ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኢንዶኔዥያ ከኢየሱሳውያን ጋር የወንድማማችነት ውይይት አካሄዱ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእስያ አኅጉር የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በመቀጠል በኢንዶኔዥያ ከሚገኙት የኢየሱስ ማኅበር አባላት ጋር ዕሮብ ነሐሴ 29/2016 ዓ. ም. ተገናኝተው ተወያይተዋል። ቅዱስነታቸው ከኢየሱሳውያን ማኅበር ካኅናት ጋር የተገናኙት ከኢንዶኔዥያ ባለስልጣናት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲያዊ አካላት ጋር በፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት ከተሰበሰቡ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።
ጃካርታ ውስጥ በሚገኝ የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከተገኙት የቀድሞው የጃካርታ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ጁሊየስ ሪያዲ ዳርማትማጃ ይገኙበታል። እንደወትሮው ሁሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከኢየሱሳውያን ጋር ለአንድ ሰዓት ያህል በግል ከተወያዩ በኋላ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።
በማኅበርተኞች መካከል የተደረገ የወንድማማችነት ጉብኝት
በቅድስት መንበር የባሕል እና የትምህርት ጉዳዮችን የሚከታተል ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ጸሐፊ አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ ከቅዱስነታቸው ጋር የነበራቸው ጊዜ አስደሳች እንደነበር ገልጸው፥ “ቅዱስነታቸው እንደ ሁልጊዜው መረጋጋት እና ቤተኛነት ይሰማቸዋል” በማለት የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጀመሪያ ቀናት አቋማቸውን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ተናግረው፥ ከኢንዶኔዥያ ኢየሱሳውያን ወንድሞቻቸው ጋር በተገኛኙ ጊዜ በርካታ ወጣት ኢየሱሳውያንን በማየታቸው መደነቃቸውን እና መደሰታቸውን ገልጸው፥ የኢየሱሳውያን ማኅበር በኢንዶኔዥያ ወጣት ኢየሱሳውያንን ለክኅነት በማዘጋጀት ማኅበሩ ገና ወጣት እንደሆነ አስተውለዋል ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ኢየሱሳውያን ማኅበር ሲናገሩ፥ ማስተዋል እና ጸሎት ለማኅበሩ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል። ከቅዱስነታቸው ጋር ከተገናኙት ወጣት ኢየሱሳውያን መካከል በዕድሜ ትንሹ የሆነው፥ የሚጸልይበት ጊዜ የት እንደሚያገኝ በማለት ላቀረበላቸው ጥያቄ ጥቂት ታሪኮችን በመጥቀስ፥ የጥያቄው ርዕሠ ጉዳይ በኢንዶኔዥያ ውስጥ ካሉ ሌሎች አስፈላጊ ርዕሠ ጉዳዮች ጋር የተገናኘ መሆኑን እና ይህም በሃይማኖቶች መካከል ውይይት ማድረግ እና የክርስቲያን ትምህርቶች እና ልምዶች ከባህሎች ጋር መላመድን እንደሚገባ አጥብቀው መናገራቸውን አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ ተናግረዋል።
“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አናሳ የምዕመና ቁጥር የሚገኝባቸውን አብያተ ክርስቲያናት እንደሚወዱ የገለጹት አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ፥ በ280 ሚሊዮን ከሚቆጠር ከጠቅላላው የኢንዶኔዥያ ሕዝብ 3% ወይም 8 ሚሊዮን ካቶሊክ ምዕመናን እንደሚገኙ እና በሀገሪቱ ውስጥ ጎልተው እንደሚታዩ አስረድተዋል። የክርስቲያን ዓላማ ለአገር ዕድገት አስተዋፅኦ ማድረግ፣ እርሾ መሆን እና ይህም ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስፈላጊ መሆኑን አባ ስፓዳሮ አስረድተው፥ ለክርስቲያኖች በተላለፈው በዚህ መልዕክት መሠረት ከብዛት ይልቅ ለጋራ ጥቅም ሙሉ በሙሉ መተባበር፣ ሕያውነት እና ከጊዜ ወደ ጊዜ የማደግ አቅም ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስፈላጊ መሆኑን አክለው ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቲሞር-ሌስቴ እና በሲንጋፖር ውስጥ ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ስብሰባዎችን ከኢየሱሳውያን ካኅናት ጋር ለማድረግ ቀጠሮ መያዛቸው የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ-ግብር ያመለክታል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ያላቸውን ዕይታ አድንቀው፥ በኢንዶኔዥያ ምድር ሊኖር የሚችለውን ዕድል፣ በብዝሃነት አውድ ውስጥ የመግባባት ዕድል እንዳለ መገንዘባቸውን ገልጸው፥ የኢንዶኔዥያው ፕሬዝዳንትም በዛሬው ዕለት ባደረጉት ንግግር ስለ መግባባት እና ብዙሃነት የተናገሩትን አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ አስታውሰዋል። ዓለም በተበታተነችበት እና በተከፋፈለችበት በዚህ ወቅት የወደፊት ተስፋ በኢንዶኔዥያ ውስጥ መኖሩን እንደሚያምኑ እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዐይኖችም ለእውነት እና ለመልካም የወደፊት ጊዜ ፍለጋ ክፍት ናቸው” ብለዋል።