ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከሕዝባዊ እንቅስቃሴ ተወካዮች ጋር በቫቲካን ተገናኝተው ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከሕዝባዊ እንቅስቃሴ ተወካዮች ጋር በቫቲካን ተገናኝተው   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ለማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ፍትህ እንዲሠሩ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአሥር ዓመት በፊት በቫቲካን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበትን ዕለት የሚያከብሩ የልዩ ልዩ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ተወካዮች ጋር ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለተወካዮቹ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ማኅበራዊ ኢ-ፍትሐዊነትን እንዲዋጉ በማበረታታት፥ መሠረታዊ የሆነው ሁለንተናዊ ገቢ እንዲያድግ እና ባለሃብቶች ከፍተኛ ግብር እንዲከፍሉ ያቀረቡትን ሃሳብ በድጋሚ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈትን ዓርብ መስከረም 10/2017 ዓ. ም. ጎብኝተው ሰብዓዊነትን የሚያዋርዱ ተግባራትን ለመቃወም የተደረገ የባንዲራ መትከል ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከቅዱስነታቸው ጋር ለመገናኘት ከሚጠብቋቸው እንግዶች መካከል፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2014 በቫቲካን ለመጀመሪያ ጊዜ ከቅዱስነታቸው ጋር የተገናኙበትን አሥረኛ ዓመት የሚያከብሩ የልዩ ልዩ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ተወካዮች እንደነበሩ ታውቋል።

ከአምስቱ አኅጉራት የተውጣጡ የትናንሽ ሕዝባዊ ድርጅቶች የወንድማማችነት መድረክ ዋና ዓላማ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2014 ጀምሮ የዛሬዎቹን ተግዳሮቶች ለመፍታት፣ ማኅበራዊ ፍትህን ለማምጣት እና በጋራ መኖሪያ ምድራችን ውስጥ ሰላምን ለማንገሥ ሲባል የመኖሪያ ቤትን፣ የእርሻ መሬትን እና የሥራ ዕድልን በማመቻቸት የእርስ በርስ ግንኙነት ባሕልን ማበረታታት እንደሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከስብሰባው ተሳታፊዎች መካከል ሆነው፥ “አንድም ቤተሰብ ያለ መጠለያ፣ ገበሬ ያለ መሬት፣ ሠራተኛ ያለመብት እና ያለ ሥራ ክብር መኖር የለበትም” በሚሉት ርዕሦች ላይ የተደረጉ ውይይቶችን አድምጠዋል።

የሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ምሥረታ አሥረኛ ዓመት መታሰቢያ

ወንድማማችነትን ማሳደግ
ቅዱስነታቸው ማኅበራዊ ፍትህን በማስመልከት ባደረጉት ረጅም ንግግር፥ ለችግር ተጋላጭ ለሆኑት አረጋውያን፣ ሕጻናት እና ድሆች እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበው፥ ለርህራሄ ከፍተኛ ዋጋን በመስጠትም የሌሎችን መከራ መጋራት፣ ከጎናቸው መቆም እና ለድምጽ አልባዎች ድምጽ መሆን እንደሚገባ አደራ ብለዋል። ሃብት፥ ከሌሎች ጋር በመካፈል ወንድማማችነትን ለመፍጠር እና ለማስተዋወቅ የተሠራ በመሆኑ ባለጠጎች ሃብታቸውን ከሌሎች ጋር እንዲካፈሉ ጠይቀዋል።

“ያለ ፍቅር ምንም መሆን አንችልም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የእርስ በርስ ግንኙነቶች በሙሉ በፍቅር ላይ መመሥረት እንዳለባቸው በማሳሰብ፥ ቅዱስ ሉቃስ በጻፈው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ምዕ. 18: 2-5 ላይ የተጠቀሰውን የመበለቷን ምሳሌ በማስታወስ ፍትህ ያለ አመፅ መምጣት እናዳለበት ተናግረዋል።

