የአየር ንብረት ጉባኤ ከብዙ ውጥረት የተሞላበት ውይይት በኋላ የ1 ትሪሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ መስማማቱ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከ11 ቀናት ውጥረት የተሞላበት ረጅም ድርድር በኋላ፣ ኮፕ29 (COP29) በመባል የሚታወቀው 29ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ዘመቻ አራማጆች በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ላይ “ክህደት” ተፈጽሟል ባሉት ስምምነት ተፈጽሟል።
በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ የተካሄደው 29ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ቁልፍ እና አንገብጋቢ ጉዳይ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳትን እያስተናገዱ ባሉ ታዳጊ ሀገራት እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ እንዲያስችል፣ ቃል የተገባው የገንዘብ ድጋፍ እንዲጨምር እና ተግባራዊ እንዲሆን ከፍተኛ ድርድር ሲካሄድ ነበር።
በስምምነቱ መሠረት ታዳጊው ዓለም ወደ ዝቅተኛ የካርቦን ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ቢያንስ 1.3 ትሪሊዮን ዶላር በዓመት የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ይኖርበታል የተባለ ሲሆን፥ ከዚህም ባለፈ ገንዘቡ እ.አ.አ. በ2035 በአስከፊ የአየር ሁኔታ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቋቋም ብሎም መሰረተ ልማቶችን ለመዘርጋት ይረዳል ተብሏል።
የኮፕ29 ፕሬዝዳንት የሆኑት ሙክታር ባባዬቭ በውጤቱ ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ፥ “የዓለሙ ማህበረሰብ ወደ ባኩ በመጣ ጊዜ ሰዎች ከአዘርባጃን ብዙ ውጤት እንደማይጠበቅ ገልጸው ነበር” ካሉ በኋላ፥ እንዲሁም የጉባኤው ተሳታፊዎች ሊስማሙ እንደሚችሉ ተጠራጥረው ነበር፥ ነገር ግን በሁለቱም ጉዳዮች ተሳስተዋል” ብለዋል።
ፕረዚዳንቱ አክለውም “በዚህ አንፃር፣ የባኩ ፋይናንስ ግብ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት ውስጥ ቢሊዮኖችን ወደ ትሪሊዮን ይለውጣል” ካሉ በኋላ፥ በየዓመቱ ለታዳጊ ሀገራት የሚሰጥ የአየር ንብረት ፋይናንስ ግብን በሶስት እጥፍ አሳክተናል” ያሉ ቢሆንም ሁሉም ተሳታፊዎች በእሳቸው ሃሳብ አይስማሙም።
አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት ቃል ከተገባው 300 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 1.5 ቢሊዮን ዶላሩ የሚገኘው በዋነኛነት ከእርዳታ እና ከአደጉት ሀገራት ዝቅተኛ የብድር ወለድ እንደሚገኝ የጠቆሙ ሲሆን፥ ቀሪው ከግል ባለሀብቶች እና አዳዲስ የገንዘብ ምንጮች እንደሆነ፣ ከእነዚህም ውስጥ ገና ስምምነት ላይ ባልተደረሰባቸው በቅሪተ አካል ነዳጆች እና መሰል ነገሮች ላይ ሊጣሉ ከሚችሉ ታክሶች እንደሆኑ ተገልጿል።
ይህ ህንድን የመሳሰሉ ሃገራትን ያስቆጣ ሲሆን፥ ይሄንን በማስመልከት የህንድ የልዑካን ቡድን ተወካይ የሆኑት ቻንድኒ ራይና ሲያስረዱ፥ “በውጤቱ ቅር ተሰኝተናል ይህም ያደጉ ሀገራት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በግልፅ ያሳያል” ሲሉ ተችተዋል።
“ይህ ሰነድ ከቅዠት ያለፈ ነገር ነው ብዬ አላስብም” ያሉት ቻንዲኒ፥ በእሳቸው አስተያየት ስምምነቱ ተጎጂ ሃገራት የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ትልቅነት በሚገባ እንደማይገልጽ በመጥቀስ፥ በዚህም ምክንያት የዚህን ሰነድ ተቀባይነት እንደሚቃወሙ አስረድተዋል።
በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ በተካሄደው የኮፕ29 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመሪዎች ጉባኤ ወቅት ለሁለት ሳምንታት ያህል በዘለቀው ውጥረት የተሞላበት ድርድር ላይ አንዳንድ ድሃ እና በጣም ተጋላጭ የሆኑ የዓለም ሀገራት ካደጉት ሃገራት ከሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ አብዛኛውን ድርሻ በቀጥታ ለማግኘት ከፍተኛ ትግል አድርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ ጉልህ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ካሳዩ ሃገራት ጋር ገንዘቡን ከመጋራት ይልቅ በጣም ተጋላጭ ለሆኑ ሃገራት የሚደርስ በቂ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ነበር።
ምንም እንኳን በስምምነቱ ተግባራዊነት ላይ ጥያቄዎች ቢነሱም፥ ባለፈው ዓመት በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ዋና ከተማ ዱባይ በተካሄደው የኮፕ28 የመሪዎች ጉባኤ ላይ በድንጋይ ከሰል፣ በዘይት እና በጋዝ ላይ ጥገኛ ከሆነው የሃይል አቅርቦት “ሽግግር” እንዲደረግ ጥሪ ቀርቦ ነበር።
ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ሳዑዲ አረቢያ እና አሜሪካ ያሉ ከፍተኛ የነዳጅ እና ጋዝ አምራቾችን ጨምሮ 200 ሀገራት የቅሪተ አካል ነዳጆችን ለማቆም ፍንጭ በማሳየታቸው፥ በወቅቱ ይህ እንደ አዲስ ጅማሮ ታይቶ ነበር። ሆኖም በዘንድሮ ጉባኤ ወቅት በተካሄዱ ውይይቶች ከቅሪተ አካል ነዳጆች የመሸጋገር ጥሪን በግልፅ ሳያነሱ የዱባይን ስምምነት ብቻ ጠቅሰዋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 ዓ.ም. ፓሪስ ላይ በተካሄድው 21ኛው ጉባዔ የዓለም ሀገራት በፈረሙት የፓሪስ ስምምነት የዓለም ሙቀትን 1.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ላይ ለመገድብ ተስማምተው ነበር። ይህንንም ለማሳካት እ.አ.አ በ2030 ሙቀት ማመቅ የሚችሉ የጋዝ አይነቶችን በ43 ከመቶ ለመቀነስ እና በ2050 ዓለምን ከካርበን-ዳይኦክሳይድ የፀዳ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
እጅጉን ያነሰ የአየር ንብረት ብክለት ድርሻ ይልቁንም የበዛ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት የሚያርፍባቸው አፍሪካዊያን ሀገራት የካርበን ሽያጭና ግብይትን በፍትሀዊነት የማዳረስ፣ በተፅዕኖ የሚፈተኑ ዜጎችን የመለየት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ የሚያደርግ የፖሊሲ ድጋፍና የትብብር ዕድሎች ስምምነቶቹ በትግበራቸው ወቅት ሊያጋጥሙት የሚችሉ ስጋቶች ተብለው ተቀምጠዋል።
በ አጠቃላይ የኮፕ 29 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ አፍሪካዊያን ለካርበን ሽያጭ ያላቸውን እምቅ አቅም አሟጠው በመጠቀም ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ዕድል የሚፈጥር ሆኖ ተጠናቋል።
ታዳጊ ሃገራት በሚያከናውኑት የአረንጓዴ ልማት ዘርፍ በሀገራት መካከል ያለው ትብብር እንዲጠናከር በር የሚከፍተው ስምምነቱ በቀጣይ ትግበራና ለከባቢ አየር ጥበቃ በሚያደርጉት በጎ ሚና ይመዘናል ተብሏል።
ለዚህም ኢትዮጵያና አፍሪካዊያን የጀመሯቸውን ጥረቶች እንዲያጠናክሩ የቀሯቸውን የቤት ስራዎች እንዲከውኑ ይጠበቃል።