ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ የቡድን ሰባት አባል አገራት ሚኒስትሮችን በቫቲካን ሲቀበሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ የቡድን ሰባት አባል አገራት ሚኒስትሮችን በቫቲካን ሲቀበሉ  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያን እንዲሰጥ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ የቡድን ሰባት አባል አገራት ሚኒስትሮችን በቫቲካን ተቀብለዋል ንግግር አድርገዋል። ፍትህ፣ ዓለም አቀፍ ተደራሽነት እና ትብብር በሚሉት ላይ በማትኮር ባስተላለፉት መልዕክት፥ የዓለም መሪዎች የአካል ጉዳተኞችን ክብር በማስጠብቅ፣ በማካተት፣ እና በማገዝ ላይ ቅድሚያ እንዲሰጡ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢንዱስትሪ ከበለጸጉ የቡድን ሰባት አባል አገራት ሚኒስትሮች ጋር ጥቅምት 7/2017 ዓ. ም. በነበራቸው ቆይታ ማካተትን እና የአካል ጉዳተኞችን በማስመልከት ባሰሙት ንግግር፥ የበለጠ ፍትሃዊ እና አካታች ዓለምን ለመገንባት ላደረጉት ቁርጠኝነት ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።

እንግዶቹ ከቅዱስነታቸው ጋር የተገናኙት በጣሊያን ማዕከላዊ ክፍለ ሀገር ኡምብሪያ ውስጥ እስከ ረቡዕ ጥቅምት 6/2017 ዓ. ም ድረስ ለሦስት ቀናት ካካሄዱት የመሪዎች ስብሰባ ማጠናቀቂያ እና “ከሶልፋኛኖ ቻርተር” ፊርማ በኋላ እንደሆነ ታውቋል። ይህ ቻርተር በውስጡ ስምንት ቅድሚያ የሚሰጥባቸውን ጉዳዮች የያዘ እና የአካል ጉዳተኞች በማህበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ሙሉ ተሳትፎ የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተመልክቷል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳት ፍራንችስኮስ ለእንግዶቹ እንደተናገሩት፥ “እነዚህ መርሆች የቤተ ክርስቲያኗን የሰብዓዊ ክብር ራዕይን በጥልቅ ያስተጋባሉ፣ እያንዳንዱን ግለሰብ እንደ ሁለንተናዊ የሰው ልጅ ቤተሰብ አካል አድርጎ ዋጋን የሚሰጥ ማኅበረሰብ ለመቅረጽ ወሳኝ ናቸው ሲሉ” አስረድተዋል። በአንድ ወቅት አንድ ሰው ስለ አካል ጉዳተኞች የተናገረውን ታሪክ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፥ “ሁላችንም አንዳንድ የሚጎድሉን ነገሮች አሉን” ማለቱን አስታውሰው “ይህ እውነት ነው” ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአካል ጉዳተኞችን በማኅበራዊ ሕይወት ለማካተት ቅድሚያ እንዲሰጥ አሳስበው፥ “አካታች ዓለምን ለመፍጠር አወቃቀሮችን ማስተካከል ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ለውጥም እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተደራሽነት ጥሪ ከማድረግ በፊት ሁሉም አካላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እንቅፋቶች ተወግደው ግለሰቦች ተሰጥኦአቸውን እንዲያዳብሩ፥ የሕይወት ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን ለጋራ ጥቅም አስተዋፅዖ ማበርከት ይችላሉ” ብለዋል።

የቡድን ሰባት አባል አገራት ሚኒስትሮችን በሶልፋኛኖ ኡምብሪያ ግዛት
የቡድን ሰባት አባል አገራት ሚኒስትሮችን በሶልፋኛኖ ኡምብሪያ ግዛት

ፍትህን ለማምጣት መሥራት
ለአካል ጉዳተኞች አገልግሎቶችን መስጠት እና ኑሮአቸውን ማመቻቸት ማኅበራዊ ዕርዳታ ብቻ ሳይሆን የፍትህ ጉዳይ ነው” በማለት ያሳሰቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ ሁሉም አገራት የእያንዳንዱን ሰው ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያበረታቱ ማኅበረሰቦችን የመፍጠር ሃላፊነት እንዳለባቸው በማስገንዘብ፥ አንድን ሰው ከእነዚህ ጉዳዮች ማግለል ከባድ አድልዎ መሆኑን በማስጠንቀቅ፥ የተከበረ የሥራ ዕድል መስጠት እና በባህላዊ እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ማሳተፍ አስፈላጊ መሆኑን ደጋግመው ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂን እንደ መሣሪያ መጠቀም
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቴክኖሎጂን በማካተት ሂደት ውስጥ ያለውን ሚና በማጉላት፥ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። ይሁን እንጂ ቴክኖሎጂን በጥበብ መጠቀም እንደሚገባ በማሳሰብ ይህም እኩልነትን የሚያሰፋ እንጂ የሚያስወግድ መሆን እንደሌለበት አሳስበው፥ “ቴክኖሎጂ ወደ ጋራ ተጠቃሚነት የሚመራ፣ የእርስ በስር ግንኙነት እና የመተሳሰብ ባሕል የሚያሳድግ መሆን አለበት” ብለዋል።

የችግር ጊዜያት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ እጅግ ተጋላጭ የሆኑትን ተመጣጣኝ ባልሆነ መልኩ የሚጎዱ እና አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ቀውሶች የትኞቹ እንደሆኑ አብራርተዋል። በግጭት ሆነ በተፈጥሮ አደጋ ወቅት ማንም ሰው ወደጎን እንዳይባል፥ የአካል ጉዳተኞችን ልዩ ፍላጎት መሠረት ያደረገ ሁሉን አቀፍ የመከላከል እና የአደጋ ጊዜ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም የአሲሲውን ቅዱስ ፍራንችስኮስ ዝንባሌ በማስታወስ፥ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ የቡድን ሰባት አባል አገራት ተወካዮች በተስፋ እና በቁርጠኝነት ሥራቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበው፥ “የእያንዳንዱ ሰው ክብር ሙሉ በሙሉ እውቅና የሚያገኝበትን እና የሚከበርበትን ዓለም በጋራ መገንባት እንችላለን” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቡድን ሰባት አባል አገራት ሚኒስትሮች ጋር በቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቡድን ሰባት አባል አገራት ሚኒስትሮች ጋር በቫቲካን
19 October 2024, 16:47