ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የፓፑዋ ኒው ጊኒ ወጣቶች ከመከፋፈል ይልቅ ስምምነትን እንዲመርጡ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓፑዋ ኒው ጊኒ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ከአገሪቱ ወጣቶች ጋር በፖርት ሞርስቢ ሲር ጆን ጊስ ስታዲዬም ተገናኝተዋል። ቅዱስነታቸው በዝግጅቱ ላይ ለወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት፥ የፓፑዋ ኒው ጊኒ ወጣቶች ከመከፋፈል ይልቅ ስምምነትን እንዲመርጡ በማሳሰብ የፍቅር እና የአገልግሎት ቋንቋን እንዲለማመዱ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጹሑፍ ያዘጋጁትን ንግግር ወደ ጎን በመተው በፖርት ሞርስቢ በሚገኘው በሲር ጆን ጊስ ስታዲዬም ከተሰበሰቡት ወደ 10,000 ከሚገመቱ ወጣቶች ጋር ፊት ለፊት የተወያዩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከ800 የሚበልጡ ቋንቋዎች በሚነገሩባት በፓፑዋ ኒው ጊኒ የሚኖሩት ወጣቶች የፍቅርን እና የአገልግሎትን የጋራ ቋንቋን እንዲጋሩ አሳስበዋል።

ወጣቶችን የሚያጋጥሙ ልዩ ልዩ ችግሮች
የባሕል አልባሳትን የለበሱ ወጣቶች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያደረጉትን ደማቅ አቀባበል ተከትሎ የከምቤ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆን ቦስኮ አውራም ለቅዱስነታቸው ሰላምታን ካቀረቡላቸው በኋላ በፓፑዋ ኒው ጊኒ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን ከሚያጋጥሟቸው ዋና ዋና ተግዳሮቶች መካከል በቤተሰባቸው እና በኅብረተሰቡ ውስጥ ክርስቲያናዊ እሴቶችን በተግባር መኖር፣ ውስን የዕድገት ዕድሎች እና ከኅብረተሰቡ፣ ከመንግሥት እና ከቤተ ክርስቲያን የሚጠበቁ ድጋፎች ሲጎድሉባቸው የሚሰማቸው ብስጭቶች እንደ ሆኑ አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆን ቦስኮ አውራም ለቅዱስነታቸው ንግግር ሲያደርጉ
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆን ቦስኮ አውራም ለቅዱስነታቸው ንግግር ሲያደርጉ

በዝግጅቱ መካከል የቀረቡ ሦስት ምስክርነቶች
አንዳንድ ወጣቶች ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምስክርነትን ያቀረቡ ሲሆን፥ የመጀመሪያዋ ምስክርነት ሰጭ የካቶሊክ ባለሙያዎች ማኅበር አባል ፓትሪሲያ ሃሪክነን-ኮርፖክ፣ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ፣ ማኅበራዊ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ የካቶሊክ እምነት እና ሥነ-ምግባርን በማኅበረሰቡ ውስጥ ለመመስከር ከፍተኛ ተጽዕኖ ማድረጉን ተናግራለች።

ራያን ቩሉም የተባለ ወጣት በበኩሉ ወላጆቹ በተለያዩበት አስቸጋሪ የልጅነት ጊዜ ቤተ ክርስቲያን መሸሸጊያው እንደሆነችለት በማስረዳት በፓፑዋ ኒው ጊኒ ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ወጣቶች ከተፋቱ ወይም ሕይወት ከሌሉ ወላጆች ጋር መገናኘት ስለሚከብዳቸው ተመሳሳይ ፈተናዎች እንደሚያጋጥማቸው አስረድቶ ይህም ብዙውን ጊዜ አደገኛ የዕፅ ሱሰኝነት፣ በሕገ-ወጥ ድርጊቶች ተሳታፊ በማድረግ ተስፋ ወደ መቁረጥ እንደሚያደርሳቸው ገልጿል።

የመጨረሻውን ምስክርነት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅበር አባል ቤርናዴት ቱርሞኒ፥ ቤተሰብ በወጣቶች ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት አስከፊ ተጽእኖ እንደሚያስከትል ተናግራ፥ ተጠቂዎች እንደተጠሉ ስለሚሰማቸው እና ይህም እራሳቸውን እንዲያጠፉ ወይም ቤተሰቦቻቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ያደርጋቸዋል ብላለች። ፓፑዋ ኒው ጊኒ በተፈጥሮ ሃብት የበለፀገች አገር ቢትሆንም ድህነት ብዙ ወጣቶችን ትምህርታቸውን አቋርጠው ዕፅ አዘዋዋሪዎች እንዲሆኑ፣ ወደ ስርቆት ወይም ወደ ልመና እንደሚገቡ ያደርጋቸዋል ስትል ቤርናዴት አክላለች።

ቤርናዴት ቱርሞኒ፥ ለቅዱስነታቸው ሰላምታ ስታቀርብ
ቤርናዴት ቱርሞኒ፥ ለቅዱስነታቸው ሰላምታ ስታቀርብ

የወደፊት ሕይወትን በተስፋ እና በፈገግታ መጋፈጥ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በበኩላቸው ውቅያኖሶች፣ ተራራዎች እና ሞቃታማ ደኖች ባሉባት ፓፑዋ ኒው ጊኒ ውስጥ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፥ ፓፑዋ ኒው ጊኒ በወጣቶች የተሞላች ወጣት ሀገር መሆኗን እና ወጣቶችም የወደፊት ሕይወታቸውን በተስፋ እና በፈገግታ እንዲጋፈጡ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሁለት የፓፑዋኒው ጊኒ ወጣቶች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሁለት የፓፑዋኒው ጊኒ ወጣቶች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ
ቅዱስነታቸው በፓፑዋ ኒው ጊኒ ከወጣቶች ጋር የነበራቸውን ጊዜ የሚያሳይ ሙሉ የቪዲዮ ቅንብር
09 September 2024, 16:58