ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለሐዋርያዊ ጉብኝት ወደ ሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም መጓዛቸው ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው ከሐዋርያዊ ጉብኝት ረዳቶች እና በርካታ ጋዜጠኞች ጋር ወደ ሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም ለመጓዝ ከሮም ፊውሚሲኖ አየር ማረፊያ የተነሱት በአገሩ የሰዓት አቆጣጠር ሐሙስ ጠዋት ሁለት ሰ ዓት ከሃያ ዘጠኝ ደቂቃ ላይ እንደነበር ታውቋል።
ቅዱስነታቸው በቫቲካን ከሚገኘው የቅድስት ማርታ የጳጳሳት መኖሪያ ቤት ከመነሳታቸው በፊት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዙሪያ ከሚያድሩ ወደ አሥር ከሚጠጉ መጠለያ ከሌላቸው ጋር ተገናኝተዋል።
ችግረኞቹን ወደ ቅዱስነታቸው ዘንድ ይዘው የሄዱት በሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት የምጽዋዕት ሰብሳቢ ክፍል እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጎ አድራጎት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራየስኪ እንደ ነበሩ የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል አስታውቋል።
ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በመጀመሪያ ተረጂዎቹን ወደ ቅዱስነታቸው ያመጧቸው ለጠዋት ቁርስ ቢሆንም ነገር ግን በኋላ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ወደተደረገ የግል ስብሰባ መቀየሩ እንግዶችን እንዳስገረማቸው ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመንበረ ጴጥሮስ ሐዋርያዊ አገልግሎት መጀመሪያ ጀምሮ የሚያደርጉትን ትውፊት በመቀጠል በየአገራቱ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለመጀመር ከቫቲካን ሲነሱ “ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወክሉ ድሆች ሰላምታ መስጠት ይፈልጋሉ” ሲሉ ብፁዕ ካርዲናል ክራየስኪ ጨምረው ገልጸዋል።
ቅዱስ አባታችን ወደ ሉክሰምበርግ አየር ማረፊያ የሚደርሱት በአገሩ የሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ እንደሚሆን እና ወደ አገሪቱ ሲደርሱ በቅድሚያ ከሉክሰምበርግ ንጉሣውያን ቤተሰብ ጋር፣ ከአውሮፓ አገራት ርዕሠ መስተዳድር እና ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሉክ ፍሬደን ጋር በግል ከተገናኙ በኋላ ለሲቪል ባለስልጣናት እና ለዲፕሎማሲ አካላት ንግግር እንደሚያደርጉ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሰዓት በኋላ ወደ ቤልጂየም ዋና ከተማ ብራስልስ ከማቅናታቸው በፊት ከሉክሰምበርግ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ጋር በኖትር ዳም ካቴድራል እንደሚገናኙ የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል አስታውቋል።