ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ስለ ብዝሃነት እና አንድነት ከኢንዶኔዥያ ወጣቶች ጋር ተወያዩ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ 45ኛውን የውጪ ሃገራት ሐዋሪያዊ ጉዟቸውን ሲጀምሩ ይህ ከስኮላስ ኦከረንቴስ የወጣቶች ቡድን ጋር የሚያደርጉት ቆይታ በጉጉት የሚጠበቅ የነበረ ሲሆን፥ ይህም ስብሰባ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የውጭ ጉብኝቶች መደበኛ ባህሪ እንደሆነ እና ሁልጊዜ ለቅዱስ አባታችን ልብ እና ለጵጵስናቸው በጣም አስፈላጊ የሆኑትን አንዳንድ ጭብጦች እንደሚዳሰሱበት፥ ከዚህም ባለፈ እነዚህ መሪ ቃሎች ከኢንዶኔዥያ ሕዝብ መለያ ከሆነው “በብዝሃነት ውስጥ አንድነት” ከሚለው የህይወት አተያያቸው ጋር አብረው እንደሚሄዱ ተገልጿል።
ስኮላስ እ.አ.አ. በ2013 ዓ.ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የተመሰረተ እና ለወጣቶች የሕግ፣ የሥነ ጥበብ እና የስፖርት ትምህርት የሚሰጥ ለትርፍ ያልተቋቋመ ዓለም አቀፍ ጳጳሳዊ ድርጅት ነው።
ከተለያዩ ደሴቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና ኃይማኖቶች የመጡት እነዚህ 200 የሚሆኑት የኢንዶኔዥያው የስኮላስ ቅርንጫፍ ወጣቶች ብጹእነታቸውን ጃካርታ በሚገኘው “ግሬሃ ፔሙዳ” ተብሎ በሚጠራው የወጣቶች መኖሪያ ቤት ውስጥ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፥ ይህም ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እና ለኢንዶኔዥያ ህዝብ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ብዝሃነት እና አንድነትን በትክክል ያሳየ ነው ተብሏል።
'ፖሊሄድሮን'
ስብሰባው በተካሄደበት ክፍል ውስጥ በወጣቶቹ የተሰራው የፖሊሄድሮን ወይም በሶስት ማዕዘን ቅርጽ የተገነባው ቤት በጉልህ ይታይ እንደነበር እና በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ያለምንም ችግር ወደ ውስጥ ለመግባት ችለዋል። ቅርጹ ከ1500 በላይ በሚሆኑ ከጃካርታ፣ ከሎምቦክ፣ ከበላቡአን ባዮ እና ከባሊ በመጡ ወጣቶች የተሰራ ሲሆን፥ በፖሊ-ሄድሮኑ ውስጥ የነበሩ ሁለት ወጣት ሴቶች ምስክርነታቸውን ከማካፈላቸው በፊት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ሰላምታ ሰጥተዋቸዋል።
