ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “በመንፈስ ቅዱስ የምትመራ ትሑት እና ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ታስፈልገናለች!"
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
16ኛውን የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ ሁለተኛ ምዕራፍ ማክሰኞ መስከረም 22/2017 ዓ. ም. ባስጀመሩበት ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ ያላትን የሰላም እና የይቅር ባይነት ተልእኮዋን ለመወጣት በመንፈስ ቅዱስ የምትመራ ትሑት እና ሲኖዶሳዊት መሆን እንዳለባት በማሳሰብ፥ ጉባኤው ከተጀመረበት ከመስከረም 30/2014 ዓ. ም. አንስቶ በተካሄደው የሲኖዶሳዊነት ጉዞ ላይ አስተንትነዋል።
የማያቋርጥ ዘላቂ ጉዞ
ቤተ ክርስቲያን ከሐዋርያት ዘመን አንስቶ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያስቀመጠውን ተልእኮ ሳታቋርጥ በመወጣት ላይ እንደምትገኝ ለጉባኤው ተሳታፊዎች በማስታወስ፥ የቤተ ክርስቲያን ዋና ተልዕኮ ኢየሱስ ክርስቶስን ለዓለም በመመስከር ሰላምን እና እርቅን ማግኘት እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመንፈስ ቅዱስን ሚናን በማስታወስ እንደተናገሩትም፥ “መንፈስ ቅዱስ የደነደነውን፣ የቀዘቀዘውን እና የተሳሳተውን ልብ በማስተካከል ወደ ትክክለኛው መንገድ ይመራል” ሲሉ አስገንዝበዋል። በተለይም የሰው ልጅ በሐዘን፣ በተስፋ መቁረጥ እና በመከፋፈል ፈተናዎች ውስጥ ሲገኝ መንፈስ ቅዱስ በስው ልጆች መካከል እንደሚገኝ ተናግረው፥ “የእግዚአብሔር የተስፋ ስጦታ በመሆኑ እንባችንን በማበስ ያጽናናል” ሲሉ አክለዋል።
በመቀጠልም “ለይቅርታ ያለንን ፍላጎት ለማወቅ ትሑታን መሆን ያስፈልጋል!” ያሉት ቅዱስነታቸው ማክሰኞ ምሽት የተካሄደውን የምሕረት ጸጋን ለማግኘት የተደረገውን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በመጥቀስ፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙትም የዕርቅ ጸጋ የተቀበሉበት ዕድል አስታውሰዋል። “ከሌሎች የተሻልን የሚያስመስለንን የኩራት መንፈስ እና ግምት ወደ ጎን በመተው ‘በእርግጥ ትሑታን ሆነናል ወይ?” ብለው ጠይቀዋል።
የሚለውጠን መንፈስ ቅዱስ ኃይል
በመቀጠል፥ የመንፈስ ቅዱስ የመለወጥ ኃይል በውስጣችን የፍቅር እና የደስታ እሳትን እንደሚቀጣጠል እና ሁሉንም የሰው ልጆች ያለ አድልዎ የሚያፈቅር እንደሆነም አስረድተዋል። እግዚአብሔር የዘወትር አፍቃሪያችን በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ዘንድ የማያቋርጥ ይቅርታ እንደሚያስፈልጋት ገልጸዋል። የጉባኤው ተሳታፊዎች በእግዚአብሔርን ወሰን የለሽ ምሕረት ላይ እንዲያስተነትኑ በማሳሰብ ሌሎችን ዘወትር ይቅር እንዲሉ እና ይህን ለማድረግ ዝግጁነቱ ከራሳችን የይቅርታ ልምድ የሚገኝ እንደሆነም አስረድተዋል።
የሲኖዶሱን ሂደት በማስመልከት ሲናገሩ፥ ጉባኤው የወቅቱ ክስተት ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኗ እራሷን በሚገባ ለማወቅ እና ተልእኳንም ለመወጣት ውጤታማ መንገዶችን በቀጣይነት የምትማርበት ጊዜ እንደሆነ ተናግረዋል። የሲኖዶሱ ጉባኤ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ምእመናን፣ ካኅናት፣ ገዳማዊያን እና ገዳማውያት በአንድነት የእግዚአብሔርን ምሕረት የሚያገለግሉበት የጋራ ጉዞ እንደሆነ ገልጸዋል።
የምዕመና ተሳትፎ አስፈላጊነት
በሲኖዶሱ ሂደት መካከል የምእመናን ተሳትፎ አስፈላጊነት የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፥ በጉባኤው መካከል የምእመናን መገኘት የጳጳሳትን ሥልጣን እንደማይቀንስ፥ ይልቁንም የቤተ ክርስቲያንን ግንኙነት የሚያጠናክር በመሆኑ መተባባር አስፈላጊ እንደሆነ በማስረዳት፥ “ብቻውን የዳነ ማንም የለም” ሲሉ ለምዕመና ንቁ ተሳትፎ አፅንዖት ሰጥተዋል።
በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1965 የመሠረቱት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እንደ ነበሩ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ዛሬ በሚካሄደው ጉባኤ መካከልም የእርሳቸው ጥበብ እንዲበዛ ተመኝተዋል። ሲኖዶሱ ቀጣይነት ያለው የመማማር ሂደት እንደሆነ በመግለጽ የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ በመንፈስ ቅዱስ የሚታደስ እና ወደ እግዚአብሔር እቅድ ለመድረስ የምታደርገው ጉዞ እንደሆነ ገልጸው፥ “የሲኖዶሱ ሂደት የመማማር ሂደት እንደሆነ፥ በዚህ ሂደትም ቤተ ክርስቲያን ራሷን በደንብ የምታውቅበት መንገድ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው መጨረሻ፥ ሁሉም የጉባኤው ተሳታፊዎች ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ራሳቸውን ግልጽ እንዲያደርጉ በማሳሰብ፥ “መንፈስ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያን እርግጠኛ መሪ እና አጽናኝ ነው” ብለው፥ “ይህን የአንድነት ጉዞ አብረን የምንጓዘው በተስፋ፣ በትህትና እና በእግዚአብሔር በመታመን ነው” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።