ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ሉክሰምበርግ ለሰላም በመቆም የአንድነት ምሳሌ ልትሆን ትችላለች” አሉ

በሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቅድሚያ በጎበኟት ሉክሰምበርግ ውስጥ ንግግር አድርገዋል። ለስምንት ሰዓት ያህል በቆዩባት በዚህች አገር ውስጥ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር፥ በአውሮፓ እምብርት ላይ ያለች ትንሿ አገር የአውሮፓን አንድነት እና ሰላም ለማስፈን የምትጫወተውን ወሳኝ ሚና ገልጸው፣ ያገረሸውን የብሄረተኝነት ስሜት እና ጦርነት አውግዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ሉክሰምበርግ ከጦርነት አስከፊነት በተቃራኒ የሰላምን ጥቅሞች ለሁሉም ማሳየት ትችላለች” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ሐሙስ ጠዋት ወደ ሉክሰምበርግ በደረሱ ጊዜ ለመንግሥት ባለሥልጣናት ንግግር በማድረግ፣ ለሰላም ያላቸውን የረዥም ጊዜ ቁርጠኝነት እንዲያከብሩ እና በአኅጉሪቱ እያንሰራራ ያለውን የብሔረተኝነት ስሜት እና ጦርነት በማውገዝ አንድነት እና ወንድማማችነት የነገሠባት አውሮፓን እንዲገነቡ አበረታትተዋል።

ሉክሰምበርግ በአውሮፓ ውስጥ ሰላምን እና አንድነትን ለማስተዋወቅ የተጫወተችው ታሪካዊ ሚና

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንጉሣዊ ቤተ መንግሥት ውስጥ ለባለሥልጣናት፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ እና ለዲፕሎማሲያዊ አካላት ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር፥ ሉክሰምበርግ በአውሮፓ ውስጥ የታላላቅ ታሪካዊ ክስተቶች ምንጭ ሆና እንደምትገኝ አስታውሰው፥ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጥፋት በኋላ የአውሮፓ ኅብረት መሥራች አባል አገር በመሆን በአውሮፓ ሰላምን እና አንድነትን በማስተዋወቅ ረገድ የተጫወተችውን ወሳኝ ሚና አወድሰዋል።

“ጦርነት ምንጊዜም ሽንፈት መሆኑን መዘንጋት የለብንም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በአውሮፓ ውስጥ ከፍተኛ ገቢን የሚያስገኝ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት የጦር መሣሪያ ምርት መሆኑ እጅግ ያሳዝናል” ብለዋል። በአውሮፓ እምብርት ላይ የምትገኝ ይህች ትንሽ ሀገር እንድትበለጽግ እና በዓለም አቀፍ መድረክ ትልቅ ሚና እንድትጫወት የሚያስችላትን ጠንካራ የዲሞክራሲ መዋቅሯን አወድሰዋል።

“አንድ መንግሥት በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ትልቅ ሚና እንዲጫወት ወይም የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ምንጭ እንዲሆን የግዛቱ ስፋት ሆነ የነዋሪዎች ብዛት እንደ አስፈላጊ መስፈት ሆኖ የሚወሰድ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

የአገር ሃብት ለድሆች ያለውን ሃላፊነት ያካትታል!

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1985 በሉክሰምበርግ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት የተናገሩትን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ በተለይም ድሃ አገራትን በመደገፍ ረገድ ያደጉ አገራት መተባበር እንደሚያስፈልግ ደጋግመው አሳስበዋል።

ሉክሰምበርግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሕልን እና ትብብርን ለማስተዋወቅ የምትጫወተውን ሚና እንድትቀጥል አበረታትተው፥ ከቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ጋር በሚስማማ መልኩ ሁሉም በተደራጀ የመደመር ሂደት ውስጥ ዋና ተዋናዮች እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።

በተለይም የመኖሪያ አካባቢን የሚያከብር እና ማኅበራዊ መገለልን የሚቃወመው የዕድገት ሞዴል እንዲኖር ጥሪ አቅርበው፥ ሃብት መያዝ ኃላፊነትንም ጭምር የሚጠይቅ መሆኑን አስታውሰዋል።