የመጀመሪያዋ ሴት ተማሪ በትምህርት ዓለም ውስጥ በነበረችበት ወቅት፣ በከተማዋ ውስጥ የትምህርት ዕድል እንድታገኝ የዳረጋትን እና በጣም ስለምትወደው የህይወት ተመክሮ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ያካፈለች ሲሆን፥ ስኮላስ በሕይወቷ ውስጥ ያለውን ጠቀሜታ ከመናገሯ በፊት እንደ አስተማሪ እና እንደ አማካሪ ስላሏት ሃላፊነት ገልፃ “በስኮላ የተማርኩትን ሁሉ በምሰራበት ቦታ በተማሪዎቼ እና በስራ ባልደረቦቼ ላይ ተግባራዊ አደርጋለሁ” ስትል ገልፃለች። “ስኮላስ ውስጥ የሰለጠንኩበት መንገድ፣ ከተለያዩ አከባቢ ከመጡ ሰልጣኞች ጋር የነበረኝ ቆይታ እና የተስተናገድኩበት መንገድ ለሁሉም ተማሪዎች የሚያስፈልግ ባህል ነው” ብላለች።
የብሪያን ምስክርነት
ብሪያን የተባለው ሌላኛው ተማሪ በሰጠው ምስክርነት ስለ አንድነት የሚገልጸውን የሃገሪቷን መሪ ሃሳብ በድጋሚ በማስታወስ፥ “ምንም እንኳን የተለያየን ብንሆንም አንድ ነን” በማለት ገልጿል። በቦታው የሚገኙ እንግዶች በሃገሪቷ ውስጥ ያሉትን በጎ ልምዶችን እንዲመለከቱ እና እያንዳንዱ ሰው ከሌላው ጋር ተስማምቶ የሚኖርበትን ልምድ እንዲካፈሉ በመጠየቅ፥ ሆኖም ግን “አሁን ላይ የሆነ ነገር እንደጎደለ” ችላ ማለት አይቻልም ብሏል።
ብሪያን ስለ አድልዎ እና የሳይበር ጥቃት እውነታዎች በመጥቀስ፥ በስኮላስ ውስጥ እያንዳንዱ ሰው ስለ ጥሩም ሆነ መጥፎ የህይወት ልምዱን ማካፈል የሚችሉበት መድረክ እንደሚሰጣቸው ተናግሯል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አራት አብሮ የመኖር እና የሰላም መርሆዎች የሆኑትን ማለትም፥ እውነታዎች ከሀሳብ እንደሚሻሉ፣ አንድነት ከግጭት እንደሚሻል፣ አጠቃላይ ሁኔታው ከቁንጽል ሃሳብ እንደሚሻል እንዲሁም አጠቃላይ ሁኔታ ከአንድ ሀሳብ እንደሚሻል በማስታወስ ለብሪያን ምላሽ ሰጥተዋል።
የክርስቲን ምስክርነት
ከሁለቱ ወጣቶች በተጨማሪ ክርስቲ የምትባል አንዲት ወጣት የሳይበር ጥቃት የደደረሰባትን አጋጣሚ በማስታወስ ምስክርነቷን ያጋራች ሲሆን፥ ያለምንም ምክንያት እንደተገለለች እና ለብቸኝነት ተዳርጋ እንደነበር ለብጹእነታቸው ከገለጸች በኋላ ይህ በዓለም ዙሪያ ባሉ በበርካታ ወጣቶች ላይ እንደሚደርስ በማስታወስ ጉዳዩ እንደሚያሳስባት ተናግራለች።
ነገር ግን ትላለች ክርስቲን፣ በስኮላስ በኩል ብዙውን ጊዜ ይከፋፍሉናል ብለን ያልናቸው ልዩነቶች አንድ ሊያደርጉን እንደሚችሉ ሰዎች በቀላሉ ሊማሩ እንደሚችሉ በመጥቀስ፥ በተቋሙ ውስጥ “ልዩነቶቻችንን አንድ ማድረግ፣ የአንድነት ትስስርን መገንባት እንድንችል እና ልዩነቶች ወደ አንድነት የሚያመጡ እንጂ ወደ ጥፋት መንገድ የሚወስዱ አለመሆናቸውን ለመረዳት ችለናል” ብላለች።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በመጨረሻም ለክርስቲ ሲመልሱ “ሁላችንም አንድ ዓይነት ከሆንን አሰልቺ እንደሚሆን” ከገለጹላት በኋላ፥ ልዩነት ወደ ጦርነት ወይም ወደ ውይይት ሊመራን ይችላል፥ እኛ ግን አንዱን መምረጥ አለብን፥ ጦርነት ሁልጊዜ ሽንፈት ነው፥ ነገር ግን ከወዳጅ ጋር መወያየት በጣም ቆንጆ ነገር ነው፣ ይሄ መንገድ ብቻ ነው ሊያሳድገን የሚችለው” በማለት መክረዋታል።