ፈልግ

ለር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የክብር አቀባበል ሲደረግላቸው  ለር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የክብር አቀባበል ሲደረግላቸው   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ጀመሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሐሙስ መስከረም 16 እስከ እሑድ መስከረም 19/2017 ዓ. ም. ድረስ በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም የሚያደርጉትን 46ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለመጀመር ወደ ሉክሰምበርግ ደርሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም የሰዓት አቆጣጠር ሐሙስ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከሃያ ዘጠኝ ደቂቃ ላይ ከሮም ፊውሚሲኖ አየር ማረፊያ የተነሱት ቅዱስነታቸው ወደ ሉክሰምበርግ አየር ማረፊያ የደረሱ በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከሃምሳ ስድስት ደቂቃ እንደ ነበር ታውቋል።

ቅዱስነታቸው በቫቲካን ከሚገኘው የቅድስት ማርታ የጳጳሳት መኖሪያ ቤት ከመነሳታቸው በፊት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዙሪያ ከሚያድሩ ወደ አሥር ከሚጠጉ ችግረኞች ጋር ተገናኝተው እንደነበር ታውቋል።

ችግረኞቹን ወደ ቅዱስነታቸው ዘንድ ይዘው የሄዱት በሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት የምጽዋዕት ሰብሳቢ ክፍል እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራየስኪ እንደ ነበሩ የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል አስታውቋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ  ወደ ሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም  ጉዞ ሲጀምሩ
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም ጉዞ ሲጀምሩ

ቅዱስነታቸው ለጣሊያኑ ፕሬዝዳንት መልዕክት ልከዋል
ቅዱስነታቸው በጣሊያን የአየር ክልል ውስጥ በነበሩበት ወቅት ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት አቶ ሴርጆ ማታሬላ የቴሌግራም መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፥ ለመላው የጣሊያን ሕዝብ መልካምን እና ብልጽግና በጸሎት በመመኘት፥ በሉክሰምበርግ እና በቤልጂየም ለሚገኙ ሕዝቦች የሰላም እና የተስፋ መልዕክት በማምጣት ሊያገኟቸው እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

የጣሊያኑ ፕሬዝዳንት የአቶ ሴርጆ ማታሬላ ምላሽ
ለቅዱስነታቸው ምላሽ በሰጡት የቴሌግራም መልዕክት በተለያዩ አኅጉራት የተከሰቱት ጦርነቶች እና ግጭቶች ሞትን እና ስቃይን በማስከተል ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የፍራንችስኮስ ወደ አውሮፓ እምብርት የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ቅድስት መንበር በዓለም ላይ አንድነት፣ ፍትህ እና ዕርቅ እንዲሰፍን የምታደርገውን ያላሰለሰ ጥረት በድጋሚ ይመሰክራል” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ጉዞ ላይ እያሉ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ
ቅዱስነታቸው ጉዞ ላይ እያሉ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ

 

26 September 2024, 12:17