ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የተጠራነው እምነታችንን በብርቱ ጸሎት በተግባር ልንኖረው ነው!” አሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከማር. 7: 1-8፣ 14-15 እና 21-23 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ምንባብ ላይ በማስተንተን ባሰሙት ስብከት፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ የንጽሕና ሥርዓትን ሳይፈጽሙ ምግብ እንዲበሉ ፈቅዷል” በማለት በአንዳንድ ጸሐፍት እና ፈሪሳውያን ለቀረበባቸው ክስ ምላሽ በመስጠት ስለ ንጽሕና እና ርክሰት መናገሩን አስታውሰዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ንጽህና አስፈላጊነት የተናገረው ከውጫዊ የአምልኮ ሥርዓቶች ጋር የማይገናኝ ነገር ግን በመጀመሪያ እና በዋናነት ስለ ውስጣዊ ባህሪ መሆኑንም አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ የውጫዊ መንጻት ምልክቶችን በመቃረን፣ የሰው ልጅ በልቡ እንደ ስግብግብነት፣ ምቀኝነት፣ ትዕቢት፣ ማታለል፣ ስርቆት ወይም ስም ማጥፋት የመሳሰሉ ክፉ ሃሳቦችን ይዞ ነገር ግን እጆችን ብዙ ጊዜ መታጠቡ እንደማይጠቅም መናገሩን አስታውሰዋል።
“በበጎነት ከማይታይባቸው የአምልኮ ሥርዓቶች መጠንቀቅ አስፈላጊ እንደሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ትኩረት በመስጠት ተናግሯል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ይህ የአምልኮ ሥርዓት አንዳንድ ጊዜ ነፍስን የሚያቆስል እና ልብን የሚዘጋ፣ ከበጎ አድራጎት ጋር የሚቃረኑ ምርጫዎችን እና አመለካከቶችን ወደ ራስ እና ወደ ሌሎች ሰዎች ልብ በማምጣት ወደ ቸልተኝነት ሊያመራ ይችላል” በማለት አስረድተዋል።
ይህ ጽንሰ-ሐሳብ ለሁላችንም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት የሰጡት ቅዱስነታቸው፥ መስዋዕተ ቅዳሴን መካፈል ትተን በሐሜት የተነሳ በነገሮች እና በሰው ሁሉ ላይ በጎነትን ማጉደል አንችልም ብለዋል። ሐሜት ልብን እና ነፍስን የሚያበላሽ በመሆኑ ልንሳተፍበት እንደማይገባ አሳስበው፥ መስዋዕተ ቅዳሴን በመካፈል በጸሎታችን እግዚአብሔርን እንደምንፈራ ከገለጽን በኋላ ወደ ቤት ተመልሰን ቤተሰቦቻችን በብርድ እንዲሰቃዩ ወይም የእኛ ዕርዳታ እና እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው አረጋውያን ወላጆቻችንን ችላ የምንል ከሆነ ዋጋ ያለውን ምንም የተለየ ነገር አልሠራንም ብለዋል።
“ድርብ ሕይወትን ልንፈቅደው አንችልም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ለሰዎች መልካም እና መሐሪነት ያለው አመለካከት የሌለን ከሆነ ውጫዊ ንጽሕናችን ዋጋ እንደሌለው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ውጫዊ ንጽሕና አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ወዳጅነት በመቀነስ በሃሳቡ እና በቃሉ ፍቅርን በማሳጣት ውስጣዊ የጸጋን የማንፃት ተግባር ቸል ይላል” ሲሉ አጽንኦት በመስጠት “የተፈጠርነው ለሕይወት ንፅህና፣ ለርህራሄ እና ለፍቅር ነው” በማለት አስረድተዋል።
የግል ሕይወታችንን እንድንመለከት ምክራቸውን የለገሡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እምነታችንን በቤተ ክርስቲያን ሆነ በውጭ በተመሳሳይ መንፈስ የምንኖር እንደሆነ ጠይቀዋል። “የማስበው፣ የምናገረው እና የማደርገው ተመሳሳይ መንፈስን የሚያንፀባርቅ ነው ወይ?” ብለን ራስን መጠየቅ እንደሚገባ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ “በጸሎት የምገልጸው ነገር ለወንድሞቼ እና ለእህቶቼ ያለኝ ቅርበት እና አክብሮት ተጨባጭ እንዲሆን ለማድረግ የምጥርበት ነው ወይ?” በማለት ጠይቀዋል።
ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ “እጅግ ንጽህት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕይወታችን በልባዊ እና ተጨባጭ ፍቅር የተሞላ እንዲሆን እና ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ አምልኮ ማቅረብ እንድንችል ትርዳን” በማለት የዕለቱ ስብከታቸውን ደምድመዋል።