ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ሲደርሱ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ሲደርሱ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለሐዋርያዊ ጉብኝት ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ደረሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከኢንዶኔዥያው የሦስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት በኋላ የጉብኝታቸው ሁለተኛ አገር ወደ ሆነች ፓፑዋ ኒው ጊኒ ደርሰዋል። ከጃካርታ ሶኬርኖ-ሃታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዓርብ ጳጉሜ 1/2016 ዓ. ም. ጠዋት የተነሱት ቅዱስነታቸው ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ፖርት ሞርስቢ የደረሱ ማምሻውን ሲሆን፥ በዚህች አገር የሦስት ቀናት ጉብኝት እንደሚያደርጉ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ፓፑዋ ኒው ጊኒ ከቫቲካን 19,047 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን፥ ይህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ለመሆን ባላቸው ምኞት እስካሁን ካደረጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች መካከል ከፍተኛ ርቀት ያለው እና አስፈላጊነቱም ከፍተኛ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ተብሏል።

በርቀት፣ በኤኮኖሚ እና በተፈጥሮአዊ አቀማመጥ ከሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ጋር ያልተገናኙ ጎሳዎች መኖሪያ በሆነችው ፓፑዋ ኒው ጊኒ ውስጥ የመሬት መንቀጥቀጥ እና መንሸራተት የተለመዱ ናቸው። በጣም ተራርቀው በሚገኙ አካባቢዎች የመሠረተ ልማት እጥረት በመኖሩ በነፍስ አድን ዕርዳታ እና የሕክምና አቅርቦት ላይ ከባድ ፈተና ከመፍጠሩ ጋር ለአገር ጎብኚዎችም እንቅፋት ሆኗል።

ነገር ግን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህ ተግዳሮቶች ሳያግዷቸው በሰሜን ምዕራብ የባሕር ዳርቻ በምትገኘው የቫኒሞ ከተማ ውስጥ የሚገኙትን ጨምሮ የአርጀንቲና ሚስዮናውያን በሚገኙባት እና 2.5 ሚሊዮን ካቶሊካዊ ምዕመናን በሚኖሩባት ፓፑዋ ኒው ጊኒ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ቆርጠዋል።

እንደ አከባቢው ጎረቤት አገሮች በመልክዓ-ምድር አቀማመጥ በምሥራቅ ፓሲፊክ ውቅያኖስ በምትገኝ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ ተጨባጭ ተፅእኖዎችን ማስከተሉ ጨምሯል።

ፓፑዋ ኒው ጊኒ የዘላቂ ልማትን ሞዴል ለመከተል እና ደካማ ሥነ-ምህዳሮቿን እና ሕዝቦችዋን ከአደጋ ለመታደግ በምትጥርበት በዚህ ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የድሆችን እና የምድርን ጩኸት ለመስማት ያቀረቡት ጥሪ በኃይል ማስተጋባቱ አይቀርም።

ስለዚህ ለምዕመናን የሚደረገ ሐዋርያዊ አገልግሎት፣ ለፍጥረት የሚደረግ እንክብካቤ እና የአገሬው ነባር ተወላጅ ጥበብን እና ባሕልን የመንከባከብ እና የመጠበቅ ጥሪ ቅዱስነታቸው በሀገሪቱ በሚያደርጉት የሦስት ቀናት ቆይታ ትኩረት የሰጥባቸው ጉዳዮች ናቸው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሌሎች ምን ዓይነት ጉዳዮችን ማጉላት እንደሚገባ በትክክል የሚያውቁ፣ እንደ ኩላዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ እና እንደ ዘመናችን የማያሻማ የሞራል የበላይነት ስልጣን ያላቸው ድንቅ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ናቸው።

በእርግጠኝነት የእርሳቸው ፍላጎት ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሰው ልጅ እና ለፓፑዋ ኒው ጊኒ ሕዝቦች የተስፋ እና የማበረታቻ መልዕክት ይሆናል።

 

07 September 2024, 10:10