ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከፓፑዋ ኒው ጊኒ ጄኔራል ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከፓፑዋ ኒው ጊኒ ጄኔራል ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከፓፑዋ ኒው ጊኒ ርዕሠ መስተዳድር ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል

የፓፑዋ ኒው ጊኒ ርዕሠ መስተዳድር ጄኔራል ፍራንሲስ ቦፌንግ ዳዳ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በቤተ መንግሥት በክብር ተቀብለው ምስጋናን አቅርበውላቸዋል። ጄኔራሉ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለሰላም፣ ለፍትህ፣ ለሰብዓዊ መብቶች እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እርምጃ ለመውሰድ የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፖርት ሞርስቢ በሚገኝ አፔክ ሃውስ ከሲቪል ባለስልጣናት ጋር ለመገናኘት ከማቅናታቸው በፊት የፓፑዋ ኒው ጊኒ ርዕሠ መስተዳድር ጄኔራል ቦብ ቦፌንግ ዳዳን በዋና ከተማዋ በሚገኘው ቤተ መንግሥት ጎብኝተዋል።

ርዕሠ መስተዳድሩ በፓፑዋ ኒው ጊኒ መንግሥት እና ሕዝብ ስም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በደስታ ተቀብለው የሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ጠቀሜታ በማጉላት “የእንኳን ደህና መጡ!” ንግግር አድርገዋል።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ እምነቱን ይዛ የገባችው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ እንደሆነ በማስታወስ፥ በትምህርት፣ በጤና እና በመንፈሳዊ እንክብካቤ ውስጥ ያላትን ወሳኝ ሚና እና የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶችን ተራርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ለማዳረስ እያደረገች ያለውን ጥረት እንደሚገነዘቡት ገልጸዋል።

ቤተ ክርስቲያን ለሰብዓዊ መብቶች በመቆም ለአየር ንብረት ለውጥ የምትወስደው እርምጃ
ርዕሠ መስተዳድሩ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሰላም፣ ለፍትህ፣ ለሰው ልጅ ክብር እና ለጾታ እኩልነት የምታደርገውን ድጋፍ አስታውሰው፥ የአየር ንብረት ለውጥ በፓፑዋ ኒው ጊኒ ተራርቀው በሚገኙ ደሴቶች ላይ ለሚያሳድረው ከፍተኛ ተጽዕኖ ዓለም አቀፍ እርምጃ እንዲወሰድ የምታሰማውን ጥሪ አወድሰዋል።

በተጨማሪም መንግሥት ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን አጋርነት በተለይም የገንዘብ ድጋፍ በመስጠት እና የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቀጣሪዎችን ከመንግሥት የደመወዝ ክፍያ ሥርዓት ጋር በማዋሃድ በፓፑዋ ኒው ጊኒ ውስጥ ያለውን የቤተ ክርስቲያን እና የመንግሥት ትብብር ጥልቅ ቁርጠኝነት መኖሩን የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

ርዕሠ መስተዳድሩ በንግግራቸው ማጠቃለያ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት በፓፑዋ ኒው ጊኒ ሕዝብ ላይ ዘላቂ የሆነ መንፈሳዊ ተጽእኖ እንደሚፈጥር በመግለጽ፥ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት እና ሕዝቦች ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን ለማሸነፍ እምነታቸውን ያጠናክሩ ዘንድ ቅዱስነታቸው እንዲጸልዩላቸው ጠይቀዋል።

 

07 September 2024, 12:42