ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጃካርታ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራንን አመሰገኑ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“እጅ ለእጅ ተያይዘው የመጓዝ ፍላጎት፣ የቋንቋ ልዩነት የሚፈጥረውን መሰናክሎች የማፍረስ ጥያቄ፣ ለተፈጥሮ እና ለተናቁት ሰዎች የሚገለጽ መቆርቆር ከድሆች፣ ከአቅመ ደካሞች፣ ከተገለሉት እና ከአካል ጉዳተኞች ጋር ለመገናኘት የሚያስችሉ መንገዶችን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት አካል ነው” በማለት ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮኮስ ይህን የተናገሩት ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 29/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ውስጥ ከጳጳሳት፣ ካህናት፣ ከገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ ከዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና ከትምኅርተ ክርስቶስ መምህራን ጋር ባደረጉት ስብሰባ ወቅት የቀረቡ ምስክርነቶችን ካዳመጡ በኋላ ነው።
ሩቅ ብንገኝም ቅርብ ነን!
የኢንዶኔዥያ የሀገረ ስብከት ካህናት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አባ ማክሲ ኡን ብሪያ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ባሰሙት ንግግር፥ “በኢንዶኔዥያ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ቤተ ክርስቲያናት እና ምእመናን በአንድነት በማገልገል እጅ ለእጅ ተያይዘው በኅብረት ለመጓዝ በሚሞክሩ የሀገረ ስብከት ካኅናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማዊያት መካከል የር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መገኘት በረከት ነው” በማለት ገልጸዋል።
በዚህች የብዝሃነት አገር ኢንዶኔዥያ ውስጥ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምዕምናንን እና የሀገር የጋራ ጥቅምን ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት በመግለጽ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የቀድሞው ርዕሣነ ጳጳሳት ላሳዩት አባታዊ እንክብካቤ አድናቆታቸውን ገልጸው፥ “ይህም በሩቅ ለምንገኝ ለእኛ የቅዱስ ጴጥሮስን ቅርበት የሚያመላክት” ነው ብለዋል።
በበለጠ አንድነት ከኩላዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር መስማማት
እህት ሪና ሮዛሊና በኢንዶኔዥያ ውስጥ የሚገኙ የገዳማውያን እና ገዳማዊያት ሰላምታን ለቅዱስነታቸው ካቀረቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ “ኢንዶኔዥያ ሰፊ ሀገር ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን እና በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በመደገፍ በሥራችን ኅብረት እና አንድነት እንዳለን ይሰማናል” ብለዋል።
“ሁልጊዜ ከእናንተ ለመማር እንሞክራለን” ያሉት እህት ሮዛሊና፥ ነገር ግን በርቀት እና በቋንቋ ችግር አንዳንድ ጊዜ ከሮም የሚወጡትን ሠነዶች ለማግኘት እንደሚቸገሩ እና ጥረቶች ቢደረጉም የትርጉም ሥራው ብዙ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ገልጸዋል።
የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን የቤተ ክርስቲያን ጥንካሬ ናቸው!
በጃካርታ የቅዱስ ኡርሱላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት እና በንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ቁምስና የትምህርተ ክርስቶስ መምህርት አኜስ ናታሊያ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእውነት የአሲሲውን ቅዱስ ፍራንችስኮስን እንደሚወክሉ ተናግራ፥ አንዳንድ የቅዱስነታቸውን አስተምህሮ በመጥቀስ “ስለ ተፈጥሮ ጥበቃ እና ለዝቅተኞች፣ ለድሆች፣ ለአቅመ ደካሞች፣ ለተገለሉት እና ለአካል ጉዳተኞች በጣም ይጨነቃሉ” ስትል ተናግራለች።
ኢየሱስን ለሌሎች ለማሳየት የውይይት ድልድዮች መሆን
በቦጎር በሚገኘው የሰላም ንግሥት ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሃይማኖት መምህር እና የሀገረ ስብከቱ የትምህርተ ክርስቶስ ኮሚሽን አባል አቶ ኒኮላስ ዊጃያ “በዚህች በብዝሃነት በለጸገች በኢንዶኔዥያ ውስጥ በሚሠሩ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን መካከል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መገኘት እጅግ አበረታች እንደሆነ ተናግረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው ቃለ ምዕዳናቸው የተናገሩትን ያስታወሱት መምህሩ፥ “ድልድይ” የሚለውን ቃል በማኅበረሰቡ ውስጥ ካለች ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን ተመሳሳይነት በማሳየት፥ ቅዱስነታቸው ለሁሉም የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን እንዲጸልዩ እና ብዙ ሰዎችን አንድ የሚያደርጋቸው ድልድይ እንዲሆኑ ጠይቀዋል። የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ኢየሱስ ክርስቶስን በእምነት፣ በወንድማማችነት እና በርኅራኄ ለሌሎች በማቅረብ የውይይት ድልድዮች ለመሆን እንዲያነሳሱ ጠይቀዋል።