ፈልግ

በሲንጋፖር ብሔራዊ ስታዲዬም የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት በሲንጋፖር ብሔራዊ ስታዲዬም የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የወንጌል ማዕከል ፍቅር እንደሆነ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሲንጋፖር በማድረግ ላይ ባሉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፥ በከተማዋ ውስጥ በሚገኝ ብሔራዊ ስታዲዬም መስዋዕተ ቅዳሴን መርተዋል። ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ባሰሙት ስብከት፥ ፍቅር የማንነታችን እና የአገልግሎታችን መሠረት እንደሆነ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሲንጋፖር ውበት እና ታላቅ የኪነ-ህንጻ ሥራ ከተማዋን ታዋቂ አድርጓታል በማለት ስብከታቸውን የጀመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው የመጀመሪያ መልዕክቱ ምዕ. 8:1 ላይ ዕውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል” ያለውን አስታውሰዋል። 

ፍቅር የታላቅ ሥራዎች መሠረት ነው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ሰዎች ለሚያከናውኑት ታላቅ ሥራ መሠረቱ ገንዘብ፣ የምህንድስና ስልቶች ወይም ችሎታዎች ሳይሆን ነገር ግን ዋናው ፍቅር ነው” ሲሊ አስገንዝበዋል። አንዳንድ ሰዎች ታላላቅ ሥራቸውን በፈጠራ እና በጥበብ ተነሳስተው ቢሠሩትም በፍቅር ካልሆነ ለሥራቸው ተነሳሽነት፣ ምክንያት እና ጥንካሬ የለውም ሲሉ አስረድተዋል።

የማፍቀር ችሎታ መሠረቱ እግዚአብሔር ነው

“ይህ በእምነት የተረጋገጠ እና የበራ እምነታችን፥ የማፍቀር አቅማችን መሠረቱ እግዚአብሔር እንደሆነ ያስተምረናል” ብለዋል። “እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን በነፃ እና በፍቅር ፈጥሮናል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በአንድ ልጁ ሞትና ትንሳኤ ከኃጢአት እና ከሞት ነፃ የሚያወጣን የእግዚአብሔር ፍቅር እንደሆነ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእርሳቸው በፊት የነበሩትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን በመጥቀስ፣ “በራሳችን ፍቅር የእግዚአብሔርን ፍቅር ነጸብራቅ እናያለን፥ ይህ ፍቅር የዘር፣ የእምነት ወይም ሌላ ምንም ዓይነት ልዩነት ሳያደርግ ለሁሉም ሰዎች ያለንን ጥልቅ አክብሮት ይገለጻል” ብለዋል።

የእግዚአብሔርን ፍቅር ለሌሎች ማካፈል

“እነዚህ ለእኛ ጠቃሚ ቃላቶች ናቸው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በሰዎች ሥራ ከመገረም ባሻገር፣ በበለጠ አድናቆት እና ክብር ልንቀበለው የሚገባን አስደናቂ ነገር፥ በየዕለቱ የምናገኛቸው ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ናቸው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስብከታቸውን በመቀጠል፥ ያለንን ከሌሎች ጋር እንድንካፈል፣ የድሆችን ፍላጎት በልግስና እንድንመልስ፣ የሚሠቃዩትን እንድናበረታታ እና ሁልጊዜም ይቅር ባይ ለመሆን እና ተስፋ ለማድረግ ዝግጁ እንድንሆን የሚጋብዘን የእግዚአብሔር ፍቅር ነው ብለዋል። ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን እንደገና በመጥቀስ “ፍቅር የወንጌል ማዕከል ነው” ብለዋል።

የቅዱሳን ምሳሌ

የዚህ ፍቅር ምሳሌ የሆኑትን ሁለቱን ቅዱሳን፥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እና የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዛቪየርን ምሳሌ በመጥቀስ ስብከታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ የእመቤታችን ማርያም ቅዱስ ስም በማይተወን እናታዊ ርህራሄ እና ከሁሉ በሚያምር የአብ ፍቅር ሲገለጥ እናያለን” ብለው፥ በሲንጋፖር ውስጥ መልካም አቀባበል የተደረገለት የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዛቪየር የሚስዮናዊነት ጉዞ በጎን ከማድረግ የተገኘ መሆኑን እናያለን ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምእመናን የእነርሱን አርአያነት እንዲከተሉ እና የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዛቪየርን ቃል በመድገም፥ “በእነዚህ ቀናት ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜም ከእኛ ጋር አብረውን እንዲሄዱ፣ ወሰን ከሌለው የእግዚአብሔር ፍቅር የሚመጡ ዛሬም ወደ እኛ የሚመጡትን የፍቅር እና የፍትህ ጥሪዎችን ለማዳመጥ እና ምላሽ ለመስጠት የማያቋርጥ ቁርጠኝነት እንዲኖረኝ “ጌታ ሆይ! እነሆኝ፤ ምን እንዳደርግ ትፈልጋለህ?” ብለው እንዲጠይቁ አደራ ብለዋል።

በሲንጋፖር ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት
12 September 2024, 16:56