ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በእስያ እና በኦሼኒያ የሚያደርጉትን ጉብኝት ለመጀመር ወደ ጃካርታ ደረሱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ወደ ኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ ሶካርኖ-ሃታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጥቂት ደቂቃዎችን አስቀድሞ በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ከረፋዱ አምስት ሰዓት ከአሥራ ዘጠኝ ደቂቃ ላይ የደረሰው የጣሊያን አየር መንገዱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን እና ጋዜጠኞችን ይዞ ከሮም ፊዩሚቺኖ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተነሳው ሰኞ ከቀትር በኋላ በ6:32 እንደ ነበር ይታወሳል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ጃካርታ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፥ እንደ መርሃ-ግብሩ መሠረት ቅዱስነታቸው ማክሰኞን ያለ ምንም ስብሰባ ካሳለፉት በኋላ የ 12 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት በሚጀምሩበት ዕሮብ በዋና ከተማው ውስጥ ጉብኝቶችን ለማድረግ በርካታ ቀጠሮዎችን መያዛቸው ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእስያ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ከመቀጠላቸው በፊት በጃካርታ ሦስት ቀናትን የሚያሳልፉ ሲሆን፥ ረጅሙ የተባለውን ይህን ጉብኝታቸውን በሌሎች አገራትም ማለትም በፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ በቲሞር ሌስቴ እና በሲንጋፖር እንደሚያደርጉ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእነዚህ ጉብኝቶች ወቅትም በየአገራቱ ብፁዓ ካርዲናሎች ደማቅ አቀባበል የሚደረግላቸው ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል ሦስቱ የካርዲናልነት ማዕረግ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተቀበሉ መሆናቸው ታውቋል።
የእስያን አኅጉር በአጭሩ ስንቃኝ
የእስያ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን (ኤፍኤቢሲ) ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ማውንግ ቦ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት፥ አንዳንድ ጊዜ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በእስያ ውስጥ ለሚገኙ ምእመናን ሩቅ እንደሆኑ ስለሚሰማቸው ወደ እነርሱ መምጣት ብዙ ዋጋ የሚሰጠው መሆኑን አስረድተዋል።
እስያውያን የተለያዩ የፖለቲካ ጭቆና፣ ድህነት እና የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች እንዲሁም የሃይማኖት ስደት ወይም የእምነት ነፃነት እጦት እንደሚደርስባቸው በቁጭት ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት ወደ ሌሎች አገራት የሚሰደዱ መኖራቸውን እና በሄዱበትም እምነታቸውን ጠብቀው እንደሚቀጥሉ ተናግረው፥ ይህንንም ሲያደርጉ ‘ሚስዮናውያን’ ሆነው በመገኘት ለአዲሱ የመኖሪያ አካባቢያቸው አዲስ ተስፋ እና ቅንዓት እንደሚያመጡ ተናግረዋል።
ኢንዶኔዥያ
ኢንዶኔዢያ በዓለማችን ውስጥ አብላጫ ቁጥር ያለው የሙስሊም ሕዝብ የሚገኝባት አገር ነች። ወደ 17,000 የሚጠጉ ብዙ ደሴቶችን፣ ጎሳዎችን፣ ቋንቋዎችን እና ባሕሎችን ያቀፈች አገር ነች። ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀደም ብለው የነበሩ ሁለት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት አገሪቱን ጎብኝተው እንደ ነበር ሲታወስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1970 ዓ. ም. እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በ1989 ዓ. ም. መጎብኘታቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከወረርሽኙ በፊት በደቡብ ምሥራቅ እስያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ አቅደው እንደ ነበር ይታወሳል።
ኢንዶኔዢያ የመቻቻል እና አብሮ የመኖር ተምሳሌት ተደርጋ በሰፊው የምትታይ አገር በመሆኗ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በማለት የጻፉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው በሰው ልጆች መካከል ወንድማማችነትን እና በሃይማኖቶች መካከልም የጋራ ውይይቶችን ማስፋፋት እንደሚቀጥል ተስፋ ተጥሎበታል። 280 ሚልዮን ሙስሊም ማኅበረሰብ ባላት ኢንዶኔዥያ ውስጥ የካቶሊክ ምዕምናን ቁጥር ሦስት በመቶ ወይም 8 ሚሊዮን ቢሆኑም በሰው ልጅ የግል ክብር እና በተለያዩ ሃይማኖታዊ እምነቶች ላይ የተገነቡ መሆናቸው ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጃካርታ ውስጥ በሚያደርጉት የሦስት ቀናት ቆይታ በኢስቲቅላል መስጊድ ውስጥ የተዘጋጀውን የሃይማኖት መሪዎችች ስብሰባ ከተካፈሉ በኋላ ከአገሪቱ ካቶሊክ ምዕምናን ጋር በመሆን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያቀርቡ ታውቋል።
የጃካርታ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ኢግኔሽየስ ሱሃርዮ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ እንደ ካቶሊኮች እና ሙስሊሞች ያሉ የተለያየ እምነት ያላቸው ሰዎች በመካከላቸው ጋብቻን መፈጸም የተለመደ እንደሆነ እና ይህ በሌሎች ሙስሊም አገራት ውስጥ የተለመደ አለመሆኑን ገልጸው ብዙን ካቶሊክ ካኅናት ከሙስሊም ወይም ቡዲስት ወላጅ ቤተሰቦች እንደሚመጡም ገልጸው፥ “በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “እምነት፣ ወንድማማችነት እና ርኅራሄ” የሚለውን መሪ ቃል በመያዝ ወደ ኢንዶኔዥያ መምጣታቸው ተገቢ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ፓፑዋ ኒው ጊኒ
