ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ጉዞ ሲጀምሩ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ጉዞ ሲጀምሩ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የኢንዶኔዥያ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ተሰናብተዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዶኔዥያ ያደረጉትን የሦስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው የጉብኝታቸው ሁለተኛ አገር ወደ ሆነች ፓፑዋ ኒው ጊኒ ተጉዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው እንደ አገሩ የሰዓት አቆጣጠር ዓርብ ጳጉሜ 1/2016 ዓ. ም. ጠዋት በጃካርታ የቅድስት መንበር እንደራሴ መኖሪያ ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ካሳረጉ በኋላ ከጃካርታ ሶኬርኖ-ሃታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመነሳት ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ፖርት ሞርስቢ በረራ አድርገዋል።

በጃካርታ ሶኬርኖ-ሃታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያው ለተገኙት የኢንዶኔዥያ የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስትር፣ የሲቪል እና የሃይማኖት ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የጃካርታ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ኢግናስዮስ ሱሃርዮን ጨምሮ እሳቸውን ለማግኝት በሥፍራው ለተገኙት የአየር ማረፊያው ሠራተኞች እና የበረራው አስተባባሪ ሠራተኞችን አመስግነዋል።

ወደ ፓፑዋ ኒው ጊኒ የተደረገ ጉዞ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ 4700 ኪሎ ሜትር ከሚጠጋ የስድስት ሰዓት በረራ በኋላ ወደ ፖርት ሞርስቢ የደረሱት እንደ አገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ዓርብ ምሽት እንደሆነ ታውቋል።

የቅዱስነታቸው የፓፑዋ ኒው ጊኒ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚጀምረው ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2016 ዓ. ም. ጠዋት ሲሆን፥ ከጠቅላይ ገዥው ጋር በቤተ መንግሥት ውስጥ ከተገናኙ በኋላ ከባለስልጣናት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲ አካላት ጋር ተገናኝተው ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ቀጥለውም በካሪታስ የዕርዳታ ድርጅት በሚመራ የሞያ ማሰልጠኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ከጎዳና ላይ የተሰበሰቡ አዳጊዎችን ከጎበኟቸው በኋላ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ከፓፑዋ ኒው ጊኒ እና ከሰሎሞን ደሴቶች ከመጡት ካቶሊክ ብጹዓን ከጳጳሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን ጋር በቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቲያኖች ረድኤት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገናኝተው ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

እሑድ ጳጉሜ 3/2016 ዓ. ም. ጠዋት በፖርት ሞርስቢ ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ከተገናኙ በኋላ በጆን ጊዝ ስታዲዬም የሚቀርበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚመሩ ታውቋል።

ቀጥለውም ከእንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በረራ በኋላ ወደ ቫኒሞ ደርሰው ከሰዓት በኋላ ከሀገረ ስብከቱ ካቶሊክ ምዕመናን ጋር በቅዱስ መስቀል ካቴድራል ውስጥ ተገናኝተው ንግግር ካደረጉ በኋላ በቅዱስ ሥላሴ ትምህርት ቤት ውስጥ ከልዩ ልዩ ሚሲዮናውያን ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ እና በተመሳሳይ ዕለት ወደ ፖርት ሞርስቢ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ እንደሚመለሱ ተገልጿል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓፑዋ ኒው ጊኒ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያጠቃልሉት ሰኞ ጳጉሜ 4/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በዲሊ ጆን ጊስ ስታዲዬም ለወጣቶች በሚያስተላልፉት መልዕክት ሲሆን፥ በተመሳሳይ ዕለትም የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሦስተኛ አገር ወደ ሆነችው ቲሞር ሌስቴ እንደሚጓዙ የጉብኝታቸው መርሃ-ግብር ያመለክታል።

 

06 September 2024, 12:32