ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከእስያ እና ኦሼኒ ሐዋርያዊ ጉብኝት መልስ ለእመቤታችን ማርያም ምስጋናን ሲያቀርቡ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከእስያ እና ኦሼኒ ሐዋርያዊ ጉብኝት መልስ ለእመቤታችን ማርያም ምስጋናን ሲያቀርቡ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከእስያ እና ኦሼኒያ ጉብኝት መልስ ለእመቤታችን ማርያም ምስጋናን አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከነሐሴ 27/2016 እስከ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. ድረስ በእስያ እና ኦሼኒያ አኅጉራት ያደረጉትን የ12 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ሐዋርያዊ መንበራቸው በሰላም ተመልሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጨረሻ አገር ከሆነች ሲንጋፖር ተነስተው ወደ ሮም የደረሱት በጣሊያን የሰዓት አቆጣጠር ዓርብ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. ማምሻውን በ12፡25 ደቂቃ ላይ እንደሆነ ታውቋል።

በቫቲካን ወደሚገኝ ሐዋርያዊ መንበራቸው ከመመለሳቸው ቀደም ብለው 12 ቀናትን በፈጀ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ለደገፈቻቸው እና ጥበቃ ላደረገችላቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስጋና አቅርበዋል።

ዓርብ ማምሻውን ከፊውሚቺኖ አየር ማረፊያ ወደ ቫቲካን ሲመለሱ በሮም ወደሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካ ደርሰው የከተማው ነዋሪዎች ጠባቂ በሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል ፊት ጸሎት ማድረሳቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።

በእስያ እና ኦሼኒያ ባደረጉት የ12 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት እናታዊ ጥበቃ ላደረገችላቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአበባ እቅፍ ጋር ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ ወደ ቫቲካን ቅድስት ማርታ የጳጳሳት መኖሪያቸው በሰላም መመለሳቸውን መግለጫው አክሎ አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ኢንዶኔዥያ፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ ቲሞር-ሌስቴ እና ሲንጋፖርን ያደረጉት 45ኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት በርዕሠ ሊቃነ ጵጵስናቸው ዓመታት ውስጥ ካደረጓቸው ሐዋርያዊ ጎብኝቶች መካከል ረጅሙ ነው ተብሏል።

 

14 September 2024, 10:16