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1984 ዓ. ም. ፓፑዋ ኒው ጊኒ ጎብኝተው እንደ ነበር ሲታወስ፥ ከ40 ዓመታት በኋላ ዛሬ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የእርሳቸውን ፈለግ በመከተል በፓፑዋ ኒው ጊኒ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ መምጣታቸው ታውቋል። ፓፑዋ ኒው ጊኒ በአብላጫው የክርስቲያን ሀገር ስትሆን ከሦስት ግለሰቦች መካከል አንዱ ካቶሊክ እንደሆነ ታውቋል።
ቅዱስነታቸው ወደ 2 ሚሊዮን ከሚጠጉ ካቶሊኮች ጋር ያላቸውን ቅርርብ በተጨባጭ ከማሳየታቸው በተጨማሪ በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በአብዛኛው በአየር ንብረት ቀውስ እና በድህነት ለሚሰቃይ የፓፑዋ ኒው ጊኒ ሕዝብ ያላቸውን ቅርበት በመገንዘብ የፓሲፊክ ደሴት የሆነች ይህች አገር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጋቢት 25/2024 ዓ. ም. ከደረሰባት ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ በኋላ ዕርዳታ ለማድረግ በርካታ ጥሪዎችን ማቅረባቸው ይታወሳል።
በአገሪቱ ዋና ከተማ ፖርት ሞርስቢ ውስጥ የተዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት መስዋዕተ ቅዳሴን ጨምሮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቤተ ክርስቲያን የዕርዳታ አገልግሎቶችን የሚያገኙ የጎዳና ሕጻናትን ከጎበኟቸው በኋላ በካሪታስ ቴክኒካል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በሚያደርጉት ስብሰባ እንደሚጠቃል ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየአገራቱ በሚያደርጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች በሙሉ በዋና ከተማዎቹ የሚቆዩ ቢሆንም ነገር ግን በፓፑዋ ኒው ጊኒ በሚያደርጉት ቆይታ ወደ ቫኒሞ የባሕር ዳርቻ ከተማ በመሄድ በዚያም ከሚሲዮናውያን እና ከአካባቢው ምእመናን ጋር በግል ለመገናኘት ወስነዋል።
ቲሞር ሌስቴ
ከፓፑዋ ኒው ጊኒ ቀጥሎ ያለው የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት በእስያ አኅጉር ካቶሊካዊት አገር ወደ ሆነች ወደ ቲሞር ሌስቴ እንደሚሆን ታውቋል። በዚህች ቀድሞ የፖርቹጋል ቅኝ ግዛት በነበረች አገር ውስጥ ከ96 በመቶ በላይ የሚሆነው የካቶሊክ እምነት ተከታይ ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1989 ዓ. ም. ኢስት ቲሞር በኢንዶኔዥያ ሥር በነበረበችበት ወቅት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጎብኝተዋት እንደ ነበር ይታወሳል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “እምነት ባህልህ ይሁን” በሚል መሪ ቃል በሚጎበኟት ቲሞር ሌስቴ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ካሳረጉ በኋላ አካል ጉዳተኛ ህጻናትን ጎኝተው ከኢየሱሳውያን ማኅበር ካኅናት ጋርም እንደሚገናኑ ታውቋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በነሐሴ ወር 2022 ዓ. ም. ለመጀመሪያ ጊዜ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካርዲናልነት ማዕረግ የተቀበሉት የዲሊው ብፁዕ ካርዲናል ቪርጂሊዮ ዶ ካርሞ ዳ ሲልቫ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፥ ትኩረት ልንሰጣቸው ከሚገባቸው አስቸኳይ ጉዳዮች መካከል አንዱ አገራቸውን ለቀው የሚሰደዱ ወጣቶች ጉዳይ እንደሆነ ገልጸው፥ በድህነት እና በሥራ አጥነት ምክንያት ትውልድ አገራቸውን ለቀው ለወጡት እንዴት ዕርዳታ መስጠት እንደሚቻል ቤተ ክርስቲያናቸው እያጠናች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
ስንጋፖር
በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉባት አገር በተለምዶ እንደ ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል ተደርጋ የምትታይ የሲንጋፖር ደሴት እንደሆነ ታውቋል። የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1986 ዓ. ም ያደረጉትን የሐዋርያዊ ጉብኝት ፈለግ በመከተል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሲንጋፖርን ይጎበኟታል።
ከሲንጋፖር ሕዝብ መካከል ስድስት በመቶ የሚሆነው ካቶሊክ ምዕመናን እንደሆኑና በቁጥርም ወደ 395 ሺህ እንደሚሆኑ ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በነሐሴ 27/2022 ዓ. ም. የሲንጋፖር የመጀመሪያ ካርዲናል ሆነው የተሾሙት ብጹዕ ካርዲናል ዊልያም ጎህ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንዳስረዱት፣ በአገሪቱ የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የበለጠ ጠንክራ ብትሆን ኖሮ ምዕምናን ራሳቸውን መርዳት እንደሚችሉ፣ ከድህነት ለመውጣት ወንዶችን ወደ ሥራ የሚስብ ዝንባሌ ባለመኖሩ በአካባቢው ካለው ሰፊ ሃብት አንፃር ብዙ የሙያ ዘርፎች አለመኖራቸውን አስረድተዋል።
ምእመናኑ ከቁምስናቸው በተለይም በመንፈሳዊ አስተምህሮ ከሚቀርቡት እገዛዎች እና ጥራት ያለው የትምህርት ዕድል አንጻር ወደ ላቀ ደርጃ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሲንጋፖር በሚኖራቸው ቆይታ በካቶሊክ መካከለኛ ኮሌጅ ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር በሃይማኖቶች መካከል ባለው ግንኝነት ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ እና የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያሳርጉ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ-ግብር ያመለክታል።