ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ባቀረቡበት ወቅት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ባቀረቡበት ወቅት   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚያሰፋት እና አንድ እንደሚያደርጋት ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ መስከረም 29/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባቀረቡት አስተምህሮ፥ “መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን ያሰፋታል፣ አንድ ያደርጋታል” ሲሉ አስገንዝበዋል። ክቡራትን እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዕለቱ ያቀረቡትን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባቸን አስቀድመን ያስተነተኑበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደሚከተለው እናነብላችኋለን፥

“ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱም ወረደላቸው። ‘‘ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ’ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ። እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከልከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ?” (የሐዋ. 11:15-17)።

ክቡራት እና ክቡራን ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ያሰሙትን ስብከት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ! በመንፈስ ቅዱስ እና በቤተ ክርስቲያን ላይ የጀመርነውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአችንን በመቀጠል ዛሬ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰውን እንመከታለን። በጰንጠቆስጤ ዕለት የመንፈስ ቅዱስ መውረድ ክስተት የሚጀምረው አንዳንድ የዝግጅት ምልክቶችን በማሳየት ነው። እነርሱም ኃይለኛ ንፋስ እና በእሳት የተመሰሉ ልሳኖችን በማሳየት ነው። ነገር ግን መደምደሚያውን ያገኘው፥ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር (ሐዋ. 2፡4)። የሐዋርያትን ሥራ መጽሐፍ የጻፈው ቅዱስ ሉቃስ የቤተ ክርስቲያንን ዓለም አቀፋዊነት እና አንድነት የሚያረጋግጥ መንፈስ ቅዱስ እርሱ መሆኑን አጽንዖት ሰጥቷል። ሐዋርያት በሌሎች ልሳኖች መናገር መጀመራቸው እና ኢየሱስ ክርስቶስን ለሕዝቡ ለመስበክ ከከፍታ ሥፍራ መውጣታቸው በመንፈስ ቅዱስ የመሞላት ፈጣን ውጤት ነው(ሐዋ. 2፡4)።

ይህን በማድረግ ቅዱስ ሉቃስ በሁሉም ሕዝቦች መካከል ላለው አዲስ አንድነት ምልክት የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ተልእኮ ለማጉላት ፈልጓል። መንፈስ ቅዱስ ለአንድነት ሲሠራ የምናየው በሁለት መንገድ ነው። በአንድ በኩል ቤተ ክርስቲያን ወጣ ብላ ማገልገል እናዳለባት ይልካታል። ስለዚህም እርሷ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች እና ሕዝቦች እንድትቀበል፤ በሌላ በኩል የተገኘውን አንድነት ለማጠናከር ወደ ራስዋ ትሰበስባቸዋለች። በዓለማቀፋዊነት እንድትስፋፋ እና በአንድነት እንድትጠናከር መንፈስ ቅዱስ ያስተምራታል።

ከሁለቱ የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች መካከል ዓለም አቀፋዊነት የሚለውን የመጀመሪያውን እንመልከት። በሐዋ. ሥራ ምዕራፍ 10 ላይ እንደተጠቀሰው በቆርኔሌዎስ መለወጥ ሂደት ውስጥ ዓለም አቀፋዊነትን እናያለን። በጰንጠቆስጤ ዕለት ሐዋርያት ኢየሱስ ክርስቶስን ለአይሁዶች በሙሉ፣ ለሙሴ ሕግ መምኅራን እና ለየትኛውም ሕዝብ አባል ሰበኩላቸው። ሐዋርያት አድማሳቸውን እንዲያሰፋ እና የመጨረሻውን አጥር እንዲያፈርሱ ለማነሳሳት ከመጀመሪያው ክስተት ጋር ተመሳሳይ በሆነው በበዓለ ኀምሳ ዕለት ወደ መቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ቤት ወሰዳቸው (ሐዋ. 2:10-11)።

በዚህ የሥነ-ምግባር መስፋፋት ላይ መልክዓ ምድራዊ መስፋፋት ታክሎበት እናገኛለን። በሐዋ. 16፡6-10 ላይ እንደተጠቀሰው፥ ሐዋርያው ጳውሎስ በትንሿ እስያ አዲስ ክልል ወንጌልን ማወጅ ፈለገ። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ እንደከለከላቸው ተጽፎ እናገኛለን። ሐዋርያው ወደ ቢታንያ ለመሄድ ሞከረ፤ ነገር ግን የኢየሱስ መንፈስ ግን አልፈቀደላቸውም። ለእነዚህ አስገራሚ የመንፈስ ቅዱስ ክልከላዎች ወዲያውኑ ምክንያቱን አገኘን። በሚቀጥለው ምሽት ሐዋርያው ወደ መቄዶንያ እንዲሄድ የሚል ትእዛዝ በህልም ተቀበለ። ስለዚህም ወንጌል የትውልድ አገሩን እስያ ትቶ ወደ አውሮፓ ገባ።

