ፈልግ

በፖምፔዎ ባቶኒ የተሳለ የቅዱስ ልበ ኢየሱስ መንፈሳዊ ምስል በፖምፔዎ ባቶኒ የተሳለ የቅዱስ ልበ ኢየሱስ መንፈሳዊ ምስል 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅዱስ ልበ ኢየሱስ ላይ ያተኮረ አዲስ ሐዋርያዊ ሠነድ ይፋ እንደሚያደርጉ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ልቡን የጠፋ በሚመስለው ዓለም ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ልብ ላይ የሚያተኩር አዲስ ሐዋርያዊ ሠነድ ሐሙስ ጥቅምት 14/2017 ዓ. ም. ይፋ የሚያደርጉ ሲሆን፥ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች በበዙበት በዚህ ጊዜ “እርሱ አፍቅሮናል” በሚል ርዕሥ ይፋ የሚሆነው ይህ ሠነድ የቅዱስነታቸው አራተኛ ሐዋርያዊ ሠነድ እንደሚሆን ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዛሬ ዓለም በጦርነት፣ በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ ሚዛን መዛባት፣ በፍጆታ መስፋፋት እና የሰውን ልጅ ተፈጥሮን ለመናድ በሚያሰጉ ቴክኖሎጂዎች ውስጥ ትገኛለች ከሚለው ከዚህ ሠነድ ጋር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአመለካከት ለውጥ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ የሰው ልጅ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ልብ እንደገና እንዲያገኝ አሳስበዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ራንችስኮስ ማስታወቂያ
ይህ አርተኛው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፥ “እርሱ አፍቅሮናል” በሚል ርዕሥ የተጻፈ፣ መሠረቱን በልበ ኢየሱስ ሰብዓዊ እና መለኮታዊ ፍቅር ላይ በማድረግ ጥቅምት 14/2017 ዓ. ም. እንደሚወጣ የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል አረጋግጧል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ሠነድ ይፋ ለማድረግ ማሰባቸውን ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ባቀረቡበት ዕለት ረቡዕ ግንቦት 2/2016 ዓ. ም. እንደነበር ይታወሳል።

በወቅቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሠነዱ የቤተ ክርስቲያንን የተሃድሶ ጎዳና የሚያበራ እና ትርጉም ባለው መልኩ ልቡን የጠፋ በሚመስለው ዓለም ላይ የሚያተኮር እና በእግዚአብሔር የፍቅር ገጽታዎች ላይ እንደሚያሰላስል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። በተጨማሪ ሠነዱ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የእምነት አስተምህሮች እና የከበሩ የመጽሐፍ ቅዱሳት ትውፊቶችን በማካተት ቤተ ክርስቲያኒቱን ከጥልቅ መንፈሳዊ ቁርጠኝነት ጋር እንደሚያስተዋውቅ ጠቁመዋል።

