ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ ልጆች ራስን ዝቅ የማድረግ አስፈላጊነት ያሳዩናል አሉ

በቲሞር-ሌስቴ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የፈጸሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የባህር ዳርቻ ከተማ በሆነች ታሲ ቶሉ ላይ እጅግ በርካታ ምዕመናን የተካፈሉትን መስዋዕተ ቅዳሴን አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለምዕመናኑ ባሰሙት ስብከት፥ ሕፃናት በረከትም ምልክትም ናቸው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ማክሰኞ ጳጉሜ 5/2016 ዓ. ም. በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ወደ 600,000 የሚገመቱ ምዕመናን መሳተፋቸውን እና ይህም ከጠቅላላው የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር ግማሽ ያህሉ እንደሆነ የአካባቢው ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው ለምዕመናኑ ሰላምታ ሲያቀርቡ
ቅዱስነታቸው ለምዕመናኑ ሰላምታ ሲያቀርቡ

“ሕጻን ተወልዶልናል!”
በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ በተነበበው የመጀመሪያ ንባብ፥ “ሕፃን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና” በሚለው በነብዩ ኢሳይያስ ትንቢት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያሰሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እነዚህ ቃላት ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች የተነገሩ መሆናቸውን አስታውሰው፥ ለዚያች ከተማ ሕዝብ ፍሬያማ እና መልካም ጊዜ ቢሆንም ነገር ግን ታላቅ የሞራል ውድቀት የደረሰበት ወቅት እንደነበርም ተናግረዋል። ከተማዋ ከፍተኛ ሃብት ቢኖራትም ድሆች የተናቁበት፣ የተራቡበት፣ ታማኝነት የጎደለበት እና እንዲሁም ሃይማኖታዊ ልማዶችም ወደ መደበኛ ሥርዓትነት የተቀየሩበት ጊዜ እንደነበር አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው እንዳሉት፥ በዚህ ምክንያት ነቢዩ ኢሳይያስ በእግዚአብሔር የተከፈተውን አዲስ አድማስ ለሕዝቡ ለማወጅ መምጣቱን ገልጸው፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን ያዳናቸው በሠራዊት ኃይል፣ በጦር መሣሪያ እና በሃብት ብዛት ሳይሆን ይልቁንም በሕጻን ልጅ ስጦታ እንደሆነ አስረድተዋል።

በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥር ዓት ከተገኙት ምዕመናን መካከል
በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥር ዓት ከተገኙት ምዕመናን መካከል

ልጆች በረከት እና ምልክት ናቸው!
ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በመቀጠል፥ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሕፃን መወለድ የደስታ እና የበዓል ጊዜ እንደሆነ እና ይህም በጎ ወደ ሆነው፣ ወደ ንጽህና እና ወደ ትህትና መመለስን ያመልክታል ካሉ በኋላ፥ በቲሞር-ሌስቴ ውስጥ ብዙ ልጆች መኖራቸውን በማድነቅ፥ አገሪቱ ወጣት ትውልድ ያለባት እና የምድሯም ማዕዘናት በሕይወት መሞላታቸውን ማየት እንችላለን ብለዋል።

“ይህ ታላቅ ስጦታ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ለሕፃናት ቦታ የማዘጋጀት፣ እነርሱን የመቀበል እና የመንከባከብ አስፈላጊነት የሚያሳስብ ምልክት በመሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

መስዋዕተ ቅዳሴው የቀረበበት መንበረ ታቦት
መስዋዕተ ቅዳሴው የቀረበበት መንበረ ታቦት

ራስን ዝቅ ማድረግ
ራስን ዝቅ የማድረግን አስፈላጊነት በተመለከተ የልጅ መወለድ ትምህርት ሊሆነን ይችላል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “በእግዚአብሔር እና በሰው ፊት ራስን ዝቅ ማድረግ ሊያስፈራን እንደማይገባ ተናግረው፥ የወንድሞቻችን እና የእህቶቻችን ሕይወት እንዲሻሻል እና ደስተኞችም እንዲሆኑ ለማድረግ ጊዜን ሰጥተን፣ መስዋዕትነት ከፍለን እቅዶቻችንን ማስተካከል ይገባል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም ዕቅዶቻችንን ማስተካከል ማለት ለዕቅዶቻችን ዝቅተኛ ግምት መስጠት ማለት ሳይሆን ራሳችንን በስጦታነት አቅርበን ሌሎችን በመቀበል የበለጠ ጥሩ እንዲሆኑ ማድረግ በመሆኑ ልንፈራ አይገባም ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንሲስ ከቅዳሴ በኋላ ለም ዕመናኑ ሰላምታ ሲያቀርቡ
ር. ሊ. ጳ. ፍራንሲስ ከቅዳሴ በኋላ ለም ዕመናኑ ሰላምታ ሲያቀርቡ

የልጅ ፈገግታ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴው ፍጻሜ ላይ ሕፃናትን የመንከባከብ አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው ባደረጉት አጭር ንግግር፥ በአገሪቱ ውስጥ በቆዩባቸው ጥቂት ቀናት ውስጥ የተገነዘቡት እና እጅግጥሩ ነገር የቲሞር-ሌስቴ ልጆች የሚያሳዩት ፈገግታ እንደሆነ ተናግረው፥ ልጆችን ፈገግታ የምታስተምር ከተማ የተሻለ የወደፊት ዕድል ያላት ከተማ” እንደምትሆን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ለነበሩት በርካታ ምዕመናን ባሰሙት የማስጠንቀቂያ ምክር፥ “ባሕላችሁን እና ታሪካችሁን ለመለወጥ ከሚፈልጉ አዞዎች ራሳችሁን ጠብቁ” ሲሉ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም የቲሞር-ሌስቴ ሕዝብ ብዙ ልጆችን እንደሚወልዱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ልጆቻቸውን ሲንከባከቡ ነገር ግን የአገሪቱ መታሰቢያ የሆኑትን አረጋውያንን እንዲንከባከቡ አደራ ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ለመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ወደ ዲሊ ሲደርሱ

 

11 September 2024, 16:53