ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዓለማችን እውነተኛ ውበት ሊገኝ የሚችለው የተቸገሩትን በመንከባከብ እንደሆነ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው ለልዑካኑ ሰኞ መስከረም 20/2017 ዓ. ም. ባደረጉት ንግግር፥ “ዛሬ እየተስፋፋ የመጣው የውበት እሳቤ ከሰዎች ሁለንተናዊ ዕድገት ጋር የማይገናኝ ነገር ግን ከዓለማዊ ደስታ፣ ከንግድ እና ከማስታወቂያ መስፈርቶች ጋር መገናኘቱን በማስጠንቀቅ፥ “ይህ የተዛባ እሳቤ የሰውን ልጅ ማንነት እና ተፈጥሮን ዝቅ ወደ ማድረግ ያመራል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የሚመሩት እና “የውበት ጠባቂዎች” በሚል ስያሜ ኤኮኖሚያዊ ልማትን እያንቀሳቀሰ በሥራ እና በውበት ላይ በማትኮር አዲስ ማኅበራዊ ውህደትን ለማስተዋወቅ የሚጥሩ አትራፊ እና አትራፊ ላልሆኑ የሕዝባዊ ድርጅቶች ጥምረት ልዑካን ንግግር አድርገዋል።
ቅዱስነታቸው ልዑካኑን በቀለሜንጦስ አዳራሽ ተቀብለው ንግግር ያደረጉት ሰኞ መስከረም 20/2017 ዓ. ም. ሲሆን፥ በንግግራቸውም የእቅዱ ስያሜ ለስም ብቻ ሳይሆን በሁለት ታላላቅ ዓላማዎች ማለትም እንክብካቤ እና ውበት ላይ ያተኮረ የሕይወት ምርጫ መሆኑን አውስተው፥ የውበት ጠባቂ መሆን ትልቅ ኃላፊነት እንደሆነ እንዲሁም ለቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ እና ለመላው ኅብረተሰብ ጠቃሚ መልዕክት እንደሆነ አስረድተዋል።
“እንክብካቤ የሁሉን ሰው ክብር ለመጠበቅ የሚደረግ የማኅበረሰብ ጥረት ነው”
መንከባከብ ከጉዳት መጠበቅን፣ ሳይበላሽ ማቆየትን እና መከላከልን እንደሚያካትት የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ በኅብረተሰባችን ውስጥ ያሉ የማይጠቅሙ ወቅታዊ ፍላጎቶችን ለማስወገድ የማያቋርጥ ትኩረት እና የግል ቁርጠኝነትን እንደሚጠቅም ገልጸዋል።
እያንዳንዱ ሰው በችሎታው እና በክህሎቱ፣ በአስተዋይነቱ እና በልቡ ስለ ሌሎች ሰዎች በማሰቡ፣ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን፣ ከፍጥረት አንገብጋቢ እንክብካቤ አንፃር አንድ ነገር ማድረግ የሚችልበት የማኅበረሰብ ጥረት እንደሆነም አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዳሉት፥ እውነተኛ እንክብካቤ የሁሉንም ሰዎች ጥበቃ እና ክብር የሚያጠቃል የሥነ-ምህዳር ራዕይ፥ በተለይም በማኅበረሰቡ በመገለል ወጣ ብለው የሚኖሩ እና የተናቁ ድሆች፣ ስደተኞች፣ አረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች እንደሆኑ በመግለጽ፥ ብቻቸውን የቀሩት እና ሥር በሰደደ ሕመም የሚሰቃዩት እነዚህ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት የከበሩ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ችላ በተባሉ አካባቢዎች ውስጥ እውነተኛ ውበትን ወደነበረበት መመለስ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለእቅዱ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት የማበረታቻ መልዕክት፥ በቸልተኝነት የተተው ብዙ አካባቢዎችን ለማነቃቃት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ በአካባቢው ለሚኖሩት ሰዎች ቅድሚያ እንዲሰጡ አደራ ብለው፥ “ፍጥረትን ወደ ነበረበት ውበት መመለስ የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
የሰውን ልጅ ማንነት እና ተፈጥሮን ዝቅ የማድረግ ዝንባሌ ያላቸው የውበት ሞዴሎች
የሰውን ልጅ ማንነት እና ተፈጥሮን ዝቅ የሚያደርግ የዘመናዊው ኅብረተሰብ የውበት ሞዴሎችን የነቀፉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ይህም ብዙውን ጊዜ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ ለገበያ የቀረበ ውበት የሰውን ልጅ እና ተፈጥሮን የሚያዋርድ እንደሆነ አስረድተው፥ ነገር ግን እውነተኛ ውበት የተቀደሰ፣ ልዩ የሆነ፣ በእግዚአብሔር ፍጥረታት ላይ የሚያሰላስል፣ ጸጋን እና ቸርነትን ያጣመረ፣ ውበትን እና ሥነ-ምግባራዊ ፍጹምነትን የሚያገናኝ ነው” በማለት አስገንዝበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ለሚደገፍ፥ ለ “ውበት ተንከባካቢዎች” እቅድ ልዑካን ያደረጉትን ንግግር ሲያጠቃልሉ፥ የፕሮጀክቱ ተሳታፊዎች በሙሉ ውበትን እና ስምምነትን ወደ ነበረበት ለመመለስ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን የፈጣሪነት ሚናቸውን እንዲቀበሉ በማበረታታት፥ የትሑቱ እና ዝምተኛው የኢየሱስ ክርስቶስ አሳዳጊ፣ በአስተዋይነቱ እና በታማኝነቱ ዓለምን ወደ ውበቱ ለመመለስ አስተዋፅዖ ያደረገውን የናዝሬቱ ቅዱስ ዮሴፍ አብነት ለመከተል ቁርጠኞች እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።