የሃብታሞች ስግብግብነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የወንጌል ደስታ” የሚለው የሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ዋና መሪ ሃሳብ በማስታወስ እንደተናገሩት፥ የገበያን ፍፁም የራስ ገዝ አስተዳደር እና የፋይናንስ ትንበያን ውድቅ በማድረግ የድሆችን ችግር መፍታት እንደሚያስፈልግ አሳስበው፥ ባለጠጎችም ጭምር ሁላችንም በድሆች እንደምንመካ ተናግረዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ይልቅ ስለ ድሆች መናገርን ይመርጣሉ” በማለት አንዳንዶች ቢተቿቸውም ነገር ግን ቅዱስ ወንጌል ድሆችን ዋና ማዕከል እንደሚያደርጋቸው አስገንዝበዋል።ለሰዎች የእርሻ መሬት፣ መጠለያ እና ፍትሃዊ ደሞዝ የሚያረጋግጡ ፍትሃዊ ፖሊሲዎች ከሌሉ፥ የቁሳቁስ እና የሰው ኃይል ብክነት እንደሚስፋፋ እና ይህም ለአመፅ እና ለጥፋት እንደሚዳርግ አስጠንቅቀዋል።

“ከስግብግብነት የተነሳ ብዙውን ጊዜ ማኅበራዊ ፍትህን ወይም ሥነ-ምህዳርን እውን ማድረግ የሚቃወሙት ሃብታሞች ናቸው” ብለው፥ ይህ ስግብግብነት ብዙውን ጊዜ በርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ እንደሚሸነፍ እና መንግሥት ጎጂ ፖሊሲዎችን እንዲደግፍ የሚገፋፋ መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

ሃብትን ከሌሎች ጋር መጋራት
የኤኮኖሚ ኃያላን ተገንጥለው እንደሚወጡ ተስፋ እንዳላቸው የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የገንዘብን የውሸት ዋስትናን ውድቅ በማድረግ ሃብት መጋራትን መቀበል እንደሚገባ እና ይህም ከራሱ ከፍጥረት የመነጨ ዓለም አቀፋዊ ዕጣ ፈንታ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሃብትን እንደ ምጽዋት ሳይሆን በወንድማማችነት መንፈስ በሰዎች መካከል በፍትሃዊነት ሊከፋፈል እንደሚገባ አበክረው ተናግው፥ በእውነታው የተዛባ አመለካከት በመያዝ የሃብት ክምችት በጎነትን እንደሚያጎናፅፍ የሚያስቡት ሁሉ ሃብትን በጋራ ካልተጠቀሙት ወደ ጥፋት ሊወስድ ስለሚችል ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ አሳስበዋል

“ሃብትን መሰብሰብ ሳይሆን የተሰበሰበውን ለሌሎች ማካፈል በጎነት ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ኢየሱስ አምስት እንጀራ እና ሁለት ዓሣዎችን አባዝቶ አምስት ሺህ እና ከዚያም በላይ ሰዎችን እንደመገባቸው አስታውሰው፥ ሃብትን ማከማቸት የሚገባው በሰማይ እንጂ በምድር እንዳልሆነ የሚገልጸውን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ጠቅሰዋል።

የተገለሉ ሰዎች ጩኸት
ከቁጥጥር የወጣ የሃብት ማከማቸውት ፉክክር ወደ ጥፋት የሚያደርስ አጥፊ ኃይል እንደሆነ ተናግረው፥ኃላፊነት የጎደለው፣ ሥነ-ምግባር የጎደለው እና ምክንያታዊነት የጎደለው ነው” ሲሉ አውግዘዋል። ይህ ስግብግብነት የሰውን ልጅ የሚከፋፍል እና ፍጥረትን የሚያጠፋ ነው” ሲሉም አክለዋል።

ኤኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ መብቶችን የማስከበር ኃላፊነት ያለባቸውን የፖለቲካ መሪዎች ህሊናቸውን በማንቃት በማኅበረሰቡ የተገለሉ ሰዎችን ጩኸት እንዲያዳምጡ አሳስበዋል። እነዚህ መብቶች በአብዛኛዎቹ ሀገራት እና በተባበሩት መንግሥታት እውቅና የተሰጣቸው ቢሆንም በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እውነታ ላይ ያልተሟሉ ናቸው ብለዋል።

ርህራሄን ማድረግ
ፍትሕ በርኅራኄ መታጀብ እንዳለበት ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ይህ ማለት “ከሌሎች ጋር መከራን መቀበል እና ስሜታቸውን መጋራት ማለት ነው” ብለዋል። ርኅራኄን ማድረግ ማለት ምጽዋትን መስጠት ማለት ሳይሆን ነገር ግን መተሳሰብ እና መረዳዳት ማለት ነው” ብለው፥ እውነተኛ ርኅራሄ አንድነትን እና የዓለምን ውበት ይገነባል” ሲሉ አስረድተዋል።

