ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሲንጋፖር የሰው ልጅ ሊያሳካው የሚችለው ብርሃን ነው ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሲንጋፖር ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ለባለሥልጣናቱ፣ ለሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች እና የዲፕሎማሲ አባላት ንግግር ባደረጉበት ወቅት፥ ከሲንጋፖር ባለሥልጣናት በኩል ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ሲንጋፖር በዓለም ላይ ያላትን ልዩ ሚና በማስታወስ ሲናገሩ፥ “የመጀመሪያው ጠቀሜታ ሲንጋፖር የንግድ መስመር እንደሆነች እና የተለያዩ ሕዝቦች የሚገናኙባት አገር ናት” በማለት አስረድተዋል።
ዕድገት እና ችግርን የመቋቋም አቅም
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የከተማዋን ለውጥ በማስታወስም ባደረጉት ንግግር፥ በትሑት ጅማሬዎቿ የሥራ ዕቅዶችን እና ተነሳሽነቶችን ለማከናወን ያላትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል። ይህ ዕድገት የተገኘው በአጋጣሚ ሳይሆን በምክንያታዊ ውሳኔዎች እና በጥንቃቄ በማቀድ እንደሆነም ተናግረዋል። የመጀመርያው የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኩዋን ዩ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ራዕያቸው እና አመራራቸው ለአገሪቱ ፈጣን ዕድገት እና ለውጥ መሠረት የጣለበትን መንገድ ጠቁመዋል።
የጋራ ጥቅምን መፈለግ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ የሲንጋፖር ቁርጠኝነት ለኢኮኖሚ ዕድገት ብቻ ሳይሆን ለማኅበራዊ ፍትህ እና ለጋራ ጥቅምም ጭምር መሆኑን አስገንዝበዋል። የሕዝብ መኖሪያ ቤት፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው ትምህርት እና ቀልጣፋ የጤና አጠባበቅ ስርዓትን በማዘጋጀት ሁሉም ዜጎች በዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አገሪቱ የምታደርገውን ጥረት ተቀብለው፥ ሁሉም የሲንጋፖር ዜጎች ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ መሆን እስኪችሉ ድረስ ጥረቶች እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተጨማሪም፥ የጽንሰ ሃሳብን እና እውነታን በተግባር ውጤት መወሰን ወይም ከችሎታ እና ከጥቅም ጋር ለማያያዝ መሞከር አደጋ ሊያስከትን እንደሚችል አስጠንቅቀው፥ ይህም ባለማወቅ ሰዎችን ወደ ማግለል ሊያደርስ እንደሚችል ተናግረዋል። በዚህ ረገድ ብዙ ጊዜ እንደሚያደርጉት ሁሉ ድሆችን እና አረጋውያንን በማስታወስ እና የስደተኛ ሠራተኞችን ክብር የመጠበቅን አስፈላጊነት አሳስበዋል። “ስደተኞች ለኅብረተሰቡ ትልቅ አስተዋፅዖ ስለሚያበረክቱ ፍትሃዊ ደሞዝ ሊረጋገጥላቸው ይገባል” ብለዋል።
በዲጂታል ዘመን ማኅበራዊ ስምምነትን ማምጣት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ትክክለኛ የሰዎች ግንኙነቶችን በተለይም በዲጂታል ዘመን ውስጥ የመንከባከብን አስፈላጊነት በማጉላት፥ ሲንጋፖርውያን በሐሰት እና በማይጨበጥ እውነታ ውስጥ ግለሰቦችን ከማግለል ይልቅ መግባባትን እና አንድነትን ለማጎልበት የቴክኖሎጂ ዕድገቶችን እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።
በተጨማሪም የሲንጋፖርን የተለያዩ ጎሳዎች፣ ባሕሎች እና ሃይማኖቶች አብሮ የመኖር አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል። “ይህ ሁሉን አቀፍነት እያንዳንዱ ግለሰብ ለጋራ ጥቅም ማበርከት የሚችልበትን ሁኔታ የሚያረጋግጥ፣ ከሁሉም ጋር ገንቢ ውይይት በሚያደርጉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ገለልተኛነት ጋር የተመቻቸ ነው” ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል። የእርስ በርስ መከባበር፣ ውይይት እና ትብብር “ግጭት እና ትርምስን ለማስቀረት እና ልማቱ ሚዛናዊ እና ቀጣይነት ያለው ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ አስፈላጊ እንደሆኑ ጠቁመዋል።
ለአካባቢ ጥበቃ ቁርጠኛ መሆን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ የአካባቢን ችግር በመዋጋት ረገድ ትናንሽ መንግሥታት እንኳን ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ እና የከተማ አስተዳደርን እንደ ምሳሌ በመውሰድ ሲንጋፖር ለአካባቢ ጥበቃ ላደረገችው ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ሲንጋፖር “አካባቢያዊ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ አዳዲስ መፍትሄዎችን መፈለግ እንድትቀጥል ጥሪ አቅርበው፥ ጥረታቸው ሌሎች ሀገራትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ሊያነሳሳቸው እንደሚችል አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ እግዚአብሔር የሲንጋፖር መሪዎች ለሕዝቦቻቸው ፍላጎት እና ምኞት ምላሽ የሚሰጡበትን ብርታት እንዲሰጣቸው ጸሎት አቅርበው፥ የሀገሪቱ ቀጣይነት ያለው ጥረት ለሁሉም የሚጠቅም፣ የአንድነት እና የወንድማማችነት መንፈስ እንደሚያንጸባርቅ ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ “እግዚአብሔር ሲንጋፖርን ይባርክ!” በማለት ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።