ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለፓፑዋ ኒው ጊኒ ምዕመናን፥ "የሕይወታችን መሪ እግዚአብሔር ብቻ ነው!"
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቀለማት ባሸበረቁ የፓፑዋ ኒው ጊኒ ሕዝብ የብዝሃነት እና የአንድነት መግለጫ በሆነው የባሕል ልብስ እና የሙዚቃ መሣሪያ ከታጀቡት ምዕመናን ጋር ሆነው በሲር ጆን ጊዝ ስታዲዬም የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በእንግሊዝኛ ቋንቋ መርተዋል።
የማበረታቻ ቃል
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከ30 ዓመታት በፊት በፓስፊክ ውቅያኖስ ውስጥ ለምትገኝ እና እጅግ ሩቅ ለሆነችው ፓፑዋ ኒው ጊኒ የማበረታቻ እና የተስፋ መልዕክት ማምጣታቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የፓፑዋ ኒው ጊኒ ሕዝብ በእግዚአብሔር እና በመንፈስ ቅዱስ ስም የተዋሐደ ነው ሲሉ በስብከታቸው በማብራራት፥ “እግዚአብሔር የፓፑዋ ኒው ጊኒ ሕዝብን ዛሬም አይዞአችሁ አትፍሩ! ለወንጌል ደስታ እና ለወንድሞች ፍቅር ራሳችሁን ክፈቱ የሚለን ስለሆነ ለዚህ ግብዣ ሁላችንም ብንሆን ችላ ማለት አይገባም” ብለዋል።
የተዘጋ ልብ
“የዛሬው ሰው በማርቆስ ወንጌል ውስጥ የተገለጸውን ደንቆሮ ሰው ሊሆን ይችላል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ይህ ሰው መስማት እና ማየት ስለማይችል ደንቆሮነቱ እራሱን ከሌሎች ጋር የሚያነጻጽርበት ብቸኛው ማመሳከሪያ ነው ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን በማስታወስ፥ ከዮርዳኖስ ማዶ የሚገኝ ይህ ሰው ከእግዚአብሔር እና ከሰዎች የራቀበትን ድንቁርናውን እና ልበ ደንዳነቱን እንድንመለከት አሳስበውናል።
ውስጣችንን የሚዘጋን ራስ ወዳድነት፣ ግዴለሽነት፣ ፍራቻ፣ ጥላቻ እና ሌሎች እንቅፋቶችም እንዳሉ ጠቁመው፥ “እነዚህ በሙሉ ከእግዚአብሔር፣ ከወንድሞቻችን እና ከእኅቶቻችን ጋር አልፎ ተርፎም ከራሳችን ጋር እንዳንገናኝ በማድረግ ከአስደሳች ሕይወት የሚያርቁን ናቸው” በማለት አስገንዝበዋል።
አምላክ ለልጆቹ ቅርብ ነው!
በተቃራኒው “ለዚህ ዓይነቱ መራራቅ እግዚአብሔር ልጁን ኢየሱስን ወደ እኛ በመላክ ምላሽ እንደሰጠን፣ እርሱ ሁልጊዜ ቅርባችን፣ ሩኅሩኅ፣ ሕይወታችንን የሚንከባከብ እና ሁሉንም ርቀቶች የሚያሸንፍ አምላክ ነው” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስገንዝበዋል።
የሕይወታችን መሪ
“የሰውን ልበ ደንዳናነት እና ድንቁርና የሚፈውሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የርቀት ስሜት ሲሰማን ወይም ራሳችንን ከእግዚአብሔር፣ ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ስናርቅ እራሳችንን በመዝጋት ብቻችንን እንቀራለን፣ ለእግዚአብሔር ቃል እና ለባልንጀራችን ጩሄት ችላ ስለምንል ከእግዚአብሔር እና ከጎረቤታችን ጋር መነጋገር ይሳነናል” ብለው፥ እራሳችንን ለእግዚአብሔር፣ ለወንድሞቻችን እና ለቅዱስ ወንጌል በመክፈት የሕይወታችን መሪ ማድረግ አስፈላጊው ነው” ብለዋል።
ይህ ግብዣ በጥላቻ ምክንያት የተገደለውን የሚስዮናዊ የብሩክ ጆቫኒ ማዙኮኒ ፈለግ ለመከታተል እንደሚያግዝ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ይህ ገዳማዊ ማንም የድኅነትን መልዕክት ሰምቶ ችላ እንዳይል፣ ሁሉም የእግዚአብሔርን ፍቅር ለመመስከር ምላሱን እንዲፈታ” በማለት በብዙ መከራ እና ጠብ መካከል ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ሕዝቡ ዘንድ ማምጣቱን ገልጸዋል።
ሚስዮናውያንን የምታመሰግን ቤተ ክርስቲያን
በመስዋዕተ ቅዳሴው ፍጻሜ ላይ የፖርት ሞርስቢ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ጆን ሪባት ለፓፑዋ ኒው ጊኒ ቤተ ክርስቲያን ሲሉ ሕይወታቸውን የሰጡ በርካታ ሰማዕታት መኖራቸውን በማስታወስ ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ አስቸጋሪ የሁከት፣ የግድያ፣ የንብረት ውድመት እና የተፈጥሮ አደጋ ጊዜያት እንደ ነበሩ አስረድተዋል።
ሁልጊዜ ለሰላም፣ ለዕድገት፣ ለፈውስ እና ለበረከት እንጸልያለን” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ጆን ሪባት በመጨረሻም ከሮማ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለንን አንድነት በማጠናከር በረከትን፣ ሰላምን እና ብርታትን የሚያጎናጽፉንን፣ እምነታችን እንዲጠነክር የሚያግዙን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስንን ለሐዋርያዊ ጉብኝታቸው እናመሰግናለን” ብለዋል።