ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጃካርታ ተረጂዎችን “የፍቅር አሸናፊዎች ናችሁ” በማለት አጽናንተዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጃካርታ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተረጂዎች ጋር ተገናኝተው ምስክሮቻቸውን አድምጠዋል። ቅዱስነታቸው የተረጂዎችን ታሪክ ካዳመጡ በኋላ እያንዳንዳቸውን “በታላቁ የሕይወት ውድድር ውስጥ የፍቅር አሸናፊዎችሁ ናችሁ” በማለት አጽናንተዋቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሁለተኛ ቀን በሆነው ረቡዕ ነሐሴ 29/2016 ዓ. ም. በኢንዶኔዥያ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተጠቃሚዎች ጋር ተገናኝተዋል።

የአገሪቱ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት አቡነ አንቶኒየስ ሱቢያንቶ ለቅዱስነታቸው ያላቸው ፍቅር ወሰን የለሽ ነው በማለት ስብሰባው የከፈቱ ሲሆን፥ እሳቸውን በብጹዓን ጳጳሳቱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ከተገኙት አንዳንድ በሽተኞች፣ አካል ጉዳተኞች እና ድሆች ጋር ከማስተዋወቃቸው በፊት ሁለቱ ተረጂዎች ታሪካቸውን እንዲያካፍሉ ጋብዘዋል።

ታሪኳን በቅድሚያ የተናገረችው ወጣት ሚሚ በ17 ዓመቷ የዓይን ብርሃኗን ማጣቷን ገልጻ፥ ካቶሊክ በመሆኗ በመስቀል መንገድ ጸሎት መጽናናትን ማግኘቷን አስረድታለች። ኢየሱስ ፈጽሞ እንዳልተዋት በማመን “እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በዓለማችን ውስጥ ያለውን ልዩነት ለማሳደግ ልዩ ችሎታ ያላቸውን ፍጥረታት አድርጎ እንደፈጠረ አጥብቄ አምናለሁ፤ የአካል ጉዳተኝነት ከእነዚህ ልዩ ገጽታዎች መካከል አንዱ ነው። የቤተ ክርስቲያን ሚናም የሰውን ልጅ ክብር በማረጋገጥ ረገድ ወሳኝ ነው” ስትል ታሪኳን ደምድማለች። ላሳዩት ርኅራኄ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ከማመስገኗ በፊት “ተስፋ ይሰጡናል” ስትል ተናግራለች።

ሁለተኛው ተናጋሪ ኤንድሪው የተባለ ወጣት ሲሆን፥ አትሌት እና መለስተኛ የአዕምሮ ዝግመት እክል ያለበት ቢሆንም ወላጆቹ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚወዱት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተናግሯል። ለፓራኦሎምፒክ ውድድሮችች የምስራቅ ጃካርታ ተወዳዳሪ ሆኖ መመረጡን እና እራሱን ችሎ ለመኖር ካለው ፍላጎት የተነሳ የአስተናጋጅነት፣ የጊታር እና የከበሮ ስልጠና እና ትምህርቶችን መውሰድ መጀመሩን ተናግሯል። በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወላጆቹን እና በዓለም ዙሪያ በዚህ ሕመም የተጠቁ ልጆች ያሏቸውን ወላጆች ቅዱስነታቸው እንዲባርኳቸው ጠይቋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምስጋና
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በሥፍራው ለተገኙት ሁሉ እና ምስክርነታቸውን ላካፈሉት ሁሉ ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ ለ100ኛ ዓመት የመታሰቢያ በዓላቸው የኢንዶኔዥያ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳትንም በማመስገን እንደ ትናንሽ ብሩህ ኮከቦች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ጠቀሜታ አጉልተው አሳይተዋል።

ቅዱስነታቸው ለወጣት ሚሚ በሰጡት ምላሽ፥ የዓለማችንን ልዩነት የሚያበለጽግ የሰው ልጅ ችሎታ ልዩ መሆኑን በማጉላት “ኢየሱስ የተስፋችን ብርሃን ነው” በማለት በተናገረችው አመስግነው፥ በመቀጠል በሥፍራው የተገኙትን በሙሉ “በታላቁ የሕይወት ውድድር የተካፈሉ የፍቅር አሸናፊዎች ናችሁ” ካሉ በኋላ በፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ በመሳተፉ እንኳን ደስ አለህ! በማለት ኤንድሪውን አመስግነውታል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን በአጭር ሰላምታ ሲያጠቃልሉ፥ “እግዚአብሔር ማንንም ሳይዘነጋ ሁላችንንም ይወዳልና” ብለው፥ በዚህ መንፈስ በአሳዛኝ ሁኔታ በሕመም ምክንያት ዝግጅቱ ላይ መገኘት ያልቻለች እና 87ኛ ዓመት የልደት ቀኗን ለምታከብር አንዲት እናት መልካም ምኞታቸውን ልከዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጃካርታ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተረጂዎች ጋር ተገናኝተውዋል
05 September 2024, 16:57