ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት አገር በጦርነት ለሚሰቃዩት ሕዝቦች ያላቸውን አጋርነት ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በአመጽ የተቀሰቀሰ አሳዛኝ የጥላቻ ቀን የጀመረበት አንደኛ ዓመት በማስታወስ በቅድስት አገር ለሚገኙት ካቶሊክ ምዕምናን ሰኞ መስከረም 27/2017 ዓ. ም. በላኩት መልዕክት “አሁንም የሰው ደም እና እንባ እየፈሰሰ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
የቅድስት አገር ሕዝቦችን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና ኃያላን መንግሥታት የጦር መሣሪያዎች ድምጽን ጸጥ ማሰኘት እና የጦርነት አሳዛኝ ሁኔታን ለማስቆም አለመቻላቸው አሳፋሪ ነው” በማለት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።
ከበቀል ጋር ቁጣ እያደገ መምጣቱን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን ስለ ውይይት እና ስለ ሰላምን የሚያስቡ ሰዎች ጥቂት ብቻ እንደሆኑ ተናግረው፥ ጦርነት ሽንፈት መሆኑን በድጋሚ አስረድተዋል።
የጦር መሣሪያ መልካም የወደፊት ሕይወት የሚገነባ ሳይሆን የሚያፈርስ፣ ዓመፅ ሰላምን የማያመጣ መሆኑን ታሪክ እንደሚያረጋግጥ በማስረዳት፥ “ዓመታትን የዘለቀው ግጭት ምንም ያላስተማረን ይመስላል” ሲሉ አስረድተዋል።
እግዚአብሔር የሚወደው ተከላካይ ያጣ መንጋ
ሰላምን ለተጠማ የቅድስት አገር ትንሹ መንጋ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በቅድስት አገር የሚገኙ ካቶሊክ ምዕመናን በጸሎት እና እርስ በርስ በመዋደድ፥ በትውልድ አገራቸው ለመቆየት የፈልጉ በእግዚአብሔር የተወደዱ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋቸዋል። በዙሪያቸው ባለው ጨለማ ሳይዋጡ ፍሬ የሚያፈሩበት እና ሕይወት የሚሰጡበት መንገድ እንዲፈልጉ በማለት አሳስበዋል።
"በተቀደሱ አገሮቻችሁ ላይ ተተክላችሁ የተስፋ ቡቃያዎች እንድትሆኑ፥ ምክንያቱም የእምነት ብርሃን በጥላቻ መካከል ፍቅርን እንድትመሰክሩ ያደርጋችኋል፣ እያደገ ባለ ግጭት መካከል ጠላትነት ሲጨምር ወደ አንድነት ይመራችኋል” በማለት ጽፈዋል።
በአባታዊ ልብ መልዕክት እንደጻፉላቸው የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ዛሬ እውነተኛ ሰማዕትነት እያጋጠማቸው ያሉት ልጆቻቸው በጦርነት ውስጥ የሰላም ዘርን እንዲዘሩ እና አመጽ የሌለበት ሰላም ኃይለኛ መሆኑን እንዲመሰክሩ ይጠቀዋል።
የጸሎት እና የጾም ቀን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንንችስኮስ በመልዕክታቸው፥ ዛሬ ሰዎች ሰላምን ከወዴት ማግኘት እንደሚችሉ እንደማያውቁ ገልጸው፥ “ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰላምን መለመን ሊደክመን አይገባም” ብለዋል።
“በዚህ ቀን ሁሉም ሰው በጸሎት እና በጾም እንዲተጋ ያሰቡት ለዚህ ነው” ብለው “ታሪክን የሚቀይር የፍቅር መሣሪያ፣ እውነተኛ ጠላታችንን የሚያሸንፍ እና ጦርነትን የሚያነሳሳ ክፉ መንፈስን የምናሸንፈው በጸሎት እና በጾም ነው” ብለዋል።
“ከእናንተ ጋር ነኝ!”
የቅዱስነታቸው መልዕክት ሁለተኛው ክፍል፥ “እኔ ካንተ ጋር ነኝ፣ ዘወትር ቅርባችሁ ነኝ” በሚል የተዋቀረ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህን ቃላት ከዚህ በፊት ለወንድሞች እና እህቶች የተናገሩ ቢሆንም ነገር ግን ዛሬ በመካከለኛው ምስራቅ በጦርነት ለሚሰቃዩ ወንድሞች እና ሴቶች በሙሉ፣ ለእያንዳንዱ ቤተ እምነቶች አባላት ጭምር እንደሆነ ገልጸዋል።
በኢየሱስ አጠገብ በሐዘን እንደቆመች እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም፥ የሞቱትን ወይም የቆሰሉ ልጆቻቸውን እያዩ የሚያለቅሱ የጋዛ እናቶች እና ነዋሪዎቿን፣ ከሰማይ የሚዘንበውን እሳት በመፍራት ቀና ብለው ማየት የሚፈሩትን፣ ድምፅ የሌላቸውን፣ በጦርነት ውድመት የሚሰቃዩትን፣ ሰላምን እና ፍትህን የተጠሙትን በሙሉ በዕለታዊ በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ሰላም ወዳድ ለሆኑት ወንዶች እና ሴቶች፣ በዓለም ዙሪያ ለሚሰቃዩት ዕርዳታ ለሚያቀርቡት እና ብቸኝነት ለሚሰማቸው እና ለተተዉት የእግዚአብሔርን የመጽናኛ ቃል ለሚያደርሱ ብጹዓን ጳጳሳት እና ካኅናት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።
“በኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞች እና እህቶች ለሆኑት በሙሉ በልባዊ ፍቅር እባርካችኋለሁ! የሰላም ንግሥት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትጠብቃችሁ፤ የቤተ ክርስቲያን ጠባቂ ቅዱስ ዮሴፍ ይጠብቃችሁ!” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።