ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “እምነት 'ከሞት በኋላ ሁሉም ነገር ያበቃል' ከሚለው ፍራቻ ነፃ ያደርገናል!"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጥቅምት 6/2017 ዓ. ም. ሳምንታዊ የረቡዕ ዕለት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ባቀረቡት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፥ “እምነት ከሞት በኋላ ሁሉም ነገር ያበቃል ከሚለው ፍርሃት ነፃ ያወጣናል” ሲሉ አስገንዝበዋል። ክቡራትን እና ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በዕለቱ ያሰሙትን አስተምህሮ ሙሉ ትርጉም ከማቅረባቸን አስቀድመን፣ ያስተነተኑበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እናነብላችኋለን፥

“የምትወዱኝ ከሆነ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ። እኔም አብን እለምናለሁ፤ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ምክንያቱም ዓለም ስለማያየው እና ስለማያውቀው ነው። ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቁታላችሁ” (ዮሐ. 14.15-17)።

ክቡራት እና ክቡራን ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ለምዕመናን ያሰሙትን ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ እንደምን አረፈዳችሁ! በዛሬው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአችን መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ከገለጠልን ነገር ተነስተን በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ እንዴት እንደሚገኝ እና እንደሚሠራ ማየትን እንቀጥላለን።

በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዓመታት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ላይ ባላት እምነት ግልጽ መግለጫ መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ አልተሰማትም ነበር። በቤተ ክርስቲያን እጅግ ጥንታዊ በሆነው እና የሐዋርያት ምልክት እየተባለ በሚጠራው የሐዋርያት ጸሎተ ሃይማኖት ውስጥ፥ ‘ሁሉን ቻይ በሆነው ሰማይን እና ምድርን በፈጠረ በእግዚአብሔር አብ አምናለሁ፤ የአብ አንድ ልጅ በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ። እርሱ ከመንፈስ ቅዱስ ተወለደ፣ ተሰቃየ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፣ ወደ ሲኦል ወረደ፣ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሳ፥ ወደ ሰማይ ዐረገ’ ካለ በኋላ ምንም መግለጫ ሳይሰጥ፥ ‘በመንፈስ ቅዱስም አምናለሁ’ ይላል።

ቤተ ክርስቲያን ይህንን እምነት በጸሎት እንድትገልጽ ያደረጋት በዘመኑ የነበረው መናፍቅነት ነው። በአራተኛው ክፍለ ዘመን ቅዱስ አትናቴዎስ ይህን ሂደት ሲጀመር፥ በትክክል የመንፈስ ቅዱስን የመቀደስ እና የመለኮታዊነት ተግባር ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ሙሉ አምላክነት እርግጠኛ እንድትሆን አደረጋት። ይህም የሆነው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ381 ዓ. ም. በቁስጥንጥንያ የክርስቲያኖች አንድነት ጉባኤ ወቅት ነበር።ይህ ጉባኤ የመንፈስ ቅዱስን መለኮትነት በሚገልጹ የታወቁ ቃላት ዛሬ እንዲህ በማለት የምንደግመውን ጸሎት ሰጠን፡- ‘ሕይወትን በሚሰጥ ጌታ በመንፈስ ቅዱስ አምናለሁ፣ በነቢያት አፍ እንደ ተነገረው፥ እርሱም ከአብ እና ከወልድ ጋር የሚሰግዱለት እና የሚያከበሩት ነው’ ይላል።

መንፈስ ቅዱስ ጌታ ነው። የእግዚአብሔርን ጌትነት በሙላት የሚካፈል፣ ፈጣሪ እንጂ ፍጡር አይደለም። ለዚህም ጠንካራው ማረጋገጫ የሚሆነው፥ እርሱ ልክ እንደ እግዚአብሔር አብ እና እንደ እግዚአብሔር ወልድ ክብር እና ስግደት የሚገባው አምላክ ነው። የሃይማኖት መመሪያ ዋና አዘጋጅ የነበረው ታላቁ ቅዱስ ባዝሊዮስ ለመንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው የእኩልነት ክብር የመከራከሪያው ዋና ነጥብ ነበር።

