ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፥ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በምናደርገው ጉዞ ወዳጅነትን ማዳበር ይገባል አሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእስያ እና በኦሼንያ በማድርግ ላይ በሚገኙት 45ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሦስተኛ ቀን ማለትም ሐሙስ ነሐሴ 30/2016 ዓ. ም ጠዋት በኢንዶኔዥያ መዲና ጃካርታ የሚገኘውን እና በደቡብ ምሥራቅ እስያ ትልቁ የተባለውን መስጊድ ጎብኘተው የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤን ተካፍለዋል። ቅዱስነታቸው ወደ ሥፍራው ሲደርሱ በታላቁ ኢማም ዶ/ር ናሳሩዲን ኡመር ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ጋር የሚያገናኘውን የመሬት ውስጥ የእግረኛ መንገድ ወይም “የወዳጅነት ዋሻን” ጎብኝተዋል። እንዲሁም በሁሉም ሃይማኖታዊ ወጎች ውስጥ ያሉ እሴቶች፥ የጥቃት እና የግዴለሽነት ባህልን በማሸነፍ እርቅ እና ሰላምን ለማጎልበት ውጤታማ መሆናቸውን በመግለጽ የኢስቲቅላል 2024 ዓ. ም. የጋራ መግለጫን ፈርመዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጉባኤው ተካፋዮች ባደረጉት በንግግር፥ ታላቁ ኢማም ላደረጉት መልካም አቀባበል እና መስተንግዶ ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ ይህ የአምልኮ እና የጸሎት ሥፍራ ለሰው ልጅ የሚሆን ታላቅ ቤት እንደሆነ በማስታወስ፥ በልባችን ከመለኮታዊው ጋር ለመገናኘት እና ከሰዎች ጋርም የወዳጅነት ደስታን የመለማመድ አስፈላጊነትን ተናግረዋል።
ውይይትን እና ስምምነትን ማዳበር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለኢንዶኔዢያውያን ታላቅ ስጦታ በሆነው በሃይማኖቶች እና በተለያዩ መንፈሳዊ ስሜቶች መካከል የሚደረገው ውይይት፣ እርስ በርስ መከባበርን እና ተስማምቶ መኖርን እንደሚያበረታታ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። “የመስጊዱ ታሪክ ለእነዚህ ጥረቶች ማሳያ ነው” በማለት የአካባቢው ነዋሪ የሆነው ክርስቲያን አርክቴክት አቶ ፍሬድሪክ ሲላባን በመስጊዱ ግንባታ የዲዛይን ውድድር ማሸነፉን አስታውሰው፥ ይህንን ስጦታ በየዕለቱ እንዲያዳብሩት ብርታትን በመመኘት የሃይማኖት ልምዶች ለወንድማማች እና ሰላማዊ ማኅበረሰብ ዋቢ ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የእርስ በርስ ግንኝነት እና ውይይት
የኢስቲቅላል መስጊድ እና የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ካቴድራልን የሚያገናኘው “የወዳጅነት ዋሻ” አስደናቂ ምልክት መሆኑን ቅዱስነታቸው በመግለጽ፥ እነዚህ ሁለት የአምልኮ ሥፍራዎች ፊት ለፊት የሚተያዩ ብቻ ሳይሆን እርስ በእርስ መያያዛቸው የግንኝነት፣ የውይይት እና እውነተኛ የወንድማማችነት ልምድ መሆኑን ተናግረዋል። እያንዳንዳችን በመንፈሳዊ ጉዟችን እግዚአብሔርን በመፈለግ እርስ በርስ በመከባበር እና በፍቅር ላይ መመሥረት የምንችል፣ አደገኛ እና ፈጽሞ ተቀባይነት ከሌለው ግትርነት እና አክራሪነት በመከላከል ግልጽ ማኅበረሰብን ለመገንባት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበርክት” ብለዋል።
ዘወትር አርቆ መመልከት ያሻል
“ለሁሉም ሃይማኖታዊ ስሜቶች የጋራ ግንድ የሆነው፥ ከመለኮት ጋር ለመገናኘት ያለን ፍላጎት፣ ሁሉን ቻይ የሆነው በልባችን ውስጥ ያስቀመጠው ወሰን የለሽ ጥማት፣ የበለጠ ደስታን በመፈለግ ከማንኛውም ዓይነት ሞት ይልቅ ጠንካራ ሕይወትን መፈለግ የሕይወታችንን ጉዞ ያነቃቃል፤ ከራሳችን ወጥተን ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ይገፋፋናል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሕይወታችንን በጥልቀት በመመርመር ወሰን የሌለው ጥማት አንጻር ወንድሞች እና እህቶች የሆንን ሁላችን፣ ከሚለያየን ነገር በላይ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በሚወስደን መንፈሳዊ ጉዞ ላይ እንደምንገኝ ማወቅ እንደሚቻል አጽንኦት ሰጥተዋል።
የወዳጅነትን ትስስርን ማዳበር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም፥ “እውነትን በአንድነት ስንፈልግ በመካከላችን ባለውን የብዝሃነት ሃብት፥ ከሃይማኖታዊ ወጎቻች በመማር እና እርስ በርስ በመሰባሰብ፣ አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ በማተኮር የወዳጅነት ትስስር የመጠበቅ አስፈላጊነትን አጉልተዋል። እንዲሁም ሰብዓዊ እና መንፈሳዊ ፍላጎቶችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ሰብዓዊ ክብርን መጠበቅ፣ ድሆችን መርዳት፣ ሰላምን ማስፈን እና አካባቢን መጠበቅ የመሳሰሉ ግቦችን በጋራ ማሳካት እንችላለን” ብለዋል።
በሃይማኖታዊ መካከል ስምምነትን ለመፍጠር ተጠርቷል!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማጠቃለያቸው፥ “‘ለሰው ልጅ ሲባል ሃይማኖታዊ ስምምነትን ማሳደግ’ የሚለው የጋራ ጥሪያችን አሁን የፈረምነው የጋራ ስምምንት ርዕሥ ነው” ብለዋል። “ይህን ስናደርግ አንዳንድ ጊዜ ሃይማኖትን መጠቀሚያ በማድረግ ለሚከሰቱት ቀውሶች፣ ጦርነቶች፣ ግጭቶች፣ ብዙ ሥቃዮች እና መከራዎች በጋራ ምላሽ መስጠት እንችላለን” ብለው፥ ለሁሉም ሃይማኖታዊ ወጎች የጋራ እሴቶችን በብቃት በማስተዋወቅ የጥቃት እና ግዴለሽነት ባሕልን ለማሸነፍ፣ እርቅን እና ሰላምን ለማስፋፋት መሥራት እንችላለን” የሚለውን የኢስቲቅላል የጋራ መግለጫን ጠቅሰዋል።