ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “እውነተኛ ትልቅነት የሚገኘው በተለይ አቅመ ደካሞችን በመንከባከብ ነው!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ መስከረም 12/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን በዕለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አሰምተዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ለምዕመናኑ ባሰሙት ስብከት፥ “እውነተኛ የበላይነት ሊገኝ የሚችለው አቅመ ደካሞችን በመንከባከብ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል። ክቡራት እና ክቡራን አንባቢዎቻችን የቅዱስነታቸውን ስብከት ሙሉ ትርጉም ከዚህ ቀጥሎ እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! በዛሬው መስዋዕተ ቅዳሴያችን ከማር. 9: 30-37 ተወስዶ የተበበው የወንጌል ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወቱ ፍጻሜ የሚሆነውን ነገር የተናገረውን ይመለከታል። 'የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጣል፤ ይገድሉትማል፤ በሦስተኛው ቀን ይነሳል' (ማር.9:31) በማለት ኢየሱስ ተናገረ። ደቀ መዛሙርቱ መምህራቸው የሆነው ኢየሱስን እየተከተሉ ሳለ በአእምሮአቸው እና በከንፈራቸው ሌሎች ነገሮችን ያስቡ እና ይናገሩ ነበር። ኢየሱስ ስለ ምን እያወሩ እንዳሉ ሲጠይቃቸው አልመለሱለትም።

ለዚህ የደቀ መዛሙርት ዝምታ ትኩረት እንስጥ። ደቀ መዛሙርቱ ዝም ያሉበት ምክንያቱም ማን ታላቅ እንደሆነ በመወያየት ላይ ስለ ነበሩ ነው (ማር. 9:34)። ከኀፍረትም የተነሣ ነበር። ይህም ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ጋር ምን ያህል ልዩነት እንዳለ ያስገነዝባል። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ራሱ ሕይወት ትርጉም ሲነግራቸው ሳለ እነርሱ ግን ስለ ስልጣን ይናገሩ ነበር። ቀደም ሲል ኩራት ልባቸውን እንደዘጋባቸው ሁሉ አሁን ደግሞ እፍረት አፋቸውን ዘጋ። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ በጉዞ ላይ እያሉ ለተናገሯቸው ንግግሮች እንዲህ ሲል በግልፅ ምላሽ ሰጥቷል፥ “መጀመሪያ ለመሆን የሚፈልግ ከሁሉ መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ይሁን” (ማር. 9:35)። ከሁሉ በላይ መሆን ትፈልጋለህ? ታዲያ ራስህን ዝቅ አድርገህ የሁሉ አገልጋይ ሁን።

ወሳኝ በሆነ ቀላል አነጋገር ኢየሱስ ክርስቶስ አኗኗራችንን ያድሳል። እውነተኛ የበላይ መሆን የሚቻለው በጠንካራ ወይም በኃይል አገዛዝ ሳይሆን ነገር ግን ደካማ የሆኑትን በመንከባከብ እና በማገልገል እንደሆነ ኢየሱስ ያስተምረናል። እውነተኛ የበላይነት ማግኘት የሚቻለው እጅግ የደከሙትን እና አቅም ደካሞችን በመንከባከብ እና በማገዝ ነው። ይህ የሰዎች ሁሉ የበላይ የሚያደርገው ይህ ነው!

መምህሩ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕፃንን ጠርቶ በደቀ መዛሙርቱ መካከል ያስቀመጠው እና ያቀፈው ለዚህ ነው። እንዲህም አለ፥ 'ከእነዚህ ሕጻናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል' (ማር. 9:37)። ሕጻን አቅም ወይም ጉልበት የለውም፡ የሌሎችን ድጋፍ እና እገዛ ይፈልጋል። ሰውን ስንንከባከብ ሁል ጊዜ በሕይወት ለመኖር እንደሚፈልግ እንገነዘባለን።

እኛ ሁላችን በሕይወት የምንገኘው ከሌሎች ድጋፍ እና ዕርዳታ ስለተደረገልን ነው። ነገር ግን አለን ብለን የምንመካበት ኃይል ይህን እውነት እንድንረሳ ያደርገናል። እኛ ዛሬ በሕይወት የምንኖረው ሌሎች ሰዎች ባደረጉልን ድጋፍ ነው። በዚህ ጊዜ ኃይለኞች እንባላለን እንጂ አገልጋዮች አይደለንም። በመሆኑም በመጀመሪያ መከራን የሚቀበሉት እነዚያ ኋለኞች፣ ዝቅተኞች፣ ደካሞች እና ድሆች ናቸው።

ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! ስንት ሰዎች፣ ስንቶች በስልጣን ሽኩቻ ይሰቃያሉ ይሞታሉ! የእነርሱ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን፣ በማኅበረሰቡ የተገለሉትን እና የሚሞቱት ሰዎች ዓለም ነው። ኢየሱስ ክርስቶ በሰዎች ተላልፎ ሲሰጥ የተቀበለው መስቀልን እንጂ አጋርነትን አልነበረም። ነገር ግን የወንጌሉ ቃል በሕይወት የሚኖር እና በተስፋ የተሞላ ነው። በሰዎች የተካደው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ተነስቷል። እርሱ ጌታ ነው!

በዚህች ውብ ሰንበት እራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን። በእነዚህ በዝቅተኞች መካከል የኢየሱስ ክርስቶስን ፊት እንዴት ማወቅ እችላለሁ? በልግስና በማገልገል ጎረቤቴን እከባከባለሁ? የሚንከባከቡኝንስ አመሰግናለሁ?

ከከንቱ ውዳሴዎች ተለይተን እንደ እርሷ ለአገልግሎት ዝግጁዎች እንድንሆን በኅብረት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ እንጸልይ።"
 

23 September 2024, 17:18