ዕድገት ትክክለኛ እና መሠረታዊ እንዲሆን ከተፈለገ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን መዝረፍ እና ማውደም እንደማይገባ አሳስበው፥ እንደዚሁም “ሕዝቦችን ወይም ማኅበራትን ማግለል ወይም ወደ ጎን ማለት የለብንም” ብለዋል።

የተቸገሩ አገራት ከድህነት እንዲወጡ ለመርዳት እንደ ሉክሰምበርግ የመሳሰሉ የበለጸጉ አገራት ግዴታ እንዳለባቸው ተናግረው፥ ለስደት የሚገደዱ ሰዎች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረግ ይገባል ብለዋል። በዚህ ረገድ ታሪክ እና መድብለ ባህላዊ ሕዝብ ያለው የሉክሰምበርግ ንጉሣዊ አስተዳደር ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በመቀበል እና ከማኅበረሰቡ ጋር በማዋሃድ አርአያ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

በአውሮፓ ውስጥ እየቀነሰ የመጣውን የወሊድ መጠን ለመቅረፍ ፈጣን መፍትሄ ሊገኝለት እንደሚያስፈልግ በድጋሚ ተናግረው፥ “ልጆች የወደፊት ሕይወት ስለሆኑ ያስፈልጉናል!” ብለዋል።

ጦርነትን ለመቋቋም መንፈሳዊ እሴቶች ያስፈልጋሉ

አሁን በዓለም ላይ ያለውን አስደንጋጭ ሁኔታን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በአውሮፓም ጭምር ግጭቶች እንደገና መቀስቀሳቸውን ነቅፈው፥ ለዚህ ሞኝ ተግባር ምክንያት እንዳንሰጥ ዓይናችንን ወደ ላይ ማቅናት አለብን” ብለዋል።

“ሕዝቡ እና መሪዎቻቸው በክቡር እና ጥልቅ መንፈሳዊ እሴቶች መነሳሳት አለባቸው” ብለው፥ እነዚህ እሴቶች የሰው ልጅ ካለፉት ስህተቶች በባሰ ዛሬ ባለው ታላቅ የቴክኖሎጂ ኃይል እንዳይወድቅ የሚያግዙ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ቤተ ክርስቲያን በወንጌል ተመርታ ሰላምን እና ወንድማማችነትን ለማስፋፋት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠው፥ ሉክሰምበርግ ከጦርነት አስከፊነት በተቃራኒ የሰላምን ጥቅም ለሁሉም ማሳየት እንደምትችል እና የአገሮች መተባበር የሚጠቅም መሆኑን አስገንዝበዋል።

የዓለም መሪዎች ልዩነቶችን ለመፍታት በታማኝነት እና በቆራጥነት ተባብረው እንዲሠሩ አሳስበው፥ ፍሬያማ ስምምነቶችን ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን እንደማይጎዳ እና የሁሉንም ሰው ደህንነት እና ሰላም ሊገነባ እንደሚችል አስረድተዋል።

“የሐዋርያው ​​ጴጥሮስ ተተኪ እንደ መሆኔ እና የሰው ልጅ ስብዕናን ጠንቅቃ የምታውቅ ቤተ ክርስቲያን የምወክል በመሆኔ፥ ወንጌል የሕይወት ምንጭ እና ዘወትር አዲስ የግል እና የማኅበራዊ ተሃድሶ ኃይል መሆኑን ለመመስከር መጥቻለሁ” ብለዋል።

“ሌሎችን ማገልገል ይገባል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ “አገልግሎት” የሚለውን የሉክሰምበርግ ሐዋርያዊ ጉብኝት መሪ ቃል በመጥቀስ፥ ይህ መሪ ቃል የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ እንደሚያመለክት ገልጸው፥ እያንዳንዱን ሰው በየቀኑ ሊከተላቸው የሚገባው የተከበረ ተግባር እና የአኗኗር ዘይቤ እንደሆነ አስረድተዋል። እምነት የሌላቸውም ቢሆኑ ለወንድሞቻቸው፣ ለኅብረተሰቡ እና ለአገራቸው መሥራት እንዳለባቸው በማሳሰብ፥ “ይህ ለሁሉም ሰው ዘወትር የጋራ ጥቅም ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

በመጨረሻም “እግዚአብሔር ዘወትር በደስታ እና በልግስና ለማገልገል የሚያስችላችሁን ኃይል ይስጣችሁ!” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

27 September 2024, 10:40