የ 1673 (እ.አ.አ) ግልጸቶች
የሠነዱ ይፋ መሆን የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ለቅድስት ማርጋሬት ሜሪ አላኮክ እንደ ጎርጎርሳውያኑ በ1673 ዓ. ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የታየበትን 350ኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል ጋር ይገናኛል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በዚያው ዓመት ታኅሣሥ 27 ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ የ26 ዓመት ወጣት ለነበረች ፈረንሳዊ መነኩሲት ተገልጦላት ፍቅሩን በተለይም ለኃጢአተኞች የማስፋፋት ተልዕኮዋን እንድትሰጥ በሰጣት አደራ መሠረት በቡርገንዲ ፓራይ-ሌ-ሞኒያል ገዳም ውስጥ የተከናወኑት እነዚህ ግልጸቶች ለ17 ዓመታት ቀጥለው እንደነበር ይታወሳል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ልቡ በእሳት ነበልባል እና በእሾህ አክሊል መከበቡን ለማርጋሬት ሜሪ አላኮክ ያሳየ ሲሆን፥ይህም በሰው ኃጢአት የደረሰውን ቁስል ያሚያመለክት እንደሆነ ታውቋል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ በዓል ቀጥሎ ያለው ዓርብ ለቅዱስ ልብ እንዲሰጥ እንደነገራት እና መጀመሪያ ላይ ቅድስት ማርጋሬት ማርያም ከብዙ መነኮሳት ጋር የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ለዓለም በመግለጥ በተልእኮዋ ጸንታ ኖራለች።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ “ውሃን ታፈልቃለህ” ሠነድ
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1956 ዓ. ም. ባሳተሙት “Haurietis Aquas” ወይም “ውሃን ታፈልቃለህ” የተሰኘውን ሠነድ ለእግዚአብሔር የሚሰጥ አምልኮ እያሽቆለቆለ በነበረበት ወቅት እንደገና ለማደስ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ለቤተ ክርስቲያን ፍላጎቶች እና ለዘመናዊው ዓለም የድነት ምልክት ያለውን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ “ውሃን ታፈልቃለህ” የተሰኘውን ሠነድ 50ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ በጻፉት መልዕክት ይህንኑ ሃሳባቸውን በማጠናከር፥ “እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ለኢየሱስ ልብ የምንሰጠው ክብር ይዘት ብቻ ሳይሆን የእውነተኛ ክርስቲያናዊ መንፈሳዊነት እምብርት ነው” በማለት ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቅዱስ ልበ ኢየሱስ የሚሰጡ ክብር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቅዱስ ልበ ኢየሱስ ጥልቅ ክብር በመግለጽ ብዙውን ጊዜ ከክህነት ተልእኮ ጋር እንደሚያይዙት ይታወቃል። የካህናት ኢዮቤልዩ በተጠናቀቀበት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2016 ዓ. ም. ባሰሙት ስብከት ካህናት ልባቸውን እንደ መልካም እረኛ እንደ ኢየሱስን ቅዱስ ልብ ወደ ጠፉት እና በሩቅ ለሚገኙት እንዲያቀኑ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ቅዱስነታቸው በዚያው በኢዮቤልዩ በዓል ወቅት በምሕረት ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ አስተንትኖ፥ “ውሃን ታፈልቃለህ” የሚለውን ሠነድ በድጋሚ እንዲመለከቱት ሐሳብ በማቅረብ “የክርስቶስ ልብ የምሕረት ማዕከል ነው” ብለው፥ የምሕረት ባህሪ በእጆቹ ሌሎችን መዳሰስ እና ራሱን ከሌሎች ጋር የሚያገናኝ እንደሆነ ገልጸዋል።

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አራተኛው ሐዋርያዊ ሠነድ
“ውሃን ታፈልቃለህ” የተሰኘው ሠነድ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሠነድ አራተኛው ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ስኔ 29/2013 ዓ. ም. ከር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ ጋር አብረው ከጻፉት “የእምነት ብርሃን” ከሚለው ሐዋርያዊ ሠነድ በመቀጠል ስለ አካባቢው ቀውስ እና ስለ ፍጥረት እንክብካቤ አስፈላጊነት በማስመልከት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 24/2015 ዓ. ም. ይፋ ያደረጉት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 3/2020 ዓ. ም. ይፋ ያደረጉት “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለው ሐዋርያዊ ሠነድ፥ በእግዚአብሔር ስም የተካሄዱ ጦርነቶችን ጨምሮ በወረርሽኝ እና በግጭቶች በተሰበረ ዓለማችን ውስጥ ወንድማማችነት እና ማህበራዊ ወዳጅነት እንዲያድግ የተማጸኑበት እንደሆነ ይታወቃል።

“ውሃን ታፈልቃለህ” የተሰኘውን አዲሱ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ሠነድ፥ የነገረ መለኮት ሊቅ በሆኑት እና የኪዬቲ-ቫስቶ ሊቀ ጳጳስ በሆኑት በአቡነ ብሩኖ ፎርቴ እና የቅዱስ ወንጌል ደቀ መዛሙርት ማኅበር ጠቅላይ አለቃ በሆኑት በእህት አንቶኔላ ፍራካሮ፥ ሐሙስ ጥቅምት 14/2017 ዓ. ም. በቫቲካን የመግለጫ ክፍል እንደሚቀርብ ታውቋል።

 

21 October 2024, 17:28