ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የቲሞር-ሌስቴ ሕዝብ እምነቱን ባሕሉ አድርጎ እንዲይዘው አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለባለ ሥልጣናቱ ባደረጉት ንግግር፥ ቲሞር-ሌስቴ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ለነጻነቷ ስትታገል ከቆየች በኋላ ዛሬ ወደ ሰላም እና ወደ ዕድገት ጎዳና መመለስ መቻሏን ገልጸው፥ “የሰላም ጎዳናን ማግኘት እና አዲሱን የዕድገት ምዕራፍ መጀመር የተሻለ የኑሮ ሁኔታን ለማመቻቸት፣ የዚህች አገር ያልተበላሸ ውበት፣ የተፈጥሮ እና የሰው ሃብቶቿን በሁሉም ደረጃዎች ለማድነቅ ያስችላል” ብለዋል።
አዲስ የሰላም እና የነፃነት ጎህ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከቲሞር-ሌስቴ የፖለቲካ መሪዎች፣ ከሲቪል ማኅበራት ተወካዮች እና ከዲፕሎማሲያዊ አካላት ጋር ባደረጉት ንግግር፥ ከጨለማ እና አስቸጋሪ ጊዜያት በኋላ በአገሪቱ ለታየው የሰላም እና የነፃነት ጎህ እግዚአብሔርን አመስግነዋል።
የቲሞር ሕዝቦች ለነጻነት በታገሉበት አስጨናቂ ጊዜ ፈጽሞ ተስፋ እንዳልቆረጡ ገልጸው፥ በኢንዶኔዥያ ካሉ ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ጋር ሙሉ እርቅ ለመፍጠር ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል። እንደዚሁም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለተፈጠሩት ግጭቶች እግዚአብሔር ሰላምን እንዲሰጥ ጸሎት አቅርበዋል።
አዳዲስ ፈተናዎች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቲሞር-ሌስቴ የተከፈተውን አዲስ የሰላም እና የዕድገት አድማስ ሲገልጹ፥ ስደትን በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች የሚታየውን ድህነትን፣ የአልኮል ሱሰኝነትን እና የወጣት ወንጀለኞች መበራከትን ጨምሮ አዳዲስ ፈተናዎችን ለመፍታት ያግዛል ብለዋል። “በጦርነት እና በስቃይ ወቅት ብርሃን እና ብርታት ሆኖ የረዳው እምነት ዛሬም ነገም የሕዝቡ ሕይወት እንዲስተካከል ማድረጉን ይቀጥላል” ብለዋል።
በቲሞር-ሌስቴ ለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ማዕከላዊ ጭብጥ የሆነውን፥ “እምነትህ ባህልህ ይሁን” የሚለውን መሪ ቃል በማስታወስ በፖርቱጋል ቋንቋ ባስተላለፉት የማበረታቻ መልዕክታቸው፥ የቲሞር ሕዝብ መርሆች፣ የተግባር ውጥኖች እና ምርጫዎች ከወንጌል ጋር የሚስማሙ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
የትምህርት አስፈላጊነት
አገሪቱን የሚያጋጥሙ ችግሮችን በትክክል ለመጋፈጥ የሚያስችል፣ በተለይ ወደፊት አገሪቱን የሚመሩትን በማዘጋጀት ረገድ ትምህርት ለሚሰጠው አስፈላጊ ዝግጅት አጽንኦት የሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ለእንደዚህ ዓይነት ዝግጅት መሠረት ሊሆን እንደሚችል ገልጸው፥ ለተጨማሪ ዕድገት መሠረት ሆኖ እምነት የሚጣልበት፣ የተለያዩ አቀራረቦች ዕድገትን የሚያመጡ ካልሆነም እንቅፉት መሆናቸውን ለመለየት ያገለግላል ብለዋል።
የተስፋ ምክንያቶች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአገሪቱ የመንግሥት መሪዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮችን እና ለዲፕሎማቶች ያደረጉትን ንግግር ሲያጠቃልሉ፥ ከ65 በመቶ በላይ የሚሆነው የቲሞር-ሌስቴ ሕዝብ ከሠላሳ ዓመት በታች ያለውን የወጣትነት ገጽታን በማስታወስ ከዚሁ ጎን ለጎን ወጣቶች ከአፍላነታቸው እና ከብልሃታቸው ጋር የአረጋውያን ልምድ እና ጥበብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጋብዘው፥ ይህ ቅንዓት እና ጥበብ አንድ ላይ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆናቸው እና ስሜታዊነትን እና አፍራሽነትንም የማይፈቅድላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ቲሞር-ሌስቴ የገጠማትን ታላቅ የመከራ ጊዜ በትዕግስት እና በቁርጠኝነት ለመሻገር ያደረገችውን ጥረት በማሞገስ፥ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተከናወኑት ተግባራት አንጻር ሕዝባችሁ የዛሬዎችን ችግሮች በእውቀት እና በዘዴ መጋፈጥ እንደሚችል እርግጠኛ መሆን ይቻላል” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።