ፈልግ

የቬትናም የጎርፍ አደጋ የቬትናም የጎርፍ አደጋ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እስያ ውስጥ በጎርፍ የተጎዱትን በጸሎት አስታውሰው የሰላም ጥሪ በድጋሚ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀጥለው በእስያ ውስጥ በጎርፍ አደጋ የተጎዱትን ሰዎች በጸሎት አስታውሰው የሰላም ጥሪያቸውን በድጋሚ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እሁድ መስከረም 5/2017 ዓ. ም. ከምዕመናን ጋር ሆነው ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በመቀጥል በቬትናም እና ምያንማር በጎርፍ አደጋ የተጎዱን፣ የአባ ሞይስ ሊራ ሴራፊን ብጽዕናን እና በጡንቻ ነርቭ ሕመም የሚሠቃዩትን በጸሎት በማስታወስ ለዓለም ሰላም በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።


ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በመቀጠል በቬትናምና በምያንማር አውሎ ነፋስ ባስከተለው ጉዳት ለሚሰቃዩ ሕዝቦች ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል።

አውሎ ነፋሱ በቬትናም ሰሜናዊ ክፍል ባስከተለው የጎርፍ መጥለቅለቅ እና የመሬት መንሸራተትን አደጋ እስካሁን ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች ሲሞቱ 128 ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም። እስከ ዓርብ ድረስ በዛች አገር በጣለው ከባድ ዝናብ ቢያንስ 74 ሰዎች ሞተዋል በደርዘን የሚቆጠሩ ደግሞ ጠፍተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እሁድ መስከረም 5/2017 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት፥ በአደጋው ለሞቱት፣ ለተጎዱ እና ለተፈናቀሉ ሰዎች እንደሚጸልዩ ተናግረው፥ የሚወዷቸውን እና ቤት ንብረታቸውን ያጡትን እግዚአብሔር እንዲረዳቸው፣ የነፍስ አድን ዕርዳታን በማቅረብ ላይ የሚገኙትንም እንዲባርካቸው ለምነዋል።

“ግፍ እና ጥላቻ ይቁም!”
ቅዱስነታቸው በተለይም ዩክሬንን፣ ምያንማርን እና መካከለኛው ምሥራቅን ጠቅሰው ባደረጉት ንግግር፥ “ዓለምን በደም የሚቀቡ ጦርነቶችን አንርሳ” በማለት በዓለም ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን በድጋሚ ተማጽነዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለማችን ውስጥ በጦርነት ልጆቻቸውን ያጡ እናቶች እና ሕይወታቸውን በአጭሩ የተቀጩ እጅግ ብዙ ንጹሐን ሰዎች መኖራቸውን በቁጭት ተናግረዋል ።

ቅዱስነታቸው ከእስራኤላዊት እናት ራቸል ጎልድበርግ ፖሊን ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ልጇ ሄርሽ በሃማስ ታግቶ እንደ ነበር እና አስከሬኑም ከሌሎች አምስት የታጋቾች አስከሬን ጋር በነሐሴ ወር መገኘቱን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጸሎት አብረዋት እንደሆኑ ገልጸው፥ ለተጎዱት፣ ለታገቱት እና ለቤተሰቦቻቸው በጸሎት ቅርብ መሆናቸውን ተናግረዋል። በፍልስጤም እና በእስራኤል ውስጥ ያለው ግጭት፣ ግፍ እና ጥላቻ እንዲቆም ካሳሰቡ በኋላ በማከልም ታጋቾች እንዲፈቱ፣ የሰላም ድርድሩ ቀጥሎ መፍትሄዎች እንዲገኙ በማለት ልባዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ተጨማሪ የሰላም ጥሪ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው፥ በሜክስኮ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1950 ዓ. ም. የሞቱትን የንጽሕት እመቤታችን ማርያም የፍቅር ሥራ ሚስዮናውያን ማኅበር መሥራች እና ከአንድ ቀን በፊት ብጽዕናቸው የታወጀላቸውን አባ ሞይስስ ሊራ ሴራፊን አስታውሰው፥ ሕይወቱ ያለፈው ሰዎች በእግዚአብሔር እምነት እና ፍቅር እንዲያድጉ ሲያግዝ እንደ ነበር ተናግረዋል። “የእርሱ ሐዋርያዊ ቅንዓት ካህናት ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ሕዝብ መንፈሳዊ ጥቅም እንዲሰጡ ያነሳሳቸዋል” ብለው፥ ምዕመናኑ ለብጹዕ አባ ሞይስስ ሊራ ሴራፊን እንዲያጨበጭቡለት ጠይቀዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ዕለቱ በጡንቻ ነርቭ ሕመም የሚሠቃዩ ሰዎች ቀን መሆኑን በመግለጽ፥ ጣሊያን ውስጥ በዚህ ሕመም የሚሰቃዩትን እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠው፥ በሽታውን ለመዋጋት የሚደረጉ ጥናቶችን እና እንዲሁም በበሽታው የተጠቁትን የሚረዱ የበጎ ፈቃድ ድርጅቶችን አበረታትተዋል።
 

16 September 2024, 17:19