ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የሲንጋፖር ቤተ ክኅነት አንድ እንዲሆን እና ከሕዝቡ ጋር እንዲቀራረብ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው 45ኛውን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በሲንጋፖር ባጠናቀቁበት የመጨረሻ ዕለት በአገሪቱ ሐዋርያዊ አገልግሎት በማበርከት ላይ ከሚገኙ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካኅናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት ጋር ተገናኝተዋል።
ቅዱስነታቸው ከአባላቱ ጋር በግምት 20 ደቂቃ የፈጀ የግል ስብሰባ ያካሄዱት በከተማው በሚገኝ በቅዱስ ፍራንችስኮስ ዛቪየር የሱባኤ ማዕከል ውስጥ እንደሆነ ታውቋል።
የቅድስት መንበር መግለጫ እንደገለጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካህናትን አንዳንድ ባህሪያት በመጥቀስ፥ በሕዝቡ መካከል እንዲሆኑ፣ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲተባበሩ፣ በመካከላቸው ወንድማማችነትን በማሳደግ ከጳጳስ ጋር አንድ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ቅዱስነታቸው ለገዳማውያት ባስተላለፉት መልዕክትም፥ ማንነታቸውን እንዲያስታውሱ በማበረታታት፥ “የቤተ ክርስቲያንን እናትነት መግለጽ እንዳትረሱ” ሲሉ ተናግረዋል።
በመጨረሻም ለአባላቱ ሐዋርያዊ ቡራኬን ከመስጠታቸው እና የኅብረት ፎቶ ከማነሳታቸው በፊት፥ ሁሉም ሰው በአገልግሎቱ ደስተኛ እና ፈገግታ የማይለየው እንዲሆን አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሲንጋፖር ቤተ ክኅነት ጋር በተገናኙበት ዕለት በመካከላቸው የማሌዢያ፣ የሲንጋፖር እና የብሩኔ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ፕሬዝዳንቶችም ተገኝተዋል።