ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሲንጋፖር ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን መጀመራቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእስያ እና ኦሽንያ አኅጉራት በማድረግ ላይ በሚገኙት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው አራተኛ እና የመጨረሻ አገር ወደ ሲንጋፖር ደርሰዋል። ቅዱስነታቸው ወደ ደቡብ ምስራቅ እስያ አገር ሲንጋፖር አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእስያ እና በኦሽንያ አኅጉራት በሚያደርጉት የ12 ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የሲንጋፖርን የመጨረሻን ጉብኝት ጀምረዋል። ይህ በኢንዶኔዥያ፣ በፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ በቲሞር ሌስቴ እና በሲንጋፖር የሚያደርጉት 45ኛው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው እስካሁን ካደረጓቸው ጉብኝቶች መካከል ረጅሙ እንደሆነ ተነግሯል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ መስከረም 1/2017 ዓ. ም. በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር በ 8፡52 ደቂቃ  ወደ ሲንጋፖር ቻንጊ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ስማረፊያ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፥ ቅዱስነታቸውን ለመቀበል የመጨረሻ ዝግጅታቸውን በማድረግ ላይ የነበሩት የሲንጋፖር ነዋሪዎች፣ ወጣቶች እና አዛውንት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የመለስተኛ ካቶሊክ ኮሌጅ ወጣቶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ዓርብ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. ለሚያደርጉት የሃይማኖት ተቋማት ስብሰባ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት በሲንጋፖር ለሚደረገው የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት መታደስ ምንጭ እንደሚሆን፥ የሀገረ ስብከቱ የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ እና የዝግጅቱ ምክትል አስተባባሪ የሆኑት እህት ቴሬዛ ስዩ ሊ ኋንግ እምነታቸውን ገልጸዋል።

“የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት እና ከተለያዩ ሃይማኖቶች የተወጣጡ ወጣቶች አንድ ላይ መሰብሰባቸው ከቅዱስነታቸው ጉብኝት ማግሥትም ወጣቶችን ለአንድነት እና ለሰላም እንዲነሳሱ ሊያደርጋቸው ይችላል” ሲሉ የካኖሲያውያት ገዳም አባል እህት ቴሬዛ ስዩ ሊ ኋንግ ተናግረዋል።

በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገር ሲንጋፖር የገዳውያን እና ገዳማውያት ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን የተናገሩት እህት ቴሬዛ፥ በብዙ የገዳማውያን እና ገዳማውያት ማኅበራት ሕይወቱን የሚቀላቀሉት ወጣቶች ቁጥር እየቀነሰ መሆኑን ገልጸው፥ አክለውም “ዘላቂ ቁርጠኝነትን በተመለከተ ይህ ብዙዎች ሊረዱት የማይችሉት ነገር ይመስለኛል” ብለዋል።

ብዙውን ጊዜ “የአንበሶች ከተማ” ተብላ በምትጠራ ሲንጋፖር ውስጥ ክርስቲያኖች 18 በመቶ ሲሆኑ፥ ካቶሊክ ምዕመናን ደግሞ 3.5 በመቶ ወይም 176,000 ገደማ እንደሚደርሱ ይገመታል። ትልቁን ቁጥር የሚይዙት ቡዲስቶች ሲሆኑ ከ5 ሚሊዮን በላይ ወይም 33 በመቶ እንደሚደርሱ ሲነገር፣ ሙስሊሞች 15 በመቶ፣ ታኦይስቶች 11 በመቶ፣ ሂንዱዎች 5 በመቶ እና ሃይማኖት የሌላቸው 17 በመቶ ገደማ እንደሚደርሱ ይገመታል።

ከሕዝቡ መካከል 74 በመቶ ቻይናዊ፣ 13.5 በመቶ ማሌዥያዊ እና 9 በመቶ ህንዳዊ እንደሆኑ ሲነገር፥ ከተማዋ የብዝሃ-ሃይማኖታዊ እና የመድብለ ባሕል ባህሪ የያዘችበት ዋናው ምክንያት ስልታዊ አቀማመጧ በከፊል ዋና ዋና የምሥራቅ እና የምዕራብ የመርከብ መስመሮችን የሚያገናኝ በመሆኑ ነው ተብሏል።

