ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በፓፑዋ ኒው ጊኒ የሶስተኛ ቀን ውሎዋቸው 'ታላቅ ልብ ያላቸው ሰው' መባላቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ፓፑዋ ኒው ጊኒ በገቡ በሁለተኛ ቀን ከ20,000 የሚበልጡ የሀገር ውስጥ የካቶሊክ ምዕመናን ብጹእነታቸውን ለማግኘት ወደ ሰር ጆን ጊዝ ስታዲየም የጎረፉ ሲሆን፥ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ቅዱስ አባታችን ከሚመሩት የእሁዱ መሥዋዕተ ቅዳሴ ላይ ቦታ ለማግኘት ከለሊቱ 8 ሰዓት ላይ ወደ ሥፍራው እንደደረሱ ተገልጿል።
በርካቶች በፖርት ሞርስቢ በሚከናወነው በዚህ ልዩ ዝግጅት ላይ በጊዜ ለመገኘት ራቅ ካሉ የአገሪቱ ክፍሎች ለቀናት በእግራቸው ተጉዘው የመጡ ሲሆን፥ ህዝቡ ብፁዓን አባታችንን ለማግኘት በነበረው ጉጉት የተነሳ በዝማሬ እና በባህላዊ ውዝዋዜ ደስታውን ሲገልጽ እንደነበረም ተዘግቧል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በስቴዲየሙ ውስጥ በተከናወነው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መናገር እና መስማት የተሳነውን ሰው የፈወሰበት የማርቆስ ወንጌል ክፍል ላይ አስተንትኖ የሰጡ ሲሆን፥ ምዕመናን ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር የራቁ እንደሆኑ ቢሰማቸው፥ እሱ ሁሌም እንደማይረሳቸውን እና “የልቡ ማዕከል እንደሆኑ” በማስታወስ፥ “በጣም አስፈላጊው ነገር ራሳችንን ለእግዚአብሔር፣ ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንዲሁም የሕይወታችን መሪ እንዲሆን በመፍቀድ ለወንጌል ራሳችንን መስጠት ያስፈልጋል” በማለት በአጽንዖት ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ክፋት እና ጥንቆላ ህይወትን በአዎንታዊ መልኩ እንደማይለውጡ፥ ነገር ግን ሰዎችን “በውሸት እና በፍርሃት” ውስጥ አስረው እንደሚያስቀምጡ ገልጸዋል።
ብጹእነታቸው ከሰአት በኋላ በነበራቸው ቆይታ፣ በአውስትራሊያ ወታደራዊ ማመላለሻ አውሮፕላን በሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ወደምትገኘው ወደ ቫኒሞ የባህር ዳርቻ ከተማ ሁለት ሰዓታት በሚፈጀው በረራ ተሳፍረው በመድረስ ጥቂት ሰዓታትን ከአካባቢው ካቶሊኮች ጋር አሳልፈዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቆይታቸው የተለያዩ ምስክርነቶችን ያዳመጡ ሲሆን፥ በአካባቢው እየተካሄደ ላለው ሚስዮናዊ ስራ ምስጋናቸውን በማቅረብ፥ ሁሉም የአከባቢው ማህበረሰብ በቤት ውስጥ፣ በትምህርት ቤት ወይም በስራ ቦታ እራሳቸው ሚስዮናውያን በመሆን የቤተክርስቲያኒቷን ጥረት እንዲደግፉ አሳስበዋል።
እርስ በርሳቸው በመዋደድ የግልና የቤተሰብ የጎሳ ፉክክርና መለያየትን ማሸነፍ እንዲችሉ ብሎም ፍርሃትን፣ አጉል እምነትንና አስማትን ከሰዎች ልብ ውስጥ በማባረር እንደ ሁከት እና ታማኝነት የጎደለው ድርጊት፣ብዝበዛ፣ አልኮል እና አደንዛዥ እፅ የመሳሰሉ አጥፊ ባህሪያትን ማስቆም እንደሚችሉ መክረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ካቶሊካዊያን ምዕመናንን ካነጋገሩ በኋላ የአርጀንቲና ሚሲዮናውያን እና ገዳማዊያት እህቶች ቡድንን ለማግኘት በአቅራቢያው ወደሚገኘው ባሮ መንደር አጭር ጉብኝት አድርገዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ወደ ስፍራው መጥተው እንዲጎበኙ የጋበዟቸው ከሚስዮናውያን አንዱ የሆኑት በፓፑዋ ኒው ጊኒ ለአሥር ዓመታት ያገለገሉት የቀድሞ ጓደኛቸው አባ ማርቲን ፕራዶ እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል።
ሚስዮናውያኑ ብጹእነታቸው ረጅም ጉዞ አድርገው ሊጎበኟቸው በመምጣታቸው እጅግ ተደስተው የነበረ ሲሆን፥ “ታላቅ ልብ ያላቸው ሰው” በማለትም ጠርተዋቸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከዚህ አስደሳች ቆይታ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ በአውሮፕላን በመሳፈር ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ ከማጠናቀቃቸው በፊት ሰኞ ዕለት ከወጣቶች ጋር ወደሚገናኙበት
ወደ ፖርት ሞርስቢ ተመልሰዋል።
ብጹእ አባታችን የ45ኛው የውጪ ሃገራት ሐዋርያዊ ጉዞዋቸው ሦስተኛዋ ሃገር ወደ ሆነችው ወደ ቲሞር-ሌስቴ ጳጉሜ 4 አመሻሽ ላይ እንደሚጓዙ ይጠበቃል።