ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ኃላፊነትን የሚጠይቅ በረከት መሆኑን አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን የሚገኘውን የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካን ለዘመናት ሲንከባከብ እና ሲጠብቅ ከቆየው የቫቲካን ተቋም ጋር ሰኞ ኅዳር 1/2017 ዓ. ም. ተገናኝተው ባደረጉት ንግግር፥ ባዚሊካው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በተገቢ እና ገንቢ መንገድ መጠቀም እንዲችል ምክር ለግሠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቴክኖሎጂውን ጥበብ በተመላበት መንገድ በኃላፊነት መጠቀም
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በሐዋርያዊ አገልግሎት ባዚሊካውን ሊረዱ እንደሚችሉ ገልጸው፥ “በእርግጥ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች የባዚሊካውን አገልግሎት መርዳት የሚችሉበት እምቅ አቅም ቢኖራቸውም አሻሚዎች በመሆናቸው በአግባብ እና ገንቢ በሆነ መንገድ መጠቀም ይገባል” ሲሉ አሳስበው፥ ይህ ካልሆነ ግን ውጤቱ የተገላቢጦስ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ባዚሊካው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በተገቢ እና ገንቢ መንገድ መጠቀም እንዲችል ምክር ለግሠዋል
ቅዱስነታቸው ባዚሊካው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በተገቢ እና ገንቢ መንገድ መጠቀም እንዲችል ምክር ለግሠዋል

የአጠቃቀም ደንቡ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ እንክብካቤ እና ጥበቃ ውስጥ የእምነት እና የታሪክ መኖሪያ ቦታ መሆኑን ለማረጋገጥ አስፈላጊ እንደሆነ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከዓለም ዙሪያ ወደ ባዚሊካው ለሚመጡት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሚያምኑ እና እምነትን ገና በመፈልግ ላይ የሚገኙ ሰዎችን በሙሉ የሚቀበሉበት ቦታ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ዋና እምብርት
የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መካነ መቃብር በባዚሊካው እምብርት ላይ የሚገኝ በመሆኑ የባዚሊካው የእድሳት ሥራ የባዚሊካውን ቅድስና በሚያከብር መልኩ እንዲከናወን ያሳሰቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ምዕመናንን በማጀብ እና መንፈሳዊ ጉዟቸውን በመደገፍ ረገድ የመጀመርያውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተልዕኮን የተከተል መሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

ይህን ለማሳካት ሦስት መመዘኛዎችን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጸሎት መንፈስን መከተል፣ የእምነት እይታ እና የነጋዲያኑ ልብ መንካት እንደሆኑ ገልጸዋል። የመጀመርያው ተቋሙ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የጎብኝዎች መስተጋብራዊ ተሳትፎ እንዲፈጥር እና ለቦታው ያለውን ክብር ጠብቆ እንዲሠራ የሚጠይቅ ሲሆን፥ ሁለተኛው መመዘኛ የባዚሊካው ሠራተኞች ዋና ሥራቸው አገር ጎንኚዎችን ወይም ቱሪስቶችን

ከባዚሊካው ጋር በማስተዋወቅ ላይ ያተኮረ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን እምነት እና የሳደገችውን ባህል ለማስረዳት አዲስ መንገድ በማመቻቸት ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበት፣ ሦስተኛው የቅርጻ ቅርጽ፣ ሥዕላዊ እና የሥነ ሕንፃ ጥበብን በእግዚአብሔር ሕዝብ አገልግሎት ላይ ማስቀመጥን እንደሚያካትት ተገልጿል።

በግልጽ የማይታይ ተልዕኮ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከባዚሊካ አካላዊ ሥራ ባሻገር ትኩረታቸውን በተቀደሰ ቦታ ላይ ወደ ሚፈጸመው ሌላ የጥበብ ሥራ ላይ በማዞር እንደተናገሩት፥ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካን ለሚጎበኙት ምዕመናን ዘወትር ኑዛዜያቸውን የሚያዳምጥ ካኅን ሊኖር እንደሚገባ ያላቸውን ምኞት በመግለጽ ሚናቸው ላይም አሰላስለዋል።

“እጅግ ጥበባዊ እና ውብ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ ግላዊ የመግባቢያ ጥበብም አለ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ኑዛዜን የሚያስገቡ ካኅናት ተናዛዡ ማንም ይሁን፣ ከየትም ይምጣ፣ የየትኛውም እምነት ተከታይ ይሁን ሁሉንም ነገር ይቅር ሊሉ እንደሚገባ ተናግረው፥ ወደ ባዚሊካው የሚመጣ ማንም ሳይባረክ መመለስ የለበትም” በማለት አሳስበዋል።

ለዘመናት የቆየ ተቋም
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሚያዝያ 18/1506 በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጁሊየስ ዳግማዊ የተመሠረተው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካው ተንከባካቢ እና ጠባቂ ተቋም የሐዋርያውን እና የሰማዕቱን ቅዱስ ጴጥሮስ መታሰቢያ መካነ መቃብሩን የሚጠብቀውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከቱት ነገሮች በሙሉ እንዲከታተል አደራ የተሰጠው መሆኑ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ወንጌልን ስበኩ” በሚለው ሐዋርያዊ ሠነዳቸው ውስጥ በዝርዝር ተቀምጦ እንደሚገኝ ይታወቃል።

 

12 November 2024, 16:42