ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የነገረ-መለኮት ሊቃውንት በእምነት እና በውይይት ወደፊት እንዲጓዙ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ሲሲሊ ደሴት ውስጥ በሚገኝ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኙ የነገረ-መለኮት ምሁራን ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከፍታ ጀምሮ ወደ ሌሎች ዘንድ ሲደርስ ትሁት፣ ጨዋ እና ሥር-ነቀል ቃላትን በመጠቀም እያንዳንዱን ሰው ርህራሄን የሚያስተምር እና ወደ መለኮታዊ ምሥጢር ለመድረስ የሚያግዝ የነገረ-መለኮት ትምህርት” እንዲያሳድጉ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህንን የማበረታቻ የቪዲዮ መልዕክት በሲሲሊ ፓሌርሞ ከተማ በሚገኝ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለሚያስተምሩ የነገረ-መለኮት መምህራን የላኩት ረቡዕ ጥቅምት 6/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ እንደነበር ታውቋል።
ቅዱስነታቸው የተቋሙን አዲስ የትምህርት ዘመን መጀመሪያን ምክንያት በማድረግ በላኩት መልዕክታቸው፥ የጣሊያ ደሴት ብዝሃነትን፣ ውበትን እና ተግዳሮቶችን በማስታወስ፥ እነዚህ አካላት ጥረታቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
የውይይት እና የማበልጸግ ሥራ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቪዲዮ መልዕክታቸውን የጀመሩት፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ኅዳር 12 ቀን 1972 ዓ. ም. በቤሊቼ እና ፓሌርሞ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈለግ በመከተል፥ በሲሲሊ ያደረጉት የነገረ-መለኮት ፋካልቲ ጉብኝታቸውን አስታውሰዋል።
“ፋኩልቲው በጠንካራ ቤተ ክርስቲያናዊ ጥሪ የተመሠረተ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ያላቸውን የእምነት ስሜት በትኩረት ለመከታተል እና የሜዲትራኒያን ባሕር ለነገረ-መለኮት የሚያቀርባቸውን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ዋና ተዋናይ እንዲሆን በታሪክ የተጠራ ነው” በማለት ሊቃውንቱን አበራትተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ላይ፥ በሃይማኖቶች መካከል ያለው ውይይት፣ ከምሥራቁ ዓለም ጋር፣ ከእስልምና እና ከአይሁድ እምነቶች ጋር እና እንዲሁም የሰው ልጅን ክብር በሚቀንስ በባሕር ላይ የስደተኞች ሞት ላይ የሚደረጉ ውይይቶችን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተጨማሪም የሕዝብን ባሕላዊ እና ማኅበራዊ ታማኝነት ጥንካሬን በሥነ-ጽሑፍ ከሚገለጽ የባሕል ክብር እንዲወስዱ ጋብዘዋቸዋል።
የሰማዕትነት ዋጋን መክፈል
ከዚህም በላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግዛቱ ከማፍያ ቡድን ነፃ እንዲወጣ የሚናፍቁ ሰለባዎችን ጩኸት ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ ደጋግመው ገልጸው፥ ሕይወታቸውን እስከ መስጠት ድረስ በልዩ ሁኔታ ችግሩን ያለ ፍርሃት እስከ መጨረሻው ድረስ የተቃወሙትን አድንቀዋል።
“ይህች ምድር ታላላቅ ምስክሮችን እና ሰማዕታትን ያፈራች ናት” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በግዛቲቱ ውስጥ የተደራጁ ወንጀሎችን ያለማቋረጥ በመቃወም ላይ የሚገኙ መኖራቸውን በመጥቀስ፥ “ግዛቲቱ ዛሬም ቢሆን በአሳዛኝ ሁኔታ የማፍያዎች መቅሰፍት ይታይባታል” ብለዋል።
“ይህን መዘንጋት የለብንም!”
በሜዲትራኒያን አካባቢ አገራት ውስጥ በሚደረጉ ነገረ-መለኮታዊ ውይይቶች ላይ መሳተፍ፥ ወንጌልን ለመመስከር በሚደረግ ጥረት መካከል ፍትሕን ለማስፈን የሚደረግ ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባ በማስታወስ፥ እኩልነትን ማምጣት እንደሚገባ እና ንጹሐን ተጎጂዎችን መከላከል እንደሚያስፈልግ አበክረው በማሳሰብ “ክፋት በሁሉም መልኩ ሊወገድ ይገባል” ብለዋል።
ወደ መለኮታዊ ምስጢር ለመቅረብ የሚያግዝ የሥነ-መለኮት ጥናት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ መንፈስ፥ ከተስፋ እና ከቁርጠኝነት ጋር ራሱን በታሪክ ውስጥ በማስገባት በውስጡ የኢየሱስ ክርስቶስን ልግስና የሚያበራ የነገረ- መለኮት ትምህርት ያስፈልገናል ካሉ በኋላ በማጠቃለያቸውም የፋኩልቲው አባላትን እንዲጸልዩላቸው አደራ ብለዋል።