የጉባኤው አባቶች ለመንፈስ ቅዱስ የሚሰጡት ትርጉም የመድረሻቸው ሳይሆን የመነሻቸው ነጥብ ነበር። በእርግጥ የመንፈስ ቅዱስን መለኮትነት ግልፅ ማረጋገጫ የሚያደናቅፉ ምክንያቶች አንዴ ከተሸነፉ እና ከተወገዱ በኋላ ጸሎቱ በልበ ሙሉነት በቤተ ክርስቲያን አምልኮ እና በሥነ-መለኮት ውስጥ ይፋ ሆነ። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘ ናዚንዙስ ከጉባዔው በኋላ፥ ‘ታዲያ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው? አዎ! በእርግጥ አምላክ ነው! ከአብ እና ከወልድ ጋር አንድ ከሆነ እና እውነተኛ አምላክ ከሆነ በእርግጥ እኩል ማንነት አለው’ (ኦራቲዮ 31፣ 5፡10)።

ዘወትር እሁድ በመስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የምንደግመው የእምነት አንቀጽ ለዛሬ አማኞች ምን ይለናል? ቀደም ሲል መንፈስ ቅዱስ ‘ከአብ የሰረጸ’ የሚለውን እገላለጽ በዋናነት ያሳስበ ነበር። የላቲን ቤተ ክርስቲያን ብዙም ሳይቆይ ይህንን አገላለጽ በማከል በመስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት በሚደገመው የሐዋርያት ጸሎተ ሃይማኖት ላይ መንፈስ ቅዱስ ‘ከወልድም የሰረጸ’ መሆኑን ያክላል። በላቲን ቋንቋ ‘ከወልድ’ የሚለው ‘Filioque’ ተብሎ ስለሚጠራ፣ ይህ ስም አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ይህም በምሥራቅ እና በምዕራብ ቤተ ክርስቲያናት መካከል ለተፈጠሩ ብዙ አለመግባባቶች እና መከፋፈል ምክንያት ሆኗል። እዚህ ላይ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል በተመሠረተ የውይይት መንገድ ልዩነቶችን ለማስታረቅ አጥንቶ እርስ በርስ በመግባባት በሙላት ለመቀበል ተስፋ እንድናደርግ ያስችለናል እንጂ ያለፈውን ልዩነት መመልከቱ አስፈላጊ አይደለም።

ይህንን መሰናክል ካሸነፍን በኋላ በሐዋርያት ጸሎተ ሃይማኖት አንቀጽ ላይ የተነገረውን እና ‘ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ቅዱስ’ የሚለው ዛሬ ለእኛ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ዋጋ ልንሰጠው እንችላለን። “መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን ሕይወት ምንድ ነው? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። በፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠው እስትንፋስ ሕይወትን ሰጠው። ‘ከዚህ በኋላ ጌታ እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ’ (ዘፍ. 2፡7)። አሁን በአዲስ ፍጥረት እንደ እግዚአብሔር ልጆች ለአማኞች አዲስ ሕይወት፣ የክርስቶስን እና ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ቅዱስ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ሰዎች በላከው መልዕክቱ ምዕ. 8:2 ላይ፥ “በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቶኛልና” ይላል።

በዚህ ሁሉ መካከል “ለእኛ ታላቅ እና አጽናኝ ዜና የት ይገኛል?” ብለን ብንጠይቅ መልሱ፥ “በመንፈስ ቅዱስ የተሰጠን የዘላለም ሕይወት ነው!” የሚል ነው። ሁሉም ነገር እዚህ ላይ ያበቃል፣ በምድር ላይ ለነገሠው መከራ እና ግፍ ምንም ዓይነት መፍትሄ እንደሌለ አድርገን ከማመናችን የተነሳ ከሚሰማን ፍርሃት እምነት ነፃ ያደርገናል። የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት የሚያረጋግጡልን ሌላው ነገር፥ ‘ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፥ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው መንፈስ፥ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ አማካይነት፥ ለሟች አካላቶቻችሁ ሕይወትን ይሰጠዋል’ (ሮሜ 8፡11)።

ብዙውን ጊዜ ያለ ምንም ጥፋት እምነታቸውን ለተነጠቁት እና ለሕይወት ትርጉም መስጠት የማይችሉት ይህ እምነት እንዲኖራቸው እናበረታታ። በሞቱ ይህን የማይገመት ስጦታ ያገኘልንን እርሱን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማመስገን አንዘንጋ!”

 

16 October 2024, 16:40