ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ኢንዶኔዥያ የሚያደርጉትን ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ኢንዶኔዥያ የሚያደርጉትን ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ 45ኛ የውጭ አገር ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ጀምረዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሰኞ ነሐሴ 27/2016 እስከ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. ድረስ በኢንዶኔዥያ፣ በፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ በቲሞር-ሌስቴ እና በሲንጋፖር ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ሰኞ ማታ ከሮም ፊውሚሲኖ አውሮፕላን ማረፊያ በመነሳት ጉዞ ጀምረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በእስያ እና በኦሼንያ የሚያደርጉትን 45ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለመጀመር ከሮም ፊውሚቺኖ አውሮፕላን ማረፊያ ማታ በ12:32 መንሳታቸው ታውቋል። በእስያ እና በኦሼኒያ አኅጉራት ውስጥ በሚገኙት አራት አገራት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚያደርጉት የ12 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት እስካሁን ካደረጓቸው ጉብኝቶች ረጅሙ ይሆናል ተብሏል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቅድስት ማርታ የጳጳሳት መኖሪያቸው ከመነሳታቸው በፊት በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የበጎ አድራጎት መምሪያ ከሚረዱ አሥራ አምስት ቤት የሌላቸው ሰዎች ጋር የተገናኙ ሲሆን፥ ብፁዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራጄቭስኪ እንግዶችን ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመምራት አብረዋቸው አጭር ጎብኝት ማድረጋቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በእስያ እና በኦሼኒያ አኅጉራት ለማድረግ ከመጓዛቸው በፊት፥ በሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራጄቭስኪ ሰኞ ከሰዓት በኋላ አሥራ አምስት ቤት የሌላቸውን ወንዶችን እና ሴቶችን ከቅዱነታቸው ጋር ማገናኘታቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህን ተረጂዎች በአባታዊ ምክራቸው ካበረታቷቸው በኋላ ወደ ፊውሚቺኖ አውሮፕላን ጣቢያ በመሄድ ጉዞ መጀመራቸውን መግለጫው አክሎ አስታውቋል። ቅዱስነታቸው ከአውሮፕላን ማረፊያው ከመነሳታቸው ቀደም ብለው ለጣሊያኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሴርጆ ማታሬላ የቴሌግራም መልዕክት መላካቸው ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ለጣሊያኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሴርጆ ማታሬላ በላኩት መልዕክት፥ “በእምነት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ከሆኑት ጋር ለመገናኘት ባለኝ ፍላጎት እና በሰብዓዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች በበለጸጉት፣ በፈተና ጊዜያት እንኳን አብሮነትን፣ ኅብረትን እና የጋራ ውይይቶችን በመሰከሩ አገራት፥ በኢንዶኔዥያ፣ በፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ በቲሞር ሌስቴ እና በሲንጋፖር ሐዋርያዊ ጉብኝቴን ለማካሄድ እሄዳለሁ። ክቡር ፕሬዝዳንት ለእርስዎ እና ለተወደደው የጣሊያን ሕዝብ ከተስፋ ሰላምን እና ብልጽግና ጋር ያለኝን መልካም ምኞት ልገልጽላችሁ እወዳለሁ።” ብለዋል።  

 

 

03 September 2024, 10:01