ፈልግ

በሊባኖስ እና በእስራኤል ድንበር የሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪዎች ማዕከል በሊባኖስ እና በእስራኤል ድንበር የሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪዎች ማዕከል 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሊባኖስ ለተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል ክብር እንዲሰጠው ጠየቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የእስራኤል ጦር ሠራዊት በደቡባዊ ሊባኖስ ተሰማርቶ በሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል ላይ የከፈተውን ተኩስ አውግዘው ለሰላም አስከባሪው ኃይል ክብር እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የእስራኤል ጦር በቅርቡ ሊባኖስ ውስጥ በከፈተው ተኩስ ቢያንስ አራት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪዎች መቁሰላቸው ሲታወስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ክስተት የተሰማቸውን ሐዘን በመግለጽ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ለሰላም አስከባሪ ኃይሉ ክብር እንዲሰጠው ተማጽነዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተማጽኖአቸውን ያቀረቡት በመካከለኛው ምሥራቅ ተኩስ እንዲቆም በድጋሚ ጥሪ ባቀረቡበት ወቅት ሲሆን፥ ከማንኛውም የዓለም መሪ በላይ፣ ከጥቅምት 2016 ዓ. ም. ጀምሮ በክልሉ ያለው ጦርነት እንዲቆም ሲማጸኑ መቆየታቸው ይታወቃል።

“ጦርነት ቅዠት ነው!” በማለት የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ ጦርነት ፈጽሞ ሰላምን እንደማያመጣ እና መቼም ቢሆን ደህንነትን እንደማያስገኝ ተናግረው፥ ጦርነት ለሁሉም ወገን በተለይም እራሳቸውን የማይሸነፉ አድርገው ለሚቆጥሩት ሽንፈት እንደሆነ አስረድተዋል።

በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉት ወደ መኖሪያቸው እንደሚመለሱ፣ የታገቱትም በአስቸኳይ እንደሚፈቱ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ የጦርነቱ ተጎጂዎችን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል። ይህ በጥላቻ እና በቂም በቀል የተፈጠረ ከፍተኛ አላስፈላጊ ስቃይ በቅርቡ እንዲያበቃ እንደሚጸልዩ ተናግረዋል።

ለዩክሬን እና ለሄይቲ የሚደረጉ የሰላም ጸሎቶች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጦርነት ውስጥ የምትገኝ ዩክሬይንን በማስታወስ እንደተናገሩት፥ የአገሪቱ ሕዝብ በመጪዎቹ የአውሮፓ ክረምት ወራት ለከባድ ብርድ እንዳይጋለጥ በማለት ጥሪ አቅርበው፥ በሰላማዊው ህዝብ ላይ የሚካሄደው የአየር ድብደባ እንዲቆም በአጽንኦት ጥሪ አቅርበው፥ “ከእንግዲህ ንፁሀንን መግደል አይቻልም!” ብለዋል።

ሄይቲንም ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዚያች አገር ውስጥ የሚፈጸመው የከፋ የወሮበሎች ጥቃት እና አስከፊ ድህነት የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ባለፈው ሳምንት ሄይቲ ውስጥ በምትገኝ አንዲት ትንሽ ከተማ ህጻናትን ጨምሮ ወደ 70 የሚጠጉ ሰዎች የታጠቁ ወሮበሎች በፈጸሙት ጥቃት መገደላቸው ይታወሳል።

“በሄይቲ የሚገኙ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ፈጽሞ አንርሳ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄድ ማንኛውም ዓይነት ሁከት እንዲያበቃ እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሀገሪቱ ሰላም እና እርቅ ለመፍጠር በቁርጠኝነት የጀመረውን ሥራ እንዲቀጥል ሁሉም ሰው እንዲጸልይ ጠይቀዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ በስደት ላይ ለሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት ዕርዳታን የሚለግስ ጳጳስዊ ፋውንዴሽን ለሰላም ልመና ባዘጋጀው የመቁጠሪያ ጸሎት ላይ አንድ ሚሊዮን ሕጻናት የሚሳተፉበትን ዝግጅት በማስመልከት ተወያይተ "በዩክሬን፣ በምያንማር፣ በሱዳን እና በጦርነት እና በማንኛውም ዓይነት ሁከት ለሚሰቃዩ ሌሎች አካባቢዎች ሰላም እንዲወርድ የእመቤታችንን አማላጅነት እንለምን” ብለዋል።

 

14 October 2024, 16:38