ማንም መናቅ የለበትም
“የአሸናፊዎች ባሕል” የሚባለውን የተበላሸ ባሕል ገጽታን አውግዘው፥ “ይህ ድርጊት ብዙውን ጊዜ ሰዎችን ወይም ተፈጥሮን በመበዝበዝ ገንዘብ ነክ ከሆኑት ጉዳዮች ጋር በማገናኘት አንዳንዶችን ከታክስ ማጭበርበር ወይም ከተደራጁ ወንጀሎች ተጠቃሚ በማድረግ “ተሸናፊዎች” የሚባሉትን በትዕቢት እንዲንቋቸው ያደርጋቸዋል ብለዋል።

ሌሎችን በግዴለሽነት ወይም በንቀት መመልከት ዓመፅን እንደሚያቀጣጥል ያስጠነቀቁት ቅዱስነታቸው፥ ኢ-ፍትሃዊነትን በዝምታ መመልከት ለማኅበራዊ ክፍፍል እንደሚዳርግ፥ ማኅበራዊ መለያየት ለብጥብጥ መንገድ እንደሚከፍት፥ “የቃላት ጥቃት አካላዊ ጥቃትን እና አካላዊ ጥቃት ጦርነትን ይቀሰቅሳል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

የፍቅር ጥሪ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ በሁሉም የሕይወት ዘርፍ የፍቅር አስፈላጊነትን በማረጋገጥ፥ በቅርቡ በቲሞር-ሌስቴ መዲና ዲሊ ውስጥ የአካል ጉዳተኛ ልጆች ትምህርት ቤት መጎብኘታቸውን ጠቅሰው፥ “ፍቅር ከሌለ አገልግሎቱ ምንም ትርጉም አይሰጥም” ብለዋል። ማኅበራዊ ፍትህን እና ጠቅላላ ሥነ-ምህዳርን መረዳት የሚቻለው በፍቅር ብቻ መሆኑን የሕዝባዊ እንቅስቃሴ ማኅበራት ተወካዮችን አስታውሰዋል።

የኃይለኞች ብቻ በሕይወት መኖር  ወይም ማኅበራዊ "ዳርዊኒዝም”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የግል ጥቅምን እና ግለሰባዊነትን ማሳደድ ወደ ማኅበራዊ ዳርዊኒዝም ወይም ኃይለኞች ብቻ በሕይወት ወደ መትረፍ ያመራል ብለው፥ ይህም የኃይለኞች ሕግ ግዴለሽነትን እና ጭካኔን ያረጋግጣል ብለዋል።

ይህም ከክፉ መንፈስ እንደሚመጣ በመጥቀስ የኅብረተሰቡን እሴቶች ለማጥፋት የሚጥሩትን እና ባሕላዊ ትውስታን ወይም ማንነትን ለማጥፋት የሚደረገውን ማንኛውንም ሙከራ እንዲቃወሙ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ማኅበራትን አሳስበዋል።

የተደራጀ የወንጀል ድራማ
በድሆች እና በተገለሉ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ የተደራጁ ወንጀሎች መበራከታቸው እንዳሰጋቸው ገልጸው፥ በሕዝባዊ ኢኮኖሚ አማካኝነት የሚፈጸሙ የወንጀል ኢኮኖሚን መታገል እንደሚገባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጠይቀው፥ ማንኛውም ሕጻን ወይም ሰው በገዳይ ወንጀለኞች እጅ ውስጥ ገብቶ ሸቀጥ መሆን እንደሌለበት አሳስበዋል።

ሁለንተናዊ የሆነ መሠረታዊ ገቢ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን ማንም ሰው ከመሠረታዊ ፍላጎቶች የተነፈገ አለ መሆኑን ለማረጋገጥ ሁለንተናዊ የሆነ መሠረታዊ ገቢ ሊኖረው እንደሚገባ ጥሪያቸውን አድሰው፥ ይህም ርህራሄ ብቻ ሳይሆን ጥብቅ ፍትህ መሆኑን አበክረው ተናግሯል።

ቅዱስነታቸው ለወደፊት ትውልዶች ያላቸውን የግል ተስፋ ሲገልጹ፥ “አዲሱ ትውልድ እኛ ከተቀበልነው ዓለም የተሻለ ዓለም እንዲያገኝ በመመኘት፥ ተስፋ ደካማ በጎነት ያለበት ቢሆንም ነገር ግን ማንንም የማያሳዝን መሆኑን በተስፋ መልዕክታቸው ተናግረዋል።


 

21 September 2024, 15:54