያነቃቃ ቢሆንም ነገር ግን የሚፈታተን እንዲሁም በክርስትናው ዓለም አተያይ መሠረትም ማኅበረሰቡን ለመገዳደር የሚደፍር ወሳኝ የአስተሳሰብ ማዕከል ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው የዕለቱን ሐዋርያዊ ጉብኝት ባጠቃለሉበት ምሽት ከካኅናት በኩል ወሲባዊ ጥቃት ከተፈጸመባቸው 17 ሰዎች ጋር በግል ተገናኝተው ተነጋግረዋል። “ከሁለት ሰዓታት በላይ የፈጀው ስብሰባው የጥቃቱ ሰለባዎች የግል ታሪካቸውን እና ስቃያቸውን ለቅዱስነታቸው ለማካፈል ዕድል ያገኙበት እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱ እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰት ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ለመግለጽ ዕድል ያገኘችበት ነበር” ሲል የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።

ከሰለባዎቹ አንዷ ከስብሰባው መልስ በቀጥታ በደች ቋንቋ ለሚታተም “ዴ ሞርገን” ለተሰኘ ጋዜጣ እንደተናገረችው፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰለባዎችን ልምድ በጽሞና ካዳመጡ ከልብ መናገራቸው መልካም ተሞክሮ ነበር” በማለት ገልጻለች።

 

28 September 2024, 16:45