ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥  2025 ዓ. ም. የብርሃነ ትንሳኤው በዓል አስተባባሪዎች ጋር ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ 2025 ዓ. ም. የብርሃነ ትንሳኤው በዓል አስተባባሪዎች ጋር  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የትንሳኤው በዓል የኢየሱስ ክርስቶስ በዓል እንጂ የዘመን መቁጠሪያችን አይደለም!”

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ለመጪው 2025 ዓ. ም. ሁሉም ክርስቲያኖች የብርሃነ ትንሳኤው በዓልን በጋራ ለማክበር በሚዘጋጁበት በዚህ ወቅት፥ ይህ ክርስቲያናዊ በዓል የኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ የምድራዊ የቀን መቁጠሪያዎቻችን ወይም እቅዶቻችን እንዳልሆነ ቅዱስነታቸው አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከተለያዩ በርካታ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች እና ማኅበራት ተወካዮች እንዲሁም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ 2025 ዓ. ም. የብርሃነ ትንሳኤው በዓል አስተባባሪዎች ጋር ሐሙስ መስከረም 9/2017 ዓ. ም. በቫቲካን ተገናኝተዋል።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጪው 2025 በሚከበረው የኢዮቤልዩ ዓመት፥ የብርሃነ ትንሳኤው በዓል የዩልዮሳውያኑን እና የጎርጎሮሳውያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ ክርስቲያኖች ዘንድ በተመሳሳይ ቀን እንደሚከበር ታውቋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መጭው 2025 በተጨማሪ፥ የመጀመሪያው የኒቂያ የአብያት ክርስቲያኖች ጉባኤ የእግዚአብሔርን ልጅ መለኮታዊ ተፈጥሮን የሚያብራራ ጸሎተ ሃይማኖትን ለቤተ ክርስቲያን ይፋ ያደረገበት 1,700ኛ ዓመት የሚከበርበት እንደሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመጭው የጋራ የብርሃነ ትንሳኤው በዓል አስተባባሪዎች ባደረጉት ንግግር፥ ለተነሳሽነታቸው አባላቱን አመስግነው፥ “ይህ ልዩ ዕድል በከንቱ ማለፍ የለበትም” በማለት አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንደ በተለያዩ ቀናት የሚከበረውን የብርሃነ ትንሳኤው በዓል በተመለከተ መፍትሄ እንዲፈልጉ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ ቁርጠኛ የሆኑ ሰዎች የጋራ ስምምነትን በጽናት በመፈለግ የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ አደራ ብለው፥ ይልቁንም በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን መካከል የበለጠ መከፋፈልን ሊፈጥር ከሚችል ከማንኛውም ነገር መራቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም የብርሃነ ትንሳኤው በዓል በእኛ ምርጫ የሚከበር አለመሆኑን እና ከየትኛውም የቀን መቁጠሪያ ጋር እንደማይገናኝ ተናግረዋል።

የጌታ ትንሳኤ የተከናወነው፥ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐ. 3:16) በሚለው መሠረት የተከናወነ መሆኑን አስረድተው፥ በዚህም የእግዚአብሔርን ቀዳሚነት መርሳት የለብንም ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም፥ ክርስቲያኖች በእቅዶቻችን፣ በሐሳቦቻችን፣ በቀን መቁጠሪያዎቻችን ወይም “በፋሲካችን” ተወስነን እንዳንቀር አሳስበዋል።

“ትንሳኤው የኢየሱስ ክርስቶስ ነው!” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ልንከተለው የሚገባንን መንገድ እርሱ እንዲያሳየን በመፍቀድ እና ደቀ መዛሙርቱ እንድንሆን ጸጋውን ብንለምን መልካም ነው” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ ስለ ክርስቶስ እንድንመሰክር እና ዓለም እንዲያምን ክርስቲያኖች ማስተንተን፣ ማቀድ እና አብረው መጓዝ እንደሚገባ በማሳሰብ፥ “የሰላሙ ንጉሥ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላሙን ይሰጠን ዘንድ ዛሬ ወደ እርሱ ተመልሰን ልንጸልይ ይገባል” ብለዋል።

 

19 September 2024, 14:50