ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓርማ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓርማ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተነገረ

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ46ኛ የውጪ አገራት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሉክሰምበርግን እና ቤልጂየምን እንደሚጎበኙ በሰጡ ዝርዝር ማብራሪያ ገልጸዋል። ሰላምን መሠረት ያደረገ ይህ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት መሪ ሃሳብ፥ “አህጉሪቱ እንደገና ወደ ግጭት ልትገባ የምትችልበት ወቅት” የሚል እንደሆነ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአውሮፓ አገራት በሆኑት ሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም 46ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉት ከሐሙስ መስከረም 16 እስከ እሑድ መስከረም 19/2017 ዓ. ም. እንደሚሆን መግለጫው አስታውቋል።

ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ስለ ሰላም፣ ስለ ስደት፣ ድንገተኛ የአየር ንብረት ለውጥ ስለሚያስከትለው አደጋ እና የወጣቶች የወደፊት ዕጣ ፈንታን ጨምሮ በርካታ ርዕሠ ጉዳዮችን፥ በቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች፣ በዓለማዊ ማኅበረሰቦች ውስጥ የክርስትናን ሚና እና የክርስትና ትምህርት አስተዋፅዖን በማስመልከት እንደሚናገሩ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በእነዚህ አገራት ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሌላው ምክንያት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1425 ዓ. ም. የተመሠረተው የሉቫን ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ 600ኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል እንደሆነ ታውቋል።

የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ፈለግን መከተል
ስለ 46ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝት ዝርዝር መግለጫ የሰጡት የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ የቅዱስነታቸውን የጤና ሁኔታ በማስመልከት ሰኞ መስከረም 13/2017 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ፥ እንግዶችን በቫቲካን ለመቀበል የነበራቸው ቀጥሮዎች መሠረዛቸውን ገልጸው ይህም በታየባቸው ቀላል የጉንፋን ምልክት እንደሆነ አስታውቀው፥ በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር ላይ እስካሁን ምንም ለውጥ እንዳልተደረገበት እና ሁሉም ነገር እንደታቀደው እንደሚቆይ አቶ ማቴዮ አክለው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1985 ዓ. ም. የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከሉቨን ካቶሊክ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እና ከዩኒቨርሲቲው ምሁራን ማኅበረሰብ ጋር ለመገናኘት ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የሚደረግ ጉብኝት እንደሆነ ታውቋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዚህ ወቅት በብራስልስ ውስጥ የሚገኘውን ገዳም ለአሥራ አራት ዓመታት የመራችው የእግዚአብሔር አገልጋይ አና ዴ ጂሰስ ብጽዕናን ምክንያት በማድረግ በንጉሥ ባውዶዊን ስታዲዬም የሚመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ሌላው የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር አካል እንደሆነ ታውቋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከዚህ በፊት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1995 ዓ. ም. ቤልጂየምን ጎብኝተው እንደ ነበር ሲታወስ፥ የሞሎካይ ዳሚየን በመባል የሚታወቀው የቅዱስ ዳሚየን ደ ቬስተር በሃዋይ ደሴት ለምጻሞችን እያገለገል ሕይወቱን መስዋዕት ያደረገ ታላቅ የቤልጂየም ሚስዮናዊ የብጽዕና በዓልን ማክበራቸው ይታወሳል።

የአውሮፓ ክርስቲያኖች ምስክርነት
ከቅዱስ ዳሚየን ቀደም ብሎ ሌሎች ብዙ ቅዱሳን እና ሚስዮናውያን የክርስትና እምነትን ለዘመናት በሰበኩባቸው በእነዚህ አገሮች ውስጥ ዛሬ ወደ 8,400 የሚጠጉ ካቶሊኮች በቤልጂየም እንዲሁም ከ300 ያልበለጡ ካቶሊክ ምዕምናን በሉክሰምበርግ እንደሚገኙ ታውቋል።

ዓለማዊነት የሚለው ቅዱስነታቸው ከሚያነሷቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል አንዱ ቢሆንም ነገር ግን በይበልጥ ክርስትና ካለፉት ጊዜያት በበለጠ በማይታወቅባት፣ በጥያቄዎች የተሞላች፣ ብዙ ያልተገለጡ ጉዳዮች ባሉባት እና የክርስቲያን ቁጥር የማሽቆልቆል አዝማሚያ በሚያሳይባት አውሮፓ ውስጥ የክርስቲያን ምስክርነት ፈተና ሊሆን ይችላል” ሲሉ አቶ ማቴዮ ብሩኒ አክለው፥ በእነዚህ ማኅበረሰቦች ውስጥ ለእነዚህ ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የማበረታቻ ሙከራዎች ቀድሞውኑ መኖራቸውን ገልጸዋል።

የአውሮፓ ተቋማት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአገራቱ የሚገኙ ካቶሊክ ማኅበረሰቦችን ከመጎብኘት በተጨማሪ ብዙ የአውሮፓ ተቋማት መቀመጫ ወደ ሆኑት ሁለት አገራት በተለይም የፋይናንስ ተቋም ወደሚገኝባት ሉክሰምበርግ እና የአውሮፓ ኅብረት መቀመጫ ወደ ሆነች ቤልጂየም መልዕክታቸውን እንደሚያደርሱ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቤጂየም እና በሉክሰምበርግ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓርማ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቤጂየም እና በሉክሰምበርግ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዓርማ

ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉባቸው እነዚህ አገራት ሌሎችም በአንክሮ የሚመለከቷቸው የዓለም ክፍሎች እንደሆኑ እና በአውሮጳ እምብርት የሚገኙ መሆናቸውን በማስታወስ፥ በቅርብ ጊዜ በዓለም ውስጥ ሊጫወቱት የሚፈልጉትን ሚና በማጉላት፥ ስደተኞችን በደስታ መቀበል እና በአገራት መካከል ያለውን አብሮነት ማሳደግ እንደሚገባ በመናገር፥ የወረራ እና የጥፋት ሰለባ የሆኑ ዛሬም በግጭቶች እና ጦርነት የሚሰቃዩ አንዳንድ አገራት መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

የሰላም ማዕከላዊ ጭብጥ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያንኛ ንግግር ከሚያደርጓቸው ሰባቱ ዋና ዋና ርዕሠ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሰላም እንደሆነ የገለጹት አቶ ማቴዮ ብሩኒ፥ ቅዱስነታቸው ንግግር የሚያደርጉባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መሪ ሃሳብ አህጉሪቱ እንደገና ወደ ግጭት ልትገባ በምትችልበት በዚህ ወቅት በጦርነቱ የደረሱት ስቃዮች ቆመው ሰላም እንዲሰፍን የተሠሩ ታሪኮን የሚያስታውሱበት ንግግር እንደሚሆን ተናግረው፥ አህጉሪቱ እየተወያየችበት ያለውን የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮችንም አንስተው እንደሚናገሩ ገልጸዋል።

የኅብረተሰብ ለውጥ
ከእነዚህ ጭብጦች ጋር የተጣመረ የካቶሊክ ትምህርት እና በቴክኖሎጂ ዕድገት ዘመን ውስጥ ያለው ሚናን በተመለከተ ንግግር እንደሚያደርጉ የገለጸው መግለጫው፥ በሁለቱ አገራት በሚገኙ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መስከረም 17 እና 18/2017 ዓ. ም. የሚደረጓቸው ሁለቱ ስብሰባዎች፥ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የክርስትና እምነት ዛሬም ለአውሮፓ ባሕል የሚናገረው ነገር” በሚል ርዕሥ ሃሳቦችን እንዲያቀርቡ ዕድል የሚሰጥ እንደሚሆን ታውቋል።

ከሉቨን ካቶሊክ ዩንቨርስቲ ፕሮፌሰሮች ጋር በሚደረገው ስብሰባ፥ ለስደተኞች የሚደረገውን ሰብዓዊ ዕርዳታን የሚያሳይ ቪዲዮ እንደሚቀርብ ታውቋል። ይህ ጭብጥ በዩኒቨርሲቲ ተቋማት ውስጥ ስደተኞች ካሉበት ሁኔታ እና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቤልጂየም ማኅበረሰብ እያስመዘገበው ካለው ለውጥ አንጻር የኅብረተሰቡን ፈተና የሚያሳይ ወቅታዊ ርዕሥ እንደሚሆን ታውቋል።

ጥቃት ከደረሰባቸው ጋር ሊደረግ የሚችል ስብሰባ
በመግለጫው ወቅት ከጋዜጠኞች በኩል ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል በካህናት የሚፈጸም የፆታዊ ጥቃት ጉዳይ፥ በተለይም የቤልጂየም ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከ15 የጥቃቱ ሰለባዎች ጋር ሊያደርጉ የሚችሉትን ስብሰባ በማስመልከት ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን፥ ስብሰባው በፍፁም ፈቃደኝነት የሚካሄድ እንደ ሆነ፣ የት እና መቼ እንደሚካሄድ ጳጳሳቱ ወደ ፊት እንደሚያሳውቁ ታውቋል።

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ፥ ስለዚህ ስብሰባ ማረጋገጫ ባይሰጡም ነገር ግን “የተለየ ስብሰባ የሚኖር ከሆነ ከጥቃቱ ሰለባዎች ጋር ከተስማሙ በኋላ ወደፊት መረጃ እንሰጣለን” ብለዋል። ይህን የሚመስሉ ሌሎች ጉዳዮች በተመለከተ ቤልጂየም ውስጥ ያለውን ስቃይ ቅዱስነታቸው እንደሚያውቁ እና ለዚህም ማጣቀሻዎችን እንደሚጠብቁ አቶ ማቴዮ ብሩኒ አስረድተዋል።

ጋዜጣዊ መግለጫው በማጠቃለያው ከአውሮፓ ኅብረት ባለስልጣናት እና ከተዛማጅ ተቋማት ጋር የሚደረጉ ስብሰባዎችን ጨምሮ የቅዱስነታቸው የአራት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝትን በዝርዝር ተመልክቷል።

ከዚህም ጋር ቅዱስነታቸው ከወጣቶች፣ ከካህናት ከገዳማውያን እና ገዳማውያት ጋር ብዙ ስብሰባዎች እንደሚኖሩ መግለጫው ገልጾ፥ የቅድስት መበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ቅድስት መንበርን በመወከል በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 79ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።

በተጨማሪም ጉባኤው ላይ የብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ ካርዲናል ሮበርት ፍራንሲስ ፕሪቮስት እና የቅድስና ጉዳዮች ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ብፁዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ እንደሚገኙበት መግለጫው አክሎ አስታውቋል።

 

24 September 2024, 17:06