የሲናጋፖር ከተማ ከኢኮኖሚያዊ ዕድገትዋ በስተጀርባ የፋይናንስ ማዕከል በመሆኗ እና ለስደተኞች የተሻለ የሥራ ዕድል የምታመቻች ከተማ በመሆኗ ዋና መዳረሻ እንድትሆን አድርጓታል። የሲንጋፖር የሰው ኃይል ሚኒስቴር እንደገለጹት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከታህሳስ ወር 2023 ዓ. ም. ጀምሮ የውጭ ሀገር ሠራተኞች 38 በመቶ የሚሆነውን የሠራተኛ ሃይል መጠን እንደሚይዝ ገልጸው፥ 1.52 ሚሊዮን የሚደርስ የሠራተኛ ኃይል ከእስያ፣ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ እና ከአፍሪካ የመጣ መሆኑ ታውቋል።

በሲንጋፖር ሀገረ ስብከት የስደተኞች እና የመንገደኞች ሐዋርያዊ አገልግሎት (ACMI) ኮሚሽን ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ጄኮብ ሱ እንደተናገሩት፥ “ስደተኞች ወደ ሲንጋፖር እንዲመጡ የሚያደርጋቸው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እና የባህል ስብጥር ቢኖርም፣ የሥራ ውድድር፣ የማኅበራዊ ውህደት እና ትስስር ስጋት አለ” ሲሉ ተናግረዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሲንጋፖር የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደ መልካም አጋጣሚ የሚመለከተው ለዚህ ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ጄኮብ ሱ፥ ቅዱስነታቸው በሲንጋፖር የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደሚጓዝ እና በተለይም በጣም ተጋላጭ ከሆኑ ሰዎች ጋር እንደሆነ እንዲሁም ቅዱስነታቸው ለእነዚህ ሰዎች ቅርብ መሆናቸውን የሚገልጽ፣ አንድነትን፣ መደማመጥን፣ መተሳሰብን፣ ርኅራኄን እና ለሕዝቡ ተስፋ ለመስጠት ዕድል ይሆናል” ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

“ሌላው የሲንጋፖር ትልቁ ፈተና የዜጎቿ እርጅና ነው” ያሉት የቅዱስት ቴሬዛ የአረጋውያን ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ቪክቶር ሴንግ፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓርብ መስከረም 3/2017 ዓ. ም. የሚጎበኟቸው ብዙ ቤተሰቦች አረጋውያንን መንከባከብ ባለመቻላቸው እንደ ቅድስት ቴሬዛ ወደመሳሰሉ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከላት ይወስዷቸዋል” ብለዋል።

ዝቅተኛ የወሊድ መጠን በመኖሩ ምክንያት በከፊል በሲንጋፖር ውስጥ ልጆችን የማሳደግያ ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ በሦስት ወይም በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከ 60 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ቁጥር 60 ወይም 70 በመቶው እንደሚሆን ይጠበቃል። ነገር ግን የሲንጋፖር ከተማ ነዋሪዎች ካቶሊክ እና ካቶሊክ ያልሆኑትም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የክብር እንግዳቸው አድርገው ለመቀበል ደስተኞች መሆናቸው ሚስተር ሴንግ ገልጸው፥ “በእውነቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅድስት ቴሬዛ የአረጋውያን ማዕከል በመጎበኘታቸው ደስተኞች ከመሆን በተጨማሪ ልዩ ክብር እና ዕድል ተሰጥቶናል” ሲሉ አረጋግጠዋል።

በሲንጋፖር ውስጥ ከሚታዩ ሌሎች ቁልፍ ችግሮች መካከል የመኖሪያ ቤት ፍላጎት መጨመር እና በቂ ያልሆነ የማኅበራዊ ድጋፍ እንደሆኑ ገልጸው፥ እነዚህ ሰፊ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ሕያው የሆነች ቤተ ክርስቲያንን እንደሚያገኙ እርግጠኞች ነን” ሲሉ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ቪክቶር ሴንግ ገልጸዋል።

 

12 September 2024, 11:55