ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አዲስ የመረጧቸውን የሃያ አንድ ካርዲናሎች ስም ዝርዝር ይፋ አደረጉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው እሑድ መስከረም 26/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰብሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ የላቲን ሥርዓት በምትከተል ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ የጽንሰተ ማርያም ዓመታዊ በዓል በሚከበርበት በኅዳር 29/2017 ዓ. ም. ሃያ አንድ አዳዲስ ካርዲናሎች እንደሚሰየሙ አስታውቀዋል።
ሥነ-ሥርዓቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2025 የተስፋ ኢዮቤልዩ በዓል ከመከፈቱ በፊት እና ከመላው ዓለም የመጡ ተወካዮች በቫቲካን በማካሄድ ላይ የሚገኙት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ሁለተኛው ምዕራፍ ከመጠናቀቁ በፊት እንደሚፈጸም ታውቋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅርብ ጊዜ የአዳዲስ ካርዲናሎች ሹመት የተካሄደው በሲኖዶሳዊነት ላይ የተካሄደ የመጀመሪያው ምዕራፍ ጉባኤ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ቅዳሜ መስከረም 19/2016 ዓ. ም. እንደ ነበር ይታወሳል።
ቅዱስነታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ባደረጉት ንግግር እጩዎቹ ከዓለም ዙሪያ የተመረጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። “ተመራጮቹ የሚመጡባቸው አካባቢዎችም የቤተ ክርስቲያኒቱን ዓለም አቀፋዊነት እና የእግዚአብሔርን መሐሪ ፍቅር በምድር ላይ ላሉ ሰዎች ሁሉ ማወጅ መቀጠሏንም ይገልፃል” ብለው፥ “ከሮም ሀገረ ስብከት መካተታቸውም በመንበረ ጴጥሮስ እና በመላው ዓለም በምትገኝ ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን የማይነጣጠል ትስስር ያሳያል” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው ከዚህም በላይ ምእመናን በሙሉ እነዚህን አዳድስ ካርዲናሎች በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለው፥ ካርዲናሎቹ መሐሪ እና ታማኝ ሊቀ ካኅናት ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መሆናቸውን በማረጋገጥ፥ የሮም ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ሆኜ ለእግዚአብሔር ቅዱሳን በሙሉ በማቀርበው ሐዋርያዊ አገልግሎቴ እንዲረዱኝ ለአዲሶቹ ካርዲናሎች እንጸልይ” ብለዋል።
በመጪው ኅዳር 29/2017 ዓ. ም. ከሚሰየሙት ሃያ አንድ አዳዲስ ካርዲናሎች ጋር ጠቅላላው የካርዲናሎች ቁጥር ወደ 256 እንደሚያድግ እና ከእነዚህ መካከል 141 ቱ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫን መሳተፍ እንደሚችሉ ታውቋል።
ክቡራት እና ክቡራን አዲስ የተመረጡ ካርዲናሎች ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው፥
1ኛ አቡነ አንጀሎ አቼርቢ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ፤
2ኛ አቡነ ካርሎስ ጉስታቮ ካስቲሎ ማታሶሊዮ በፔሩ የሊማ ከተማ ሊቀ ጳጳስ፤
3ኛ አቡነ ቪሴንቴ ቦካሊች ኢግሊክ (ላዛሪስት) በአርጄንቲና የሳንቲያጎ ዴል ኤስተሮ ሊቀ ጳጳስ፤
4ኛ አቡነ ሉዊስ ጄራርዶ ካብሪራ ሄሬራ፣ (O.F.M) በኢኳዶር የጓያኪል ሊቀ ጳጳስ፤
5ኛ አቡነ ፈርናንዶ ናታሊዮ ቾማሊ ጋሪብ በቺሊ የሳንቲያጎ ደ ቺሊ ሊቀ ጳጳስ፤
6ኛ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ታርሲሲዮ ኢሳዎ ኪኩቺ (S.V.D) በጃፓን የቶኪዮ ከተማ ሊቀ ጳጳስ፤
7ኛ አቡነ ፓብሎ ቪርጂሊዮ ሲዮንኮ ዳቪድ፣ በፊሊፒንስ የካልኦካን ጳጳስ፤
8ኛ አቡነ ላዲስላቭ ኔሜት፣ (S.V.D) በሴርቢያ የቢኦግራድ ስሜድሬቮ ሊቀ ጳጳስ፤
9ኛ አቡነ ያይም ስፔንግለር (O.F.M) በብራዚል የፖርቶ አሌግሬ ሊቀ ጳጳስ፤
10ኛ አቡነ ኢኛስ ቤሲ ዶግቦ በአይቮሪ ኮስት የአቢጃን ከተማ ሊቀ ጳጳስ፤
11ኛ አቡነ ዣን ፖል ቬስኮ (O.P) በአልጄሪያ የአልጀርስ ሊቀ ጳጳስ፤
12ኛ አቡነ ፓስካሊስ ብሩኖ ሲዩኩር (O.F.M) በኢንዶኔዥያ የቦጎር ጳጳስ፤
13ኛ ብጹዕ አቡነ ዶሚኒክ ጆሴፍ ማቲዩ (O.F.M.Conv.) በኢራን የቴህራን ኢስፓሃን ሊቀ ጳጳስ፤
14ኛ አቡነ ሮቤርቶ ሬፖለ፣ በጣሊያን የቱሪን ከተማ ሊቀ ጳጳስ፤
15ኛ አቡነ ባልዳዛር ሬይና፣ የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ፤
16ኛ አቡነ ፍራንሲስ ሊዮ፣ በካናዳ የቶሮንቶ ከተማ ሊቀ ጳጳስ፤
17ኛ አቡነ ሮላንዳስ ማክሪካስ፣ በሮም የቅድስት ማርያም ታላቁ ባሲሊካ ሊቀ ካህናት ተባባሪ ጳጳስ፤
18ኛ አቡነ ሚኮላ ቢቾክ (C.S.R.) በሜልበርን ለዩክሬናውያን የቅዱሳን ጴጥሮስ ወጳውሎስ ሀገረ ስብከት ጳጳስ፤
19ኛ አባ ቲሞቲ ፒተር ጆሴፍ ራዲክሊፍ (OP) የነገረ መለኮት ሊቅ፤
20ኛ አባ ፋቢዮ ባጆ (C.S.) በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ምክትል ጸሐፊ፤
21ኛ አባ ጆርጅ ያኮብ ኩቫካድ፣ በቅድስት መንበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን እና የሐዋርያዊ ጉዞ ክፍል ሃላፊ ናቸው።