ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ነፃነት ማለት ሌሎችን ማክበር ማለት እንደሆነ ለቲሞር ወጣቶች አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ በቲሞር-ሌስቴ ባደረጉት የሦስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ከወጣቶች ጋር ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለቲሞር ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ነፃነት ማለት ሌሎችን ለማክበር ምርጫ ማድረግ እንደሆነ አስገንዝበው፥ ለሀገራቸው የወደፊት እጣ ፈንታ ኃላፊነት የሚሰማቸው ነፃ ተዋናዮች እንዲሆኑ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ሁለት ምክረ ሃሳቦች አሉኝ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እነርሱም ውጥንቅጥ ሕይወት መኖር እና አረጋዊያንን አክብሯቸው” የሚሉ እንደሆኑ ገልጸው፥ ረቡዕ መስከረም 1/2017 ዓ. ም. በዋና ከተማዋ ዲሊ ውስጥ ከቲሞር-ሌስቴ ወጣቶች ጋር በተገናኙ ጊዜ ምክሮቻቸውን ለግሰዋል።

ቅዱስነታቸው ከአገሪቱ ወጣቶች ጋር የተገናኙት በስብሰባ ማዕከል ሲሆን፥ ሥነ-ሥርዓቱ በቲሞር-ሌስቴ ያደረጉት የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጨረሻው ዝግጅት እንደ ነበር ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፥ ከ1.4 ሚሊዮን ሕዝብ ከ95% በላይ ካቶሊኮች መካከል አብዛኞቹ ወጣቶች እንደሆኑ እና እምነታቸውን በትጋት ለመምራት ባላቸው ፍላጎት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቲሞር ሕዝቦች ፈገግታን ፈጽሞ እንደማይረሱ ተናግረው፥ በማከልም የቲሞር ወጣቶች አባቶቻቸው የአገሪቱን መሠረት ለመጣል የከፈሉትን መስዋዕትነት እንዲያስታውሱት ጋብዘው፥ አጋጣሚውን በመጠቀም የአገራቸውን አረጋውያን እንዲያከብሩ በማሳሰብ፥ አንድ ማኅበረሰብ ሁለት ሃብቶች እንዳሉት እነርሱም ወጣት እና አረጋውያን መሆናቸውን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እርግብ ወደ ላይ ሲለቁ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እርግብ ወደ ላይ ሲለቁ

ልጆችን እና አረጋውያንን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ብዙ ልጆች ያሉት ማኅበረሰብ ሊንከብከቧቸው እንደሚገባ እና ብዙ አረጋውያን ያሉት ማኅበረሰብም የታሪክ ባለቤት በመሆኑ ሊያከብሯቸው እና ሊንከባከቧቸው ይገባል ብለዋል።

“ነፃነት፣ ቁርጠኝነት እና ወንድማማችነት” የሚሉ ሦስት እሴቶችን በአጭሩ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቲሞር ሌስቴ የቴቱም ቋንቋ፥ “ኡኩን ራሲክ-አን” ማለት ትርጉሙም፥ “ሁሉም ሰው ራሱን ማስተዳደር ይችላል” ማለት እንደሆነ አስታውሰው፥ ወጣቶች የነጻነትን ትክክለኛ ትርጉም እና ዓላማ ማስታወስ እንዳለባቸው ተናግረው፥ “ነጻነት ማለት የምንፈልገውን ማድረግ ማለት ሳይሆን፥ ነፃነት ማለት ሌሎችን ማክበር እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን መንከባከብ ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።

የቲሞር ወጣት ለቅዱስነታቸው ሰላምታ ሲያቀርብ
የቲሞር ወጣት ለቅዱስነታቸው ሰላምታ ሲያቀርብ

ቅዱስነታቸው የወንድማማችነትን እና የእርቅን አስፈላጊነት ለወጣቶቹ በማስታወስ፥ “ደስታ ባለበት አገር ውስጥ የሚኖር ሰው ድንቅ የጀግንነት፣ የእምነት፣ የሰማዕትነት ታሪክ፥ ከሁሉም በላይ እምነት እና እርቅ አለው” ሲሉ አስረድተዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ የይቅርታ እና የእርቅ ምሳሌነት እንዲያስታውሱ በማሳሰብ ከቲሞር ወጣቶች ጋር ያደረጉትን ስብሰባ አጠናቅቀዋል።

ቅዱስነታቸው በዲሊ ከወጣቶች ጋር ሲገናኙ

 

11 September 2024, 17:11