ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሃይማኖቶች ውይይት የእርስ በርስ መከባበርን እንደሚያበረታታ ገለጹ

በእስያ አኅጉር ሐዋርያዊ ጉብኝት በማካሄድ ላይ የሚገኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ ውስጥ ከአገሪቱ ሲቪል ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። “በብዝሃነት መካከል ያለ አንድነት” የሚለውን መሪ ቃል በመደገፍ ኢንዶኔዥያን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት ቅዱስነታቸው፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖቶች መካከል ውይይት እንዲካሄድ፣ በሕዝቦች መካከልም ስምምነት እንዲኖር የምትችለውን ሁሉ እንደምታደርግ ቃል ገብተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ነሐሴ 29/2016 ዓ. ም. በኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ በሚገኘው ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት ውስጥ ለሀገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ለሕዝብ ተወካዮች እና ዲፕሎማሲያዊ አካላት ንግግር አድርገዋል።

ቅዱስነታቸው ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲደርሱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ የቫቲካን እና የኢንዶኔዢያ ባንዲራዎችን ከሚያውለበልቡ ሕጻናት እና በርካታ የክብር ዘብ ጋር ሆነው አቀባበል አድርገውላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቀረበላቸው የክብር መዝገብ ላይ በጣሊያንኛ ቋንቋ በጻፉት መልዕክት፥ “የተለያዩ ባሕሎች እና ሃይማኖቶች እርስ በእርስ በሚገናኙባት እና በሚወያዩባት በዚህች ውብ ምድር ውስጥ ሆኜ የኢንዶኔዥያ ሕዝብ በእምነት፣ በወንድማማችነት እና በርህራሄ እንዲያድግ እመኛለሁ!” ካሉ በኋላ “እግዚአብሔር ኢንዶኔዢያ ይባርክ!” በማለት ፊርማቸውን አኑረዋል።

ቅዱስነታቸው በክብር መዝገብ ላይ ፊርማቸውን ሲያኖሩ
ቅዱስነታቸው በክብር መዝገብ ላይ ፊርማቸውን ሲያኖሩ

በብዝሃነት መካከል የሚገኝ አንድነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአገሪቱ ባለሥልጣናት ባደረጉት ንግግር ስለተደረገላቸው አቀባበል ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ “ውቅያኖስ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢንዶኔዥያ ደሴቶችን አንድ እንደሚያደርጋቸው ሁሉ የሀገሪቱ በርካታ ጎሳዎች እና ሃይማኖቶች አንድ ሊሆኑ የሚችሉበትን መንገድ ጠቁመዋል። ‘በብዝሃነት መካከል የሚገኝ አንድነት’ የሚለው ብሔራዊ መፈክር በአንድ ሀገር ውስጥ ጠንካራ አንድነት ያላቸውን የልዩ ልዩ ሕዝቦች ዘርፈ ብዙ እውነታን በጥሩ መልኩ ይገልጸዋል” ብለዋል።

በሕዝቦች መካከል የሚታይ መግባባት
ሁሉም ሰው የሁሉንም በጎ በመፈለግ የወንድማማችነትን መንፈስ መቀበል እንደሚፈልግ ቅዱስነታቸው ተናግረው፥ “ይህ ጥበባዊ ሚዛን በብዙ ባሕሎች እና ርዕዮተ ዓለም ዕይታዎች መካከል አንድነትን የሚያጠናክሩ አስተሳሰቦች እንዳይቋረጡ መከላከል አለበት” ብለዋል። እንዲህ ዓይነቱ የጥበብ ሥራ ኢንዶኔዥያውያንን ሁሉ በማካተት ለስምምነት፣ ለፍትሃዊነት፣ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ለዘላቂ ልማት እና ለሰላም እንዲጥሩ የሚያደርግ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

የጋራ ጥቅምን ለማስፋፋት ቤተ ክርስቲያን የምታደርጋቸው ጥረቶች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖቶች መካከል ውይይቶችን በማስፋፋት፣ ሰላማዊ እና ፍሬያማ የሆነ ስምምነትን በማጠናከር ተሳትፎ እንደምታደርግ ቃል ገብተው፥ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት ጭፍን ጥላቻን በማስወገድ የመከባበር እና የመተማመን መንፈስን ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል።

“ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጋራ ጥቅምን በመደገፍ እና ከሕዝብ ተቋማት እና ከሌሎች የሲቪል ማኅበረሰብ ተዋናዮች ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር፣ ይበልጥ ሚዛናዊ የሆነ ማኅበራዊ ትስስር ለመፍጠር፣ የበለጠ ቀልጣፋ እና ፍትሃዊ ማኅበራዊ ድጋፍ ለሁሉ እንዲዳረስ ትፈልጋለች” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ፕሬዚደንት ዊዶዶ በፕሬዚዳንት ቤተ መንግሥት ውስጥ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ፕሬዚደንት ዊዶዶ በፕሬዚዳንት ቤተ መንግሥት ውስጥ

የጋራ መከባበር እና ፍትህ
ቅዱስነታቸው በመቀጠልም ኢንዶኔዥያ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1945 ዓ. ም. ያጸደቀችው ሕገ መንግሥት በመግቢያው፥ “ሁሉን ቻይ አምላክ” እና “ማኅበራዊ ፍትህ” የሚሉት በጥቂት መስመሮች ውስጥ ደጋግሞ ማመልከቱን ጠቁመው፥ “በብዝሃነት ውስጥ ያለው አንድነትን፣ ማኅበራዊ ፍትህን፣ መለኮታዊ በረከትን እና ማኅበራዊ ሥርዓትን ለማነሳሳት እና ለመምራት የታቀዱ መሠረታዊ መርሆች ናቸው” ብለዋል። “እነዚህ መርሆዎች ቤትን ለመገንባት የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ካለው የድጋፍ መዋቅር ጋር ሊመሰሉ ይችላሉ” ብለዋል።

የመንግሥት ባለስልጣናት አንድ ዓይነት አቋም ብቻ ሲይዙ በአገሮች ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት ሊነሳ እንደሚችል የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የኢንዶኔዥያን መንግሥት የሚመራው ፍልስፍና ሚዛናዊ እና ጥበብ የተመላበት ነው” ስሉ ተናግረዋል።

ር. ሊ. ጳ ጳሳት የኢንዶኔዥያ ባለሥልጣናት በብዝሃነት ውስጥ ስምምነትን እንዲያሳድጉ አሳሰቡ

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1989 ዓ. ም. ጃካርታን በጎበኙበት ወቅት፥ የኢንዶኔዢያ ባለሥልጣናት የሁሉም ዜጎች ሰብዓዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወት እንዲያከብሩ፣ በመቻቻል እና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት” በማለት ማሳሰባቸውን አስታውሰው፥ “ሰላም የፍትህ እና የእያንዳንዱ ሰው ሥራ ውጤት ነው” ሲሉ አክለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “መግባባት የሚገኘው ለራሳችን ፍላጎት እና ራዕይ ብቻ ስንሠራ ሳይሆን ነገር ግን ለጋራ ጥቅም፣ እርስ በርስ የምንገናኝባቸውን መንገዶች ስንገነባ፣ ስምምነቶችን እና ውህደቶችን ስናዳብር፣ ሁሉንም ዓይነት ሞራላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግሮችን በማሸነፍ ሰላምን እና ስምምነትን ለማስፋፋት ስንተጋ ነው” በማለት በኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ በሚገኘው ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት ለሀገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ለሕዝብ ተወካዮች እና ለዲፕሎማሲ አካላት ያደረጉትን ንግግር ደምድመዋል።

የቫቲካን እና የኢንዶኔዢያ ባንዲራዎችን የሚያውለበልቡ ሕጻናት ለቅዱስነታቸው አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የቫቲካን እና የኢንዶኔዢያ ባንዲራዎችን የሚያውለበልቡ ሕጻናት ለቅዱስነታቸው አቀባበል አድርገውላቸዋል።

 

04 September 2024, 10:35