ሁለተኛው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ አንድነትን የሚፈጥር ነው። በሐዋ. ምዕ. 15 ውስጥ የኢየሩሳሌም ጉባኤ ተብሎ የሚጠራው ሂደት ተግባራዊነት ይታያል። ነገር ግን ችግሩ ዓለም አቀፋዊነት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የማይጎዳ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። መንፈስ ቅዱስ በጰንጠቆስጤ ዕለት በተአምራዊ እና ወሳኝ ድርጊቶች መካከል ሁል ጊዜ አንድነትን አይፈጥርም። አብዛኛውን ጊዜ ጥበብ በተሞላበት ሥራው የሰውን ልጅ ጊዜ እና ልዩነት በማክበር፣ በሰዎች እና በተቋማት ውስጥ በማለፍ፣ በፀሎት ወቅትም ፊት ለፊት በመጋፈጥ ተዓምራትን ይሠራል። ይህን ዛሬ ሲኖዶሳዊ አካሄድ እንለዋለን። በእርግጥም የሙሴ ሕግ ከአረማዊነት በተለወጡ ሰዎች ላይ ሊጣልባቸው የሚገባውን ግዴታ ያመለክታል። በኢየሩሳሌም ጉባኤ የተከሰተውም ይኸው ነው። መፍትሔው ለመላው ቤተ ክርስቲያን በታወቁት ቃላት እንዲህ ተብሎ ታውጇል፡- ‘ለጣዖት ከተሠዋ፥ ከደምም፥ ከታነቀም፥ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ’ (ሐዋ. 15፡28)።

ቅዱስ አጎስጢኖስ በመንፈስ ቅዱስ የተገኘውን አንድነት በምስል ሲያብራራ፥ “ነፍስ የሰው አካል የሆነው መንፈስ ቅዱስ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም የክርስቶስ አካል የሆነው ቤተ ክርስቲያን ነው” በማለት ይገልጻል። ይህ ምስል አንድ አስፈላጊ ነገር ለመረዳት ይረዳናል። መንፈስ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ከውጭ አይፈጥርም። አንድ እንድንሆን በማዘዝ ራሱን አይገድብም። እርሱ ራሱ የአንድነት ማሰሪያ ነውና።

እንደተለመደው ከአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን ወደ እያንዳንዳችን እንድንሸጋገር በሚረዳን ሃሳብ እንቋጫለን። የቤተ ክርስቲያን አንድነት በሰዎች መካከል ያለው አንድነት ሲሆን፥ የሚገኘውም በምስሉ ላይ እንደተገለጸው ሳይሆን ነገር ግን በሕይወት ውስጥ ነው። ሁላችንም አንድነትን እንፈልለን። ከልባችን እንመኛለን። ነገር ግን ያንን ማግኘት በጣም ከባድ ነው። በጋብቻ እና በቤተሰብ ውስጥ እንኳ ቢሆን ወደ ኅብረት እና ስምምነት መድረስ በጣም አስቸጋሪ ነው። እንዲያውም አንድነትን እና ስምምነትን ጠብቆ መቆየት በጣም ከባድ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ነው።

ምክንያቱም አዎ! ሁሉም ሰው አንድነትን ይፈልጋል። ነገር ግን በእራሱ አመለካከት ላይ በመመሥረት፣ ሌላውም ሰው ከራሱ አመለካከት ጋር ተመሳሳይ እንደሚያስብ ስለሚገምት በው። በዚህ መንገድ አንድነት ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆናል። የጰንጠቆስጤ አንድነት እንደ መንፈስ ቅዱስ ዓላማ ከሆነ፥ አንድ ሰው ራሱን ሳይሆን እግዚአብሔርን በመሐል ላይ ለማስቀመጥ ሲሞክር ነው። ክርስቲያናዊ አንድነት የሚገነባው ሌሎች እኛ ወዳለንበት እንዲደርሱ በመጠበቅ ሳይሆን በአንድነት ወደ ክርስቶስ በመገስገስ ነው። የአንድነት እና የሰላም መሣሪያ ለመሆን እንዲረዳን መንፈስ ቅዱስን እንለምነው።”


 

09 October